በፌስቡክ በተዋወቀችው ውሃ አጣጯ የታገተችው አሜሪካዊት ነፃ ወጣች

ታትሟል

ማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ከተዋወቁት ሰው ጋር ትዳር የሚመሰርቱት ጥቂት አይደሉም። አንዳንዶቹ በዚህ አማካኝነት የመሰረቱት ትዳር ቢሰምርላቸውም፤ አንዳንዶች ደግሞ ያላሰቡት ወጥመድ ውስጥ መግባታቸው ይነገራል።

ውሃ አጣጭ ፍለጋ ወደ ናይጄሪያ ያመራችው አሜሪካዊትም ያጋጠማት ከዚህ የተለየ አይደለም።

በፌስቡክ ከተዋወቀችው ግለሰብ ጋር ጋብቻ ለመመስረት ወደ ናይጀሪያ ያመራችው ይህች ሴት፤ ከአንድ ዓመት በላይ ከታገተች በኋላ መለቀቋን ፖሊስ አስታወቋል።

እንደ ናይጀሪያ ፖሊስ ከሆነ ግለሰቧ ከምትኖርበት አሜሪካ ወደ ናይጀሪያ ያቀናቸው ባለፈው ዓመት የካቲት ወር ላይ ሲሆን፤ ግንቦት ወር ላይ ከ34 ዓመቱ ቹክውቡካ ኦቢያኩ ጋር በትዳር ተጣመሩ።

ነገር ግን የ46 ዓመቷ ይህች ሴት የገጠማት በህልሟም በእውኗም ያላሰበችው ነበር።

የወደፊት የትዳር አጋሬ ይሆናል ባለችው ሰው በሌጎስ በሚገኝ ሆቴል ያለፈቃዷ እንዲትቆይ ተገዳ ነበር።

ፖሊስ እንዳስታወቀው ድርጊቱን በመፈፀም የተጠረጠረው ኦቢያኩ፤ ስሟ ያልተገለፀውን የዚህችን ሴት የገንዘብ ማንቀሳቀሻ ካርዶች እንዲሁም የጡረታ ጥቅማ ጥቅሞችን ሙሉ በሙሉ ተቆጣጥሮት ነበር። ከ15 ወራት ለሚበልጥ ጊዜም 48 ሺህ ዶላር ገንዘብ የማጭበርበር አካል እንድትሆን ተገዳ ነበር።

ከዚህም በተጨማሪ ተጠርጣሪው ግለሰቧን ሌሎች የውጭ ዜጎችን እና ድርጅቶችን ለማጭበርበር ግንባር ቀደም መጠቀሚያ አድርጓት እንደነበር ፖሊስ አስታውቋል።

በዋሽንግተን ዲሲ የመንግሥት ሥራ ጡረተኛ የሆነችው ይህች ሴት፤ ያለ ፈቃዷ ለ16 ወራት በአንድ የሆቴል ክፍል ውስጥ እንድትቆይ መደረጓን ተናግራለች።

ከዚህ ጊዜ በኋላ ፖሊስ ከአንዳንድ ግለሰቦች በደረሰው ጥቆማ መሰረት ግለሰቧን ሊታደጋት እንደቻለ ተናግሯል። ግለሰቡ በቁጥጥር ሥር የዋለ ሲሆን በሳይበር ወንጀል ክስ ይመሰረትበታልም ተብሏል።

በናይጀሪያ በኦንላይን ማጭበርበር ምን ያህል የተለመደ ነው?

በአገሪቷ 'ያሁ ቦይስ' የተባሉ የኦንላይን አጭበርባሪዎች በሚሊየን የሚቆጠሩ ዶላሮችን በማጭበርበር ይታወቃሉ።

ባለፈው ወር በፌስ ቡክ የተዋወቀችውን ፍቅረኛዋን ለማግኘት ወደ ናይጀሪያ ያመራች ፊሊፒንሳዊት ሴትም ያለፈቃዷ ለ6 ወራት ከታገተች በኋላ ፖሊስ ታድጓታል።

በቅርቡም በዛችው በናይጄሪያ፣ ሁለት የማህበራዊ ሚዲያ ዝነኞች ከፍተኛ ገንዘብ በማጭበርበር በአሜሪካ ፌደራል ፖሊስ ከዱባይ ተወስደዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ከቱርክና ከጣሊያን ጋር ግንኙነት ያለው የሳይበር ማጭበርበር ወንጀል ሦስት ተጨማሪ ሰዎችን በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ፖሊስ የገለፀ ሲሆን፤ ተጠርጣሪዎቹ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ (ማስክ) አቅርቦት ጋር ተያይዞ በፈፀሙት ወንጀል ነው ክስ የተመሰረተባቸው።

በዚህ የማጭበርበር ወንጀልም ግለሰቦቹ ከ400 ሺህ ዶላር በላይ ገንዘብ እንዳገኙ ፖሊስ አስታውቋል።