ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ዶናልድ ትራምፕ፡ አሜሪካ ወደ ኩባ የሚደረግ የአውሮፕላን በረራን አገደች
የትራምፕ አስተዳደር ከአሜሪካ ወደ ኩባ የሚደረግ የቻርተር አውሮፕላን በረራን በአገሪቱ ላይ የኢኮኖሚ ጫና ለመጨመር በማሰብ አገደ።
የአሜሪካ ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር ማይክ ፖምፒዮ በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ እንዳሰፈሩት "የኩባ አገዛዝ ቱሪዝምና ከጉዞ የሚገኝ ገቢን በቬንዝዌላ ለሚያካሄደው ጣልቃ ገብነት እና ጥሰትን ለመደገፍ እየተጠቀመበት ነው" ሲሉ ተናግረዋል።
አሜሪካ ባለፈው ጥቅምት ወር ወደ ኩባ ከተሞች የሚደረግ የትኛውንም የአውሮፕላን በረራ ያገደች ሲሆን ዋና ከተማዋ ሃቫና ግን በዚህ ዝርዝር ውስጥ አልተካተተችም ነበር።
በኩባ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የተነሳ የጎብኚዎች ቁጥር እጅጉን ቀንሷል።
አሜሪካ በኩባ እና በቬንዚዌላ ላይ የምትወስዳቸውን እርምጃዎች በፍሎሪዳ የሚገኙ የአሜሪካ ዜግነት ያላቸው ትውልደ ኩባውያን ይደግፉታል።
ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው ዳግም ለመመረጥ በሚያደርጉት ቅስቃሳ በዚህ ግዛት ለማሸነፍ አቅደዋል።
የቻርተር አውሮፕላኖቹ እገዳ ተግባራዊ መሆን የጀመረው ከትናንት ጀምሮ ነው።
ነገር ግን ለድንገተኛ ሕክምና ወይንም ለነፍስ አድን ሥራ ፈቃድ አግኝቶ መብረር እንደሚቻል ተገልጿል።
ወደ ኩባ የሚደረጉ የቻርተር አውሮፕላን በረራዎች የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ኦባማ እኤአ በ2014 የሁለቱን አገራት ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት ዳግም እስኪያስጀምሩ ድረስ የንግድ አውሮፕላን በረራዎች ያልሞሉትን ክፍተት መሙላት ችሎ ነበር።
የአሜሪካ የንግድ አውሮፕላኖች ወደ ኩባ የሚያደርጉትን በረራ የጀመሩት ከ50 ዓመት በኋላ በ2016 ነሐሴ ወር ላይ ነበር።
በኋላ ላይም ፕሬዝዳንት ትራምፕ የሁለቱ አገራት ግንኙነትን ቀድሞ ወደነበረበት ፍጥጫ መልሰውታል።
በግንቦት ወር የአሜሪካ የትራንስፖርት መስሪያ ቤት ወደ ኩባ የሚደረጉ የቻርተር በረራዎችን በዓመት 3600 ብቻ እንዲሆኑ ወሰነ።