ታዋቂው የምግብ ኩባንያ በትራምፕ ምክንያት አድማ ተመታበት

ሥራ አስኪያጁ ከፕሬዝደንት ትራምፕ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Reuters

የምስሉ መግለጫ, ሥራ አስኪያጁ ከፕሬዝደንት ትራምፕ ጋር
ታትሟል

በላቲን አሜሪካውያን ዘንድ ታዋቂ የሆነው የምግብ ምርቶች ኩባንያ ሥራ አስኪያጅ ትራምፕን ማንቆሎጳጰሳቸውን ተከትሎ አድማ ተመቷል።

ጎያ ፉድስ የተሰኘው ተቋም ዋና ሥራ አስኪያጅ ሮበርት ኡናንዌ ዋይት ሐውስ በተገኙበት ወቅት ነው የትራምፕ አስተዳደር ከፈጣሪ የተሰጠ ፀጋ ነው ሲሉ የተደመጡት።

በሰሜን እና ደቡብ አሜሪካ አገራት ታዋቂ የሆነው ጎያ ፉድስ አሜሪካ ውስጥ ትልቁ የሂስፓኒክ ምግብ አምራች ኩባንያ ነው።

ነገር ግን አሁን የድርጅቱ ቋሚ ደንበኞችና ስም ያላቸው ዴሞክራቶች ሸማቾች የኩባንያውን ምርቶች እንዳይገዙ ጥሪ እያቀረቡ ነው።

ባለፈው ሐሙስ ነው ሥራ አስኪያጅ ሮበርት ዋይት ሐውስ ተገኝተው ከፕሬዝደንት ዶናልድ ትራምፕ ጋር ጋዜጣዊ መግለጫ የሰጡት። ሮበርት ዋይት ሐውስ የተገኙት 'ሂስፓኒክ ፕሮስፔሪቲ ኢኒሺዬቱቭ' የተሰኘውን ውል ለመፈረም ነበር።

"በዚህ ወቅት ትራምፕን የመሰሉ መሪ ማግኘታችን እውነት ፀጋ ነው፤ ትራምፕ ገንቢ ናቸው" ሲሉ ነው ሥራ አስኪያጁ ፕሬዝደንቱን ያሞካሿቸው።

ትራምፕ ወደ ሥልጣን ለመምጣት የምረጡኝ ቅስቀሳ በሚያደርጉበት ወቅት ከሜክሲኮ የሚመጡ ስደተኞችን ወንጀለኞች ናቸው ሲሉ ገልፀዋቸው ነበር። አልፎም በደቡባዊ የአገሪቱ ክፍል የግንብ አጥር ገንብተው ከሜክሲኮና ከሌሎች የደቡብ አሜሪካ አገራት የሚመጡ ስደተኞችን እመልሳለሁ ማለታቸው አይዘነጋም።

ተቺዎች የሥራ አስኪያጁ ንግግር የደንበኞችን ስሜት ያላገናዘበ ነው ሲሉ ሰውዬውን ይወቅሳሉ።

በርካታ የማኅበራዊ ድር-አምባ ተጠቃሚዎች ከዚህ በኋላ የድርጅቱን የምግብ ምርቶች አንገዛም ሲሉ እየዛቱ ነው። አድማ በጎያ ላይ የተሰኘ 'ሃሽታግ' በማኅበራዊ መገናኛ መድረኮች ላይ ተጀምሯል።

ብዙዎች ምርቱን ከላቲን አሜሪካ ባህል ጋር አጣምረው ስለሚመለከቱት በሰውዬው አስተያየት ቅር መሰኘታቸውን ይናገራሉ።

የድርጅቱ ምርቶች ለደቡብ አሜሪካ አገራት ምግቦች እንደ ቅመም ተደርገው ይቆጠራሉ።

ታዋቂዋ ክሪሲ ቲገን እና ወጣቷ ፖለቲከኛ አሌግዛንድሪያ ኦካዚዬ-ኮርቴዝ የድርጅቱን ምርት ላለመጠቀም መወሰናቸውን አሳውቀዋል።

የኩባንያው የምግብ ምርቶች

የፎቶው ባለመብት, GOYA FOODS

ኩባንያው ያለው ነገር አለ?

ሥራ አስኪያጁ ራሳቸውን መከላከል መርጠዋል። ከቀድሞዋ ቀዳማዊት እመቤት ሚሼል ኦባማ ጋር ሰርቻለሁ ሲሉም ተናግረዋል።

"ይሄ የንግግር ነፃነት አፈና ነው" ይላሉ ሥራ አስኪያጁ። "ለተናገርኩት ነገር ይቅርታ አልጠይቅም። የዩናይትድ ስቴትስ ፕሬዝደንት በአክብሮት ሲጋብዙህ 'አይ አይመቸኝም፤ አልመጣም' ይባላል እንዴ?"

"ለፕሬዝደንት ኦባማ መንግሥት እንዲያ አላልኩም፤ ለትራምፕም እንዲያ አልልም" ይላሉ።

የድርጅቱ ደጋፊዎች ኩባንያው በዚህ ዓመት ለኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ አደጋ ጊዜ መከላከል 136 ሺህ ኪሎ ምግቦችን በእርዳታ መልክ ሰጥቷልና አድማ ሊመታበት አይገባም ሲሉ ይሞግታሉ።

ሥራ አስኪያጁ ሐሙስ ዕለት በነበረው ዝግጅት ላይ አንድ ሚሊዮን ጣሳ ሽምብራ እና አንድ ሚሊዮን የታሸጉ የምግብ ምርቶች ለእርዳታ ድርጅቶች እንደሚሰጡ ቃል ገብተዋል።

የፕሬዝደንቱ ልጅ ዶናልድ ትራምፕ ትንሹ 'ግራ ዘመሞች ፕሬዝደንታችን ታላቅ መሪ በመሆናቸው ትልቁን የሂስፓኒክ ድርጅት ለማውደም ቆርጠው ተነስተዋል' ሲሉ ወቅሷል።

ዶናልድ ትራምፕ ላቲን አሜሪካውያንን አስመለክቶ በተናገሯቸው አወዛጋቢ ንግግሮች ምክንያት በተለይ ደግሞ ሜክሲኳውያን ስደተኞች 'አስገድዶ ደፋሪዎች' ናቸው ማለታቸውን ተከትሎ በደቡብ አሜሪካውያን ዘንድ እምብዛም ተቀባይነት የላቸውም።

ሥራ አስኪያጁ የተናገሩትን ተከትሎ በርካታ የተቃውሞ ድምፆች መሰማታቸው ትራምፕ የዩናይትድ ስቴትስ ዜግነት ካላቸው ላቲን አሜሪካውያን ድምፅ ላያገኙ ይችላል እየተባለ ነው።

ምንም እንኳ በርካታ የላቲን አሜሪካ ዘር ያላቸው አሜሪካውያን ፕሬዝደንት ትራምፕን አይመርጡም ቢባልም የኩባና የቬንዙዌላ ዘር ያላቸው አሜሪካውያን ግን ለትራምፕ ያደላሉ።