ኮሮናቫይረስ፡ በአለም ላይ በኮሮና የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ200 ሺህ አለፈ

ታትሟል

በአለም አቀፍ ደረጃ በኮሮናቫይረስ የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከ200 ሺህ በላይ መሆኑን ጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርስቲ ያወጣው መረጃ ያሳያል።

በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችም ቁጥር ከ2.8 ሚሊዮን በላይ መሆኑንም ይኸው መረጃ ጠቁሟል።

በቫይረሱ ክፉኛ በተመታችው አሜሪካ የሟቾች ቁጥር 50 ሺህ ያለፈ ሲሆን፤ ይህም አሃዝ ከአለም ቀዳሚ አድርጓታል።

የቻይና ሚዲያ ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ የሞተው ግለሰብ በጥር ወር አጋማሽ ሪፖርት ከተደረገበት ጊዜ ጀምሮ፣ ቫይረሱ በተለያዩ ሃገራት ተዛምቶ በ120 አገራትም ውስጥ መኖሩ ተረጋግጧል።

በአምስት አገራት ውስጥ የሟቾች ቁጥር ከ20 ሺህ በላይ የሆነ ሲሆን፤ በተለይም አሜሪካ፣ ስፔንና ጣልያን ከፍተኛ ቁጥር ያለው ዜጎቻቸውን ህይወት አጥተዋል።

በእንግሊዝም የሟቾች ቁጥር እያሻቀበ ሲሆን፣ በትናንትናውም ዕለት በኮሮና የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከሃያ ሺህ መብለጡን የሃገሪቱ የጤና ዘርፍ አስታውቋል።

ይህ ቁጥር የሚያሳየው በሆስፒታሎች ውስጥ ብቻ የሞቱትን መሆኑም ተገልጿል። በቤታቸው እንዲሁም በተለያዩ መጠለያዎች ውስጥ የሞቱ ሰዎች አሃዝም ባለመካተቱ ቁጥሩ ከዚህ በላይ ከፍ ያለ ሊሆን እንደሚችል ይጠበቃል።

በፈረንሳይም የሟቾች ቁጥር 22 ሺህ 614 ሲሆን በሆስፒታሎች ውስጥ የሟቾች ቁጥር መቀነሱን እንዲሁም በፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ የሚገኙ ህመምተኞች ቁጥርም እንዲሁ ለሰባተኛ ቀን መቀነሱን የሃገሪቱ የጤና ኃላፊዎች አሳውቀዋል።

የአለም የጤና ድርጅት ከሰሞኑ እንዳሳወቀው ከኮሮናቫይረስ ያገገሙ ሰዎች እንደገና አይያዙም ማለት እንዳልሆነ ገልጿል።

የድርጅቱ ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም በአውሮፓ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ መሆኑንና በሌሎች አገራት ግን ሊጨምር እንደሚችል አስታውቀዋል።

የቫይረሱን ወረርሽኝ ለመግታት ከፍተኛ ስራ በመስራት ምስጋና በተቸራቸው እንደ ሲንጋፖር ባሉ እስያ ሃገራት ደግሞ ወረርሽኙ በፋብሪካዎች ውስጥ መከሰቱ ተዘግቧል።

የቻይና ባለስልጣናት ባለፉት አስር ቀናት በቫይረሱ የሞተ ሰው እንደሌለ ያሳወቁ ሲሆን በደቡብ ኮሪያም እንዲሁ ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ ሞት ከተከሰተ ቀናት ተቆጥረዋል።