ጀርመን ፡ ምክር ቤቱን ጥሰው ሊገቡ የነበሩት የጀርመን ተቃዋሚዎች ለምን ሰልፍ ወጡ?

ታትሟል

በጀርመን ኮሮናቫይረስን ለመግታት የወጡ ሕግጋትን በመቃወም የተካሄደው ሰልፍ ተካፋዮች የአገሪቱን ምክር ቤት ጥሰው ለመግባት መሞከራቸውን ፖለቲከኞች ኮንነዋል።

አብዛኞቹ ቀኝ ዘመም የሰልፉ ተሳታፊዎች ምከር ቤቱ ደረጃ ላይ ሲደርሱ ፖሊስ በትኗቸዋል።

የአገር ውስጥ ሚንስትሩ፤ "እንዲህ አይነት ባህሪ አንታገስም" ሲሉ ተደምጠዋል።

በርሊን በተካሄደው ሰልፍ ላይ ወደ 38 ሺህ ሰዎች ተገኝተዋል።

የቀድሞውን የኢምፔሪያል ጀርመን ሰንደቅ አላማ የያዙ ቀኝ ዘመም ተቃዋሚዎች ምክር ቤቱን ጥሰው ለመግባት መሞከራቸውን ተከትሎ፤ ፖሊስ በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን በቁጥጥር ሥር አውሏል።

የአገር ውስጥ ሚንስትሩ ሆርስት ሸፎር፤ "ምክር ቤቱ የዴሞክራሲያችን ተምሳሌት ነው። አክራሪዎች ለጥቅማቸው ሊያውሉት ሲሞክሩ መታገስ አይቻልም" ብለዋል።

ፕሬዝዳንቱ ፍራንክ ዋልተርም፤ የተፈጠረውን "የዴሞክራሲያችን ልብ ላይ የደረሰ ጥቃት" ሲሉ ነው የገለጹት።

የምክር ቤቱ ጥበቃ እንዲሻሻል ከጠየቁ መካከል ሶሻል ዴሞክራቶች ይገኙበታል።

ዋነኛውን ሰልፍ ያስተባበረው ማይክል ባልዊግ የተባለ ግለሰብ፤ ተቃዋሚዎቹ ከእሱ ንቅቃቄ ጋር እንደማይገናኙ ተናግሯል።

የሰልፉ አላማ ምንድን ነው?

የተቃውሞ ሰልፉ በፍርድ ቤት ታግዶ ነበር። ኋላ ላይ ግን ተሳታፊዎች የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ እንዲያደርጉና አካላዊ ርቀት እንዲጠብቁ ተገልጾላቸው ሰልፉ እንዲካሄድ ተፈቀደ።

ሰልፉን ተከትሎ ባጠቃላይ 300 ሰዎች ታስረዋል። 200ው ቀኝ ዘመምና በምክር ቤቱ አቅራቢያ ድንጋይ የወረወሩ ናቸው።

የሰልፉ ተሳታፊዎች ራሳቸውን ከኮሮናቫይረስ ለመከላከል የጥንቃቄ እርምጃ እየወሰዱ ስላልነበር ፖሊሶች በትነዋቸዋል።

ሰልፈኞቹ እርስ በእርስ ተጠጋግተው ነበር። እንዲያውም አንድ ላይ ተቀምጠውም ነበር።

ከታሰሩት መካከል የሴራ ተንታኝ፤ አቲላ ሂድማን ይገኙበታል።

ጀርመን እንደሌሎቹ የአውሮፓ አገሮች በከፍተኛ ሁኔታ በቫይረሱ ባትጎዳም፤ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው።

የተቃውሞ ሰልፉ የተዘጋጀው ክዌርደንከን 711 በሚባል ስቱትግራት የሚገኝ ቡድን ነው። ፌስቡክ ላይ ከ16,000 በላይ ተከታዮች ያሉት ሲሆን፤ በሚስጥራዊ የቴሌግራም ቡድን ላይ አባላቱን ያገናኛል።

ኮሮናቫይረስን ለመከላከል የወጡ ሕግጋት መሠረታዊ መብትና ነፃነትን ይጋፋሉ ብለው ያምናሉ፤ ሕግጋቱ እንዲነሱም ይሻሉ።

ከደጋፊዎቻቸው መካከል የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆን ኤፍ ኬኔዲ አጎቱ የነበረው ሮበርት ኤፍ ኬኔዲ ይገኝበታል። የጸረ ክትባት አቀንቃኙ በበርሊኑ ሰልፍ ላይም ተገናኝቷል።

ኪውአኖን ከሚባለው የሴራ ትንታኔ ቡድን ጋር የሚገናኙ መፈክሮችና ሰንደቅ አላማዎች ሰልፉ ላይ ታይተዋል።

በሰልፉ ላይ ልጆች፣ ቤተሰቦችም የተገኙ ሲሆን፤ አንዳንዶች የመቃወም መብት እንደሚሹ ተናግረዋል።

ሰልፈኞቹን በመቃወም ሌላ ሰልፍ ተካሂዶ ነበር። ወደ 100 ሰዎች "ከናዚዎችና ከፋሺስቶች ጋር ሰልፍ ወጥታችኋል" ሲሉ ተደምጠዋል።

ጀርመን ኮቪድ-19ን ለመከላከል ምን እርምጃ ወሰደች?

ጀርመን በመመርመር፣ በሽታው ከያዛቸው ሰዎች ጋር ንክኪ ያላቸውን በማግኘት፣ በማከም ወጤታማ ከሆኑ አገራት አንዷ ናት።

ከ70 ዓመት በላይ የሆኑ ሰዎች እንዳይሞቱ በመከላከል ረገድም ጥሩ ውጤት አስመዝግበዋል።

አካላዊ ርቀትን ለመጠበቅ የወጣው ሕግ ግንቦት ላይ ከላላ በኋላ ነሐሴ ላይ በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየናረ መጥቷል።

ባለፈው ሐሙስ መራሔተ መንግሥት አንጌላ መርኬል የአፍና ፊት መሸፈኛ ጭንብል ያላደረገ ሰው 50 ፓውንድ እንዲቀጣ ውሳኔ አሳልፈዋል።

እስከ ቀጣዩ ዓመት ድረስ ሕዝባዊ መሰናዶዎች ታግደዋል።

በጀርመን 242,000 ሰዎች በቫይረሱ ተይዘዋል። 9,297 ሞተዋል። ይህም ከሩሲያ፣ ከዩናይትድ ኪንግደም፣ ከስፔን፣ ከፈረንሳይና ጣልያን ያነሰ መሆኑን የጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ አሃዝ ይጠቁማል።