ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
ኮሮናቫይረስ፡ በቻይና አሽከርካሪ አልባ ሮቦት ታክሲዎች የወረርሽኙን ስጋት ይቀንሱት ይሆን?
በቻይና በኮሮናቫይረስ የሚያዙ አዳዲስ ሰዎች ቁጥር እየተመዘገበ ባይሆንም የወረርሽኙ ስጋት ግን አሁንም አለ።
ለብዙ ወራት ቤት ተቀምጠው የነበሩ ቻይናውያን ወደቀደመው ህይወታቸው መመለስን ጥያቄን አጭሮባቸዋል። በቀላሉ ያደርጓቸው የነበሩ በህዝብ ትራንስፖርቶች ተሳፍሮ መሄድም ፍራቻን አንግሷል።
ከዚህም ጋር ተያይዞ ያለ አሽከርካሪ አገልግሎት የሚሰጡ 'የሮቦት ታክሲ' ኩባንያዎች ያለውን ፍላጎት ለሟሟላት በርካታ መኪናዎችን ለአገልግሎት ለማሰማራት ዝግጅታቸውን መጨረሳቸውን ከሰሞኑ አስታውቀዋል።
ከነዚህም ውስጥ ፈር ቀዳጅ የሆነው አውቶ ኤክስ በሚቀጥለው ወር ላይ 100 አሽከርካሪ አልባ የሆኑ መኪኖች በሻንጋይ ከተማ አገልግሎት መስጠት እንደሚጀመሩ አስታውቀዋል።
አውቶ ኤክስ ብቻ ሳይሆን ሌሎችም ኩባንያዎች አሽከርካሪ የሌላቸው መኪናዎችን ለማቅረብ በዝግጅት ላይ መሆናቸውን አስታውቀዋል።
"የኮሮናቫይረስ ወረርሸኝ አሽከርካሪ አልባ መኪናዎች ምን ያህል ለማህበረሰባችን አስፈላጊ መሆናቸውን አስታውሶናል" በማለት በድረ-ገፅ ግብይት ስመጥር በሆነው አሊባባ የሚደገፈው የአውቶ ኤክስ ቃለ አቀባይ ተናግረዋል።
አክለውም "ሮቦት ታክሲዎች በራሳቸው መኪናውን ከባክቴሪያም ሆነ ከቫይረስ እንዲያፀዱ ተደርገው የተሰሩ ሲሆን፤ ከአሽከርካሪ ጋር ተያይዞ በሚፈጠሩ ስህተቶች የሚያጋጥሙ አደጋዎችንም እንዲሁም ሞቶችን መቀነስ ይቻላል" ብለዋል
በቻይና ከጉግል ጋር ተመሳሳይ አገልግሎት የሚሰጠው 'ባይዱም' አፖሎ የተባሉ የሮቦት ታክሲዎች ለህዝብ አገልግሎት እንዲሰጡ በሶስት የቻይና ከተሞች ለማሰማራት ጫፍ ደርሻለሁ ብሏል።
የታክሲዎቹ ቁጥር በትክክል ባይገለፅም ኩባንያው ቶዮታ፣ ሆንዳና ፎርድ ከመሳሰሉ የመኪና አምራቾች ጋር በመጣመር አፖሎ የሮቦት ታክሲን ማምረት እንደተቻለ አሳውቋል።
"ወረርሽኙ አሽከርካሪ የሌላቸው መኪኖችን ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ ጨምሮታል። በኛ ኩባንያም ሆነ አጋሮቻችን በዚህ ወረርሽኝ ወቅት የምንጠቀመው እነዚህኑ የሮቦት ታክሲዎችን ነው። በአሁኑ ሰአት ለህዝብ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ባይጀምሩም 104 የሮቦት ታክሲዎች በ17 ከተሞች እቃዎችን በማመላለስ አገልግሎት እየሰጡ ነው" በማለት የባይዱ ቃለ አቀባይ ተናግረዋል።
በመጀመሪያ ወቅት አካባቢ የሮቦት ታክሲዎቹን ደህንነት የሚቆጣጠር አንድ ሰው በመኪናው ውስጥ የሚመደብ ሲሆን፤ ከጥቂት ጊዜያትም በኋላ ሙሉ በሙሉ አሽከርካሪ አልባ እንደሚሆን የአውቶ ኤክስ ቃለ አቀባይ ገልፀዋል።
"የቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት በዚህ ብቻ የሚቆም አይደለም። ገና ለረዥም ጊዜ በመጪዎቹ አመታትም የሚቆም አይሆንም እናም እንደዚህ አይነት ቴክኖሎጂዎች ግዴታም ይሆናሉ" በማለት ተናግረዋል።
መቀመጫውን ጉዋንዡ ያደረገው ዊ ራይድ ከባዩን ታክሲ ጋር በመጣመር አርባ አሽከርካሪ አልባ መኪኖች እየሞከሩ ነው።
ዊ ራይድ ሮቦት ታክሲዎቹ በሚቀጥለው አመት አገልግሎት እንደሚሰጡ አሳውቆ ነገር ግን አሁንም ቢሆን ቴክኖሎጂው ዝግጁ ቢሆንም ሌሎች መጨረስ ያለባቸው ህጋዊ ጣጣዎች እንዳሉ ገልጸዋል።
የሮቦት ታክሲዎች ከህዝብ ትራንስፖርትነት በተጨማሪ የተለያዩ እቃዎችን ለማድረስም በከፍተኛ ሁኔታ ፍላጎት እየጨመረ ነው ተብሏል።
የቻይና መንግሥትም አሽከርካሪ የሌላቸው መኪኖች በከፍተኛ ሁኔታ የሚመረቱበትንም እቅድ ነድፎ በአምስት አመታት ውስጥ ተግባራዊ ይሆናል ብሏል።