በሊቢያ 30 ስደተኞች በአንድ ሕገ ወጥ ደላላ ቤተሰቦች ተገደሉ

ታትሟል

በሊቢያ የአንድ በሕገወጥ መንገድ ስደተኞችን የሚያዘዋውር ደላላን መገደል ለመበቀል በሚል 30 ከሌሎች አገራት ተሰደው የሚገኙ ሰዎች ተገደሉ።

ይህ የጅምላ ግድያ በስደተኞቹ ላይ የተፈጸመው በምዕራብ ሊቢያ አንድ ሕገወጥ ስደተኞች አስተላላፊ ደላላ ተገድሏል በሚል በተወሰደ የበቀል እርምጃ መሆኑ ተዘግቧል።

በተባበሩት መንግሥታት እውቅና ያለው የትሪፖሊ መንግሥት እንዳስታወቀው 30ዎቹ ስደተኞች በአንድ ጊዜ የተገደሉት በአንድ ወቅት አንድ ሕገ ወጥ የስደተኞች አዘዋዋሪ ደላላን ገድላችኋል በሚል በሟች የቅርብ ሰዎች ደም ለመመለስ በሚል ነው።

ይህንን የበቀል እርምጃ የወሰዱት የደላላው ቤተሰቦች ናቸው ተብሏል።

የሟች ስደተኞቹ ዜግነት በዝርዝር ባይገለጽም 26ቱ ባንግላዴሻዊያን ሲሆኑ አራቱ ከአፍሪካ እንደሆኑ ተዘግቧል። ዘገባው ሟቾቹ ከየትኛው የአፍሪካ ክፍል እንደሆኑ አላብራራም።

ከዚህ በፊትም በአብዛኛው ከአፍሪካ አገራት የመጡ በርካታ ስደተኞች ገንዘብ ለማግኘት ሲባል በደላሎችና በታጣቂዎች ተገድለዋል።

በበአሁኑ ጊዜ በሺህዎች የሚቆጠሩ ስደተኞች በአደገኛ የባሕር ላይ ጉዞ በሕገወጥ መንገድ ወደ አውሮፓ ለመሻገር በእርስ በርስ ጦርነት በምትታመሰው ሊቢያ ውስጥ ይገኛሉ።

ስደተኞቹ በሊቢያ ቆይታቸው በሕገ ወጥ የሰው አዘዋዋሪዎችና በታጣቂ ቡድኖች ገንዘብና ንብረታቸው የሚወሰድባቸው ሲሆን በእገታም ከቤተሰቦቻቸው ገንዘብ እንዲያስልኩ ይገደዳሉ።

በተጨማሪም ከኮሎኔል ሞሐመድ ጋዳፊ መንግሥት መውደቅ በኋላ በእርስ በርስ ጦርነት ሳቢያ ስደተኞቹ የሚገኙባቸው የመጠለያ አካባቢዎች የጥቃት ኢላማ ሆነው በርካቶች ተገድለዋል።