ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
"የተከበሩ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ! እባክዎ ይፍቱን!" ኬንያዊያን
የኬንያን ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታን ሕዝባቸው "እባክዎ ክቡርንትዎ" እያላቸው ነው።
ለፕሬዝዳንቱ 'ታፈንብዎ ነጻ ያውጡን' የሚሏቸው ታዲያ በኮቪድ-19 ምክንያት ወደ ለይቶ ማቆያ የገቡ ዜጎች አይደሉም።
ወይም ደግሞ ሰዓት እላፊ ጥሰው ማረሚያ ቤት የታገቱት አይደሉም።
ወይም ደግሞ ጭምብል ሳያጠልቁ በቁጡዎቹ የኬንያ ፖሊሶች የተቀጡት አይደሉም።
ፕሬዝዳንቱን 'ይፍቱን' እያሉ እየለመኗቸው ያሉት የእንቅስቃሴ ገደቡ ጫና ፈጥሮ የሚላስ የሚቀመስ ያሳጣቸው ዜጎቻቸው እንጂ።
'በቃ! ይብቃን! አልቻንም፤ ኑሮ ከበደን። የእቅስቃሴ ገደቡ ይነሳልን እባክዎ' እየተባሉ የሚገኙት ኡሁሩ ኬንያታ ታዲያ ጆሮ ዳባ ልበስ ብለዋል።
የእርሳቸውን ዝምታ ተከትሎ ከሰሞኑ በማኅበራዊ ሚዲያው ጉዳይ ሆነው ሰንብተዋል።
የፌስቡክ ፌዝ፣ ቧልት፣ እሮሮና ንዝንዝ… ሁሉ በሰውየው ላይ ነበር ያተኮረው። ኬንያዊያን በበኩላቸው የእንቅስቃሴ ገደቡ ተጭኗቸው ነው ያሉት።
በተለይ ቅዳሜ ዕለት ለሕዝባቸው ንግግር ከማድረጋቸው ቀደም ብሎ በአገሪቱ ሌላ ወሬ ያለም አይመስል ነበር።
ብዙ ዜጎች በቅዳሜው የፕሬዝዳንቱ ንግግር ገደቡን አንስቻለው ደስ ይበላችሁ ብለው ያስደስቱናል ብሎ ጠብቀው ነበር። አልሆነም።
ሰሞኑን በኬንያ ብዙ ተመልካች ካገኙ የቪዲዮ ማኀበራዊ ቀልዶች አንዱ በኮማኪው ሙኩሜ ኦሮሶን የተቀናበረ ነበር። ቀልዱ በተንቀሳቃሽ ምሥል ተቀናብሮ ብዙ ተወዳጅነት አግኝቶ ለኬንያዊያን የሳቅ ምንጭ ሆኖላቸው ሰንብቷል።
በኬንያ ትምህርት ቤቶችም ሆነ የእምነት ቦታዎች ዝግ ናቸው። ስፖርት ማዘወተሪያዎችም ሆነ መሸታ ቤቶች ከተዘጉ ቆዩ። ከአገር መውጣት የለም፤ ወደ አገር የሚገባም የለም። በኬንያ ከተሞች መሀልም የአገር ቤት ጉዞ በከፊል ገደብ ተጥሎበታል።
ከወረርሽኙ በኋላ ከአንድ ሚሊዮን ዜጎች በላይ ሥራቸውን አጥተዋል። ሌሎች ሚሊዮኖች ደመወዝ በከፊል ነው የሚያገኙት። ብዙ ቤተሰቦች የሚላስ የሚቀመስ ማግኘት እንኳ ተስኗቸዋል።
ማጉፉሊ ኬንያን በነገር ወጋ ወጋ
ኬንያዊያንና ታንዛኒያዊያን ይቀራረባሉ። ወንድም ሕዝብ የሚባባሉ ዓይነት ናቸው። ሆኖም በመሀላቸው አንዳች የፉክክር ስሜት ሳይኖር አይቀርም።
እንደ ኬንያ ጥብቅ የእንቅስቃሴ ገደብ ያላደረገችው ጎረቤት ታንዛኒያ ታዲያ ኬንያን ለማብሸቅ በሚመስል ሁኔታ 'ትርፍ ንግግር' አብዝታለች።
አወዛጋቢው የታንዛኒያ ፕሬዝዳንት ጆን ማጉፉሊ የእንቅስቃሴ ገደብ ብሎ ነገር የለም ካሉ ቆዩ።
እንዲያውም ሰሞኑን ቫይረሱን በጸሎት ከታንዛኒያ ድራሹን አጠፋነው ሲሉ ነበር። አገራቸው ከኮሮናቫይረስ ነጻ መሆኗንም በድፍረት አውጀዋል፤ ምንም እንኳ ያመናቸው ብዙ ባይኖርም።
ለኬንያ የተወረወረ በሚመስለው ንግግራቸው ማጉፉሊ እንዲህ አሉ፣ "አንዳንድ ሕዝቦች ምግብ አጠረን ይላሉ፤ በራቸውን ቆልፈው ከርመው ነው እንዲህ የሚሉት። እኛ ስናርስ፣ ጠብ እርግፍ ስንል ከርመን እነሱ ቤት ቆልፈው ተቀምጠው…" ማጋፉሊ ቀጠሉ፤ "የአገሬ ሕዝቦች ሆይ፣ አሁን ያመረትነውን ምግም እንጠብቀው፣ እንቆጥበው፤ ለመሸጥ ስትወስኑም ዋጋውን አስወድዳችሁ ይሁን። በዋጋ ንረት አከርካሪያቸውን ስበሯቸው! ይበላቸው!"
ባለፈው ሳምንት ኬንያዊያን እጅግ ተስፋ አድርገው ነበር፤ የእንቅስቃሴ ገደቡ ይነሳል ብለው። ያ ሳይሆን ቀርቷል።
ሆኖም ኡሁሩ ኬንያታ የሰዓት እላፊ ገደቡ ላይ መጠነኛ ማሻሻያ አድርገዋል። አንዳንድ ቦታዎችም የእንቅስቃሴ ገደቡን አላልተዋል። ይህ ግን እየተቸገሩ ላሉ ኬንያውያን ምንም ነው።
ፕሬዝዳንቱ ራሳቸው ሕግ አያከብሩም?
በኬንያ ገደብ የተጣለበት የማይመስለው ዘርፍ ፖለቲካ ይመስላል። ባለፈው ሳምንት ተሟሙቆ ነበር።
በሲሲቲቪ የተቀረጸ አንድ ምስል ኬንያዊያን በማኅበራዊ ድር አምባው ሲያነጋግራሩት ነበር።
ምሥሉ ላይ ሁለት ሰዎች፣ (አንዱ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታን ይመስላል፣ ሌላኛው ደግሞ የቀድመውን ጠቅላይ ሚኒስትር ራይላ ኦዲንጋን የሚመስል ሰው ነው)፣ ሁለቱ ሰዎች በምሽት ከመኪናቸው ወርደው ግንባታ ላይ ያለ የመንገድ ሥራ ሲቆጣጠሩ ያሳያል። የመንገድ ሥራው ከቤተ መንግሥት አቅራቢያ የሚገኘው ከኬንያታ ጎዳና የሚነሳው ነው።
እነሱን የያዘው መኪና በሞተረኛ የታጀበ መሆኑና ከመኪናው በቅርብ ርቀት ደግሞ የታጠቁ ወታደሮች መታየታቸው በእርግጥም ምሥሉ ላይ የታዩት ኡሁሩና ኦዲንጋ ስለመሆናቸው ተጨማሪ መረጃን ሰጥቷል።
በምሽት መንቀሳቀስ የሚፈቀድላቸው ሰዎች አሉ። ለምሳሌ የጤና ባለሞያዎች፡፡ ራይላ ኦዲንግ ግን መርፌ ወግተው፣ መድኃኒት አዘው አያውቁም። የፖለቲካ መድኃኒት ካልሆነ…
ሕጉ በምሽት እንዲንቀሳቀሱ አይፈቅድላቸውም።
ታዲያ ሕዝቡን ከቤት አትውጣ ብለው እነርሱ ሌሊት ምን ያንጎራድዳቸዋል? ሕግ አያከብሩም ማለት ነው?
በኮቪድ-19 መሀል ፖለቲካ
ይህ ክስተት የሚያሳየው ነገር ቢኖር በኬንያ ምንም ነገር ቢቆም ፖለቲካ እንደማይቆም ነው።
ባለፈው መጋቢት አጋማሽ ቫይረሱ በኬንያ መግባቱ ከተሰማ ወዲህ ወሬ የማያጡ ኬንያዊያን ፖለቲከኞች ጭምብል አጥልቀው ተሰውረው ነበር። ኮቪድ እያዛላቸው ፍርሃት አርበድብዷቸው ይሆናል። አሁን ግን ብቅ ብቅ ማለት ጀምረዋል።
የኬንያ ፖለቲከኞች ፖለቲካ ለመፈትፈት የእምነት ሥፍራም ሆነ የቀብር ሥነ ሥርዓት አያቆማቸውም። እንዲያውም እነዚህ ሥፍራዎች ዋንኞቹ የፖለቲካ መዶለቻዎች ናቸው። ሁለቱም ተዘግተውባቸዋል ለጊዜው።
ሆኖም ከሰሞኑ የኬንያ ፖለቲከኞች ወደ መድረክ የተመለሱ ይመስላሉ። በተለይ ካለፈው ወር ጀምሮ።
ይህ የሆነው ኬንያታ ሩጫ ላይ ስለሆኑ ነው። በፈረንጆች 2022 የኡሁሩ ኬንያታ ምዕራፍ ሁለት የሥልጣን ዘመን ያበቃል።
ኡሁሩ ራሳቸውን በኬንያ ታሪክ የልማት፣ የእርቅና የብሔራዊ አንድነት ጀግና ተምሳሌት ሆነው ከቤተ መንግሥቱ መውጣት ይሻሉ። ስለዚህ ጊዜያቸው በኮቪድ-19 ሳይቃጠል መሮጥ አለባቸው። ለዚያ ይሆን በሌሊት ሹልክ ብለው እየወጡ ያሉት?
ታሪካዊው መጨባበጥ
በኬንያ ምርጫ ሲመጣ ሕዝቡ ለብሔር ቅርጫ ይወጣል። ከዚህ ቀደም በኬንያ ምድር የተደረጉ ምርጫዎች ሞት የተደገሰባቸው ነበሩ።
ይህን ነገር ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ለማጥፋት በሚል ኦዲንጋና ኡሁሩ ታሪካዊ ስምምነት አድርገዋል።
ይህም በኬንያ "The historic handshake" በሚል ይታወቃል። "ታሪካዊው መጨባበጥ" እንበለው?
በኬንያ ይህ ቃል የማይጻፍበት ጋዜጣ ማግኘት ከባድ ነው። ፖለቲካው የሚዘወረው ከዚህ ታሪካዊ መጨባበጥ ጀርባ ነው።
ኡሁሩና ኦዲንጋ የተጨባበጡት በመጋቢት 2018 ላይ ነበር። ከዚያ ወዲህ አብረው ለመሥራት ተስማምተው ለአገሪቱ አዲስ የፖለቲካ ፍኖተ ካርታ እያዘጋጅተውላት ነበር።
በሁለቱ መሀል ታዲያ ምክትል ፕሬዝዳንቱ ዊሊያም ሩቶ ይሰነቀራሉ። ሩቶ የሁለቱ ኃያላን መጨባበጥ ይረብሻቸዋል። ምክንያቱ ደግሞ በ2022 ሥልጣኑን ከኡሁሩ ለመረከብ እየተቁነጠነጡ ስለነበር ነው።
ይህ የኡሁሩና የኦዲንጋ አዲስ የፖለቲካ ፍኖተ ካርታ የዊሊያም ሩቶን ቀጣዩ የኬንያ ፕሬዝዳንት የመሆን ሕልም ያጨልመዋል።
ይህ በአንዲህ እያለ ሰኞ ለታ ዋናው የጠቅላይ ፍርድ ቤት ዳኛ ዴቪድ ማራጋ ፕሬዝዳንት 'ኡሁሩ እባክዎ ሕዝብዎ ላይ የጫኑትን ገደብ ያንሱት' ሲሉ ለብዙሃን ኬንያዊያን ድጋፍ ሰጥተዋል።
ኡሁሩን ሕግ አታከብርም በሚል በተቹበት በዚህ ንግግራቸው ዋናው ዳኛ "እኔ የተራውን ኬንያዊ ድምጽ ካላስተጋባሁማ ለምን በዚህ ሥልጣን እቀመጣለሁ?" ብለዋል።
ይህ ሁሉ ሲቦተለክ ታዲያ በኬንያ የኮቪድ-19 ተያዦችና ሟቾች ቁጥር ሽቅብ መገስገሱን ለአፍታም አልተወም።
የተያዙት 3 ሺህ ሊሞሉ ጥቂት ቀርቷቸዋል። የሞቱት 88 ደርሰዋል።
መንግሥት በተለይ በመጪዎቹ ነሐሴና መስከረም ወራት በቀን የሚያዘው ሰው ቁጥር 200 እና ከዚያ በላይ ይሆናል ብሎ ሰግቷል።
ኬንያዊያን በጥቅሉ ፖለቲከኞቻቸውን አያምኗቸውም።
በዚህ ክፉ ጊዜም ቢሆን ፖለቲካ ጨዋታቸውን እንደማያቆሙ ይገነዘባሉ። ወረርሽኙ ሲንሰራፋ የጠፉ ፖለቲከኞች ወረርሽኙ ረገብ ሲልም ጭንብላቸውን አጥልቀው ዝም እንዲሉላቸው ይፈልጋሉ። ጭንብላቸው ሳል ብቻ ሳይሆን ከንቱ ንግግርም ቢከላከልላቸው ምርጫቸው ነው።
እነ ኡሁሩም እነ ኦዲንጋም በሌሊት ከቤተ መንግሥት ድንኳን እየሰበሩ መንገድ መጎብኘታቸውን ከቀጠሉ ኬንያዊያን ሁለቱ መሪዎች ቀጥሎ የሚጎበኙት ጎዳና ወደ ሥራ ስምሪት የሚወስድ መሆን ይኖርበታል ይላሉ።