ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ሲያትል ውስጥ ፖሊስ እና የተቃውሞ ሰልፈኞች ተጋጩ
ውጥረት በነገሰበት ሁኔታ አሜሪካ ውስጥ ከተካሄዱ ሰልፎች መካከል ሲያትል ውስጥ የጸረ ዘረኝነት ተቃውሞን በመደገፍ ለሰልፍ የወጡ ሰዎች ከፖሊስ ጋር መጋጨታቸው ተዘገበ።
ሰልፈኞቹ እሳት በማያያዝና መስታወቶችን በሰበሩበት ጊዜ የፖሊስ መኮንኖች ሰልፈኞቹን ለመበተን የተለያዩ ዘዴዎችን ተጠቅመዋል።
ሰልፉ በፖርትላንድ እየተካሄደ ያለውን ተቃውሞ የሚደግፈ እንደሆነም ተነግሯል።
በፖሊስና በሰልፈኞች መካከል በተከሰተው ግጭት 45 ሰዎች ተይዘው የታሰሩ ሲሆን 21 ፖሊሶች ላይ የመቁሰል ጉዳት ደርሷል።
ኦስቲን ቴክሳስ ውስጥ በጥቁሮች የተቃውሞ ሰልፍ ወቅት አንድ ሰው መገደሉም ተዘግቧል።
ፖሊስ በመጀመሪያ ደረጃ ሪፖርቱ ላይ እንዳለው ሟች መሳሪያ ይዞ የነበረ ሲሆን ከአንድ መኪና ላይ ተተኩሶበት ነው የተገደለው። ተጠርጣሪውም ተይዞ መርመራ እየተደረገበት እንደሚገኝ ፖሊስ አመልክቷል።
እየተካሄዱ ያሉት የተቃውሞ ሰልፎች ፕሬዝደንት ትራምፕ ከግዛቲቱና ከአካባቢ ባለስልጣት የቀረበባቸውን ተቃውሞ ችላ ብለው የፌደራል ኃይሎችን በማሰማራታቸው የበለጠ እንዲባባስ ምክንያት መሆኑም ተገልጿል።
በመጀመሪያ ላይ ሲያትል ውስጥ በሺህዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚ ሰልፈኞች "የፌደራል ኃይሎች ይውጡ"፣ "በጭቆና ውስጥ ነን" እና "ካለፍትህ ሰላም የለም" የሚሉ መፈክሮችን እያሰሙ ሰላማዊ ተቃውሞ እያደረጉ ነበር።
ከዚህ በኋላ እሳት ማንደድና በአካባቢው ያሉ ተቋማትን መስታወቶችን መስበርና በፖሊሶች ላይ ጥቃት መሰንዘር በመጀመራቸው ግጭቱ ተቀስቅሷል።
ፖሊስ የተካሄዱትን ተቃውሞዎች የአመጽ ድርጊት ናቸው በማለት የከሰሰ ሲሆን፤ በአንድ የፖሊስ ጣቢያ ላይ የተፈጸመውን የፈንጂ ጥቃት እየመረመረ መሆኑንም አስታውቋል። በጥቃቱ ግን በሰው ላይ ምንም አይነት ጉዳት አልተመዘገበም።
እንደ ፖርትላንድ ሁሉ ሲያትልም ባለፈው ግንቦት በፖሊስ በግፍ የተገደለውን የጆርጅ ፍሎይድ ሞትን ተከትሎ ዘረኝነትንና የፖሊስ የጭካኔ ድርጊትን በመቃወም የተራዘመ ተቃውሞዎች ሲካሄዱ ቆይተዋል።
ነገር ግን ከሁለት ሳምንት በፊት ተከታታይ የጥይት ተኩስ ክስተት ማጋጠሙን ተከትሎ በከተማዋ ውስጥ የነበረው ከፖሊስ ጣልቃ ገብነት ነጻ የሆነው የተቃውሞ አካባቢ ይዞታ እየጠበበ መምጣቱን ተከትሎ ሰልፎች እየቀነሱ መጥተው ነበር።
በተመሳሳይ በሌሎችም ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎች መካሄዳቸውን የሚወጡ ዘገባዎች አመልክተዋል።