የሰሜን ኮሪያው ኪም ጆንግ ኡን ደቡብ ኮሪያ ላይ ወታደራዊ እርምጃ መውሰዱ "ለጊዜው ይቆይ" አሉ

የፎቶው ባለመብት, KCNA
ሰሜን ኮሪያ በደቡብ ኮሪያ ላይ ልታዘምት የነበረውን ጦር ለጊዜው ይቆይ እንዳለች የአገሬው መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።
ከሰሞኑ አንድ ሁለት ሲባባሉ የነበሩት ሰሜንና ደቡብ ኮሪያ ወደለየለት ጦርነት ይገቡ ይሆን የሚል ስጋት ፈጥረው ነበር።
ቁርሾው የተጀመረው ደቡብ ኮሪያ የሚገኙ ሰሜን ኮሪያን 'ከድተው' የወጡ ዜጎች ወደ ሰሜን ኮሪያ የሚልኳቸው ተንኳሽ ፊኛዎችና በራሪ ወረቀቶች ስላስቆጧት ነበር።
ይህን ተከትሎ ሰሜን ኮሪያ ሁለቱን አገራት እንዲያቀራርብ ድንበር ላይ ተከፍቶ የነበረውን ጊዜያዊ አገናኝ ቢሮን አጋይታዋለች።
ይህ እርምጃ ያልተጠበቀ ስለነበር ሁለቱ አገራት አካባቢውን ዳግም የጦር አውድማ ያደርጉት ይሆናል የሚሉ ፍርሃቶች ነበሩ።
ሰሜን ኮሪያም ቢሆን 'ከዚህ በኋላ ትዕግስት የለንም፤ ደቡብ ኮሪያን እናጠፋታለን' ሲሉ የተለመደ ዛቻና ማስፈራሪያ በብሔራዊ ቴሌቪዥናቸው ስታሰማ ነበር።
ነገር ግን የሰሜን ኮሪያው መሪ ኪም ጆንግ ኡን በመራው አንድ ስብሰባ "ለጊዜው ደቡብ ኮሪያን የማጥቃቱ እርምጃ ይቆይ" የሚል ትዕዛዝ አስተላልፏል።
ፕሬዝዳንቱ እዚህ ውሳኔ ላይ ያደረሰው ምን እንደሆነ ግን የተባለ ነገር የለም።
ምናልባት ውስጥ ውስጡን በሁለቱ ኮሪያዎች መካከል መግባባት ተደርሶ ሊሆን ይችላል ይላሉ ተንታኞች።
ደቡብ ኮሪያ ወደ ሰሜን ኮሪያ የሚላኩ ፊኛዎችንና በራሪ ወረቀቶችን ለማቆም ተስማምታም ሊሆን ይችላል የሚል ግምትም አለ።
ሰሜን ኮሪያ በበኩሏ አስባው የነበረው ወታደራዊ ጥቃት ይቆይ ከማለቷም በተጨማሪ ድንበር አካባቢ የሰቀለቻቸው ትልልቅ ድምጽ ማጉያዎችም እንዲነቀሉ ወስናለች።
የእነዚህ ድምጽ ማጉያዎች አገልግሎት የነበረው ከፍ ባለ ድምጽ ለደቡብ ኮሪያ እንዲሰማ አድርጎ ፕሮፓጋንዳ መልቀቅ ነበር።
የኪም ጆንግ ኡን እህት ኪም ዮ ጆንግ ባለፉት ሳምንታት የሰሜን ኮሪያ ሠራዊት ደቡብ ኮሪያን ድባቅ ለመምታት በከፍተኛ ተጠንቀቅ እንዲቆም ትዕዛዝ አስተላልፋ ነበር።
በ"ከሀዲዎች" ወደ አገሯ የሚለቀቁት በራሪ ወረቀቶችና ፊኛዎች እጅግ ያበሳጯት የኪም እህት በሰሜን ኮሪያ የፓርቲ መዋቅር ውስጥ ከፍተኛ ሥልጣን እንዳላት ይነገራል።












