በምያንማር በመሬት መንሸራተት ከ100 በላይ ሰዎች ሞቱ

ታትሟል

በሰሜን ምያንማር 'ጃዴ' የተባለ የማዕድን ማውጫ ቦታ በተከሰተ የመሬት መንሸራተት ቢያንስ 113 ሰዎች መሞታቸውን ባለሥልጣናት አስታወቁ፡፡

የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች አሁንም የጠፉ ሰዎችን እየፈለጉ ነው፡፡

የአገሪቱ የእሳትና ድንገተኛ አደጋ መሥሪያ ቤት በፌስቡክ ገጹ ላይ እንዳስታወቀው ማዕድን በማውጣት ላይ የነበሩ ሰዎች በከፍተኛ ዝናብ ሳቢያ ተገፍቶ በመጣ ጭቃ ባሉበት ተቀብረው ቀርተዋል፡፡

ፖሊስ በበኩሉ ረቡዕ ዕለት ዝናብ ከዘነበ በኋላ ሰዎች በአካባቢው እንዳይሰሩ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን አስታውሶ፤ ምንም እንኳን ማስጠንቀቂያው የበርካታ ሰዎችን ሕይወት ማትረፍ ቢችልም፤ የተወሰኑ ሰዎች ግን ማስጠንቀቂያውን ተቃውመውት ነበር ብሏል፡፡

ማኡንግ ካይንግ የተባለ የ38 ዓመት የማዕድን ሠራተኛም ሊናድ የደረሰ የቆሻሻ ክምር ማየቱንና ሰዎች "ሩጡ!" " ሩጡ!" እያሉ ሲጮሁ እንደነበር ለሮይተርስ ተናግሯል፡፡

"ይሁን እንጅ በደቂቃ ውስጥ ከተራራው ሥር ያሉት ሁሉም ሰዎች ጠፉ፤ ባዶነት ተሰማኝ ፤ በወቅቱ በጭቃው ውስጥ የተዋጡ ሰዎች ለእርዳታ ሲጮሁ ነበር፤ ግን ማንም ሊረዳቸው አልቻለም" ሲል ማኡንግ አክሏል፡፡

ምያንማር በዓለማችን ከፍተኛ 'ጃዴ' የተባለ የከበረ ማዕድን ሃብት የሚገኝባት አገር ብትሆንም፤ በማዕድን ማውጣት ሥራው ግን በርካታ አደጋዎች ሲያጋጥሙ ተስተውሏል፡፡

ከአምስት ዓመታት በፊትም በካቺን በሚገኝ የማዕድን ሥፍራ ባጋጠመ ተመሳሳይ የመሬት መንሸራተት በትንሹ የ90 ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡

ባለፈው ዓመትም በማዕድን ማውጫ ሥፍራ ባጋጠመ አደጋ ከ100 በላይ ሰዎች ሞተዋል፡፡

የምያንማር የ'ጃዴ' ንግድ በዓመት ከ30 ቢሊየን ዶላር በላይ ዋጋ አለው፡፡

በአገሪቷ ባለፈው ዓመት የማዕድን ሕግ የጸደቀ ቢሆንም፤ አሁንም መንግሥት ሕገ ወጥ የሆኑ እንቅስቃሴዎችን ማስቆም ባለመቻሉ ይተቻል፡፡