የጉዞ እቀባ የተነሳላቸው ጣሊያናዊያን በደስታ እየተቃቀፉ ነው

ታትሟል

የጣሊያኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ኮንቴ የእቀባውን መነሳት ተከትሎ ባደረጉት ተስፋን ፈንጣቂ ንግግር፣ "አሁን ፈገግ ልንል፣ ልንደሰት ይገባናል፤ ከዚያ ሁሉ መከራ እየወጣን ስለሆነ…" ብለዋል።

ቀጥለውም "አሁን አገራችንን በኢኮኖሚ የመጠገን ሥራን እናፋፍማለን" ብለዋል።

ጣሊያን 234 ሺህ ዜጎቿ በቫይረሱ ተይዘውባት 33 ሺህ 600 ሰዎች ሞተውባት ነው አሁን መጠነኛ ፋታን ያገኘችው። በወረርሽኙ መነሻ ሰሞን ከዓለም አገራት ቫይረሱ ክፉኛ ካጎሳቆላቸው አገሮች በአንደኛ ደረጃ የምትጠራ አገር ነበረች።

አሁን ባለው ደረጃ ጣሊያን በቫይረሱ የሟቾች ቁጥር አሜሪካንና ዩናይትድ ኪንግደምን ተከትላ በሦስተኛ ደረጃ ላይ ትገኛለች።

ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ በተስፋ የተሞላው ንግግራቸውን ያሰሙት አገሪቱ እቀባዎችን በማቃለሉ ሂደት የመጨረሻውን ምዕራፍ በገባደደችበት ወቅት ነው። አሁን የአገር ውስጥ በረረራዎችና ጉዞዎች ተፈቅደዋል፤ ዓለም አቀፍ ድንበሮቿንም እየከፈተች ነው።

"ይህ ወረርሽኝ በአገራችን ሥር ነቀል መዋቅራዊ ለውጥ ለማምጣት እንድንነሳ እድል ሰጥቶናል፤ አገራችንን በድጋሚ ነድፈን ልንገነባት ይገባል" ብለዋል ጁሴፔ።

ለሕዝባቸው ባደረጉት በዚህ ንግግር ጄሴፔ የግብር እፎይታ ማዕቀፍን ተግባራዊ ለማድረግ ቃል ገብተዋል።

ጁሴፔ በዚህ ተስፋን በሰነቀው ንግግራቸው ማብቂያ ሕዝባቸው በፍጹም እንዳይዘናጋ መክረዋል። በተለይም ማኅበራዊ ርቀትን መጠበቅና ጭምብል ማጥለቅ መዘንጋት የለበትም ብለዋል። እነዚህን ቸል ማለት ዋጋ ያስከፍላል ሲሉ አስምረውበታል።

እንደ ጠቅላይ ሚኒስትር ጁሴፔ ሁሉ የጣሊያኑ ፕሬዝዳንት ሰርጂዮ ማታሬላ ለሕዝባቸው ባደረጉት ንግግር "ቫይረሱ ሄዷል ብላችሁ አትዘናጉ፤ ቫይረሱ አሁንም አለ" ብለዋል።

ጣሊያናዊያን አሁን ምን ማድረግ ተፈቅዶላቸዋል?

ከባለፈው መጋቢት ወዲህ በጣሊያን የአገር ውስጥ በረራዎች እንዲቆሙ ተደርገው ነበር። ጣሊያናዊን ከቤታቸው ወጥተው መንቀሳቀስም አይቸሉም ነበር፤ እጅግ ለመሠረታዊ ጉዳዮች ካልሆነ በስተቀር።

ቱሪዝምም ባለበት እንዲቆም ተደርጎ ነበር። ወደ ጣሊያን እንዲገቡ የተፈቀደላቸው ዜጎችም ለ14 ቀናት ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ ሲገደዱ ነበር።

አሁን ግን ከትናንት ረቡዕ ጀምሮ ወደፈለጉበት ክልል መንቀሳቀስ ይችላሉ። ወደ ክፍለ አገር ብቻም ሳይሆን ወደተፈቀዱ የአውሮፓ ከተሞችም መንቀሳቀስ ተፈቅዷል። ነገር ግን ከአውሮፓ አገሮች ውጪ ወደየትም መሄድ አይችሉም።

ሱቆች፣ ካፊቴሪያዎችና ምግብ ቤቶችም በራቸውን ወለል አድርገው ከፍተዋል። እንደ ኮሎሲየም የመሳሰሉ እውቅ የቱሪስት መዳረሻዎችም ተከፍተዋል።

በሌሎች የአውሮፓ አገሮችስ ምን ተፈቅዷል?

ምንም እንኳ ጣሊያን በሯን ለሌሎች የአውሮፓ አገሮች ብትከፍትም ሁሉም ግን በምላሹ ይህንኑ አላደረጉም። ለምሳሌ ኦስትሪያ ለሁሉም የአውሮፓ አገራት ድንበሯን ከዛሬ ጀምሮ የምትከፍት ሲሆን ለጣሊያን ግን "እምብየው፤ ይቆየኝ" ብላለች።

ስዊትዘርላንድ በበኩሏ ድንበሯን ለጀርመን፣ ለኦስትሪያና ለፈረንሳይ ከሰኔ 15 ወዲህ ለመክፈት ያቀደች ቢሆንም ይህንን እድል ግን ለጣሊያን ነፍጋታለች።

ባለፈው ሳምንት ደግሞ ዴንማርክና ኖርዌይ የእርስ በርስ ድንበሮቻቸውን ከፍተዋል። በዚህ ስምምነት ስዊድንን አግልለዋታል። ስዊድን በወረርሽኙ ዙርያ የተለየ ፍልስፍናን በመከተሏ የጉዳት መጠኗ ከፍ ማለቱ እየተዘገበ ይገኛል።

ሦስቱ የባልቲክ አገራት ማለትም ሉቴኒያ፣ ላቲቪያ እና ኢስቶኒያ እርስ በርሳቸው ብቻ አንዱ ለሌላው ድንበሩን ከፍቷል።

ዩናይትድ ኪንግደምና ስፔንን የመሰሉ አገራት ደግሞ ከውጭ ለሚገቡ የለይቶ ማቆያ ሥርዓትን አበጅተዋል።