የኮሮናቫይረስ ለሮቦቶች የሥራ ዕድል ይከፍት ይሆን?

ሮቦት ኪቦርድ ሲጫን

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

ታትሟል

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዓለምን እንዲህ ወጥሮ በያዘበት ወቅት በርካታ የዓለማችን ሰራተኞችን ሲያስጨንቅ የነበረው ጉዳይ የተረሳ ይመስላል- የሮቦቶች ወደ ሥራው ዓለም መቀላቀል።

በቅርብም ሆነ ከበርካታ ዓመታት በኋላ ሮቦቶች የሰው ልጆችን ስራ ለቃቅመው እንደሚረከቡ ሲነገር የቆየ ቢሆንም የኮሮናቫይረስ መምጣት ግን ሂደቱን እንዳያፋጥነው ተሰግቷል።

'' ሰዎች በሁሉም እንቅስቃሴያቸው ከሰዎች ጋር ይገናኙ ነበር፤ አሁን ግን ሁሉም በየቤቱ ተሰብስቦ መቀመጡ ሌሎች አማራጮች እንዲፈልጉ ያደርጋል" ይላሉ የዘርፉ ባለሙያ የሆኑት ማርቲን ፎርድ።

እንደ እሳቸው ትንበያም ከሆነ የሰው ልጅ እንደዚህ በቀላሉ ከስራ ውጪ መሆነ ከቻለ ያለምንም ችግር በማንኛውም ሁኔታ መስራት የሚችሉ ሮቦቶች ተፈላጊነት በሚቀጥሉት 10 ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ ይሆናል።

በጣም ትልልቅም ሆነ አነስተኛ የሚባሉ ድርጅቶች በኮሮናቫይረስ ምክንያት ሰራተኞቻቸው ከቤታቸው ሆነው መስራት የማይችሏቸውን ስራዎች በሮቦት ማሰራት ጀምረዋል።

የአሜሪካው ትልቁ የጅምላ ንግድ ድርጅት 'ዎልማርት' ወለሎችን ለማጽዳት የሚውሉ ሮቦቶችን ወደ ስራ አስገብቷል። በደቡብ ኮሪያ የሚገኙ ሮቦቶች ደግሞ የሰዎችን የሰውነት ሙቀት በመለካትና የእጅ ንጽህና መጠበቂያ ሳኒታይዘሮችን በማከፋፈል ተጠምደው ነበር።

አንዳንድ የጤና ባለሙያዎች ማህበራዊ ርቀትን መጠበቅ እስሚቀጥለው ዓመት ድረስ ሊተገበር ይገባል ማለታቸውን ተከትሎ ሮቦቶች ተፈላጊነት በእጅጉ ሊጨምር እንደሚችል ይገመታል።

የሚያፀዱ ሮቦቶች

የፎቶው ባለመብት, UVD-Robots

በዴንማርክ የሚገኘውና የተለያዩ አገልግሎቶችን የሚሰጡ ሮቦቶችን የሚያመርተው 'ዩቪዲ ሮቦትስ' ሆስፒታሎችን የሚያጸዱ ሮቦቶቹ በጣም ተፈላጊ ሆነውለታል። የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ተከትሎም በመቶዎች የሚቆጠሩ ጽዳት የሚሰሩ ሮቦቶችን ቻይና እና አውሮፓ ለሚገኙ ሆስፒታሎች ሽጧል።

ሱፕርማርኬቶችና ምግብ ቤቶችም ቢሆኑ እነዚህን ሮቦቶች መጠቀም ጀምረዋል።

ሮቦቶች በቅርቡ ይረከቡታል ተብሎ የሚጠበቀው ደግሞ የምግብ ኢንዱስትሪውን ነው። የአሜሪካው ፈጣን ምግብ አምራች 'ማክዶናልድስ' ምግብ የሚያበስሉና የሚያቀርቡ ሮቦቶችን በመሞከር ላይ ይገኛል።

ምናልባት አንድን ሮቦት ገዝቶ ወደስራ ለማስገባትና ለማቀናጀት በርከት ያለ ገንዝብ ሊያስፈልግ ይችላል፤ ነገር ግን ሮቦቶቹ አንዴ ወደስራ ከገቡ በኋላ ለበርካታ ዓመታት ያለክፍያና ያለማቋረጥ መስራት ይችላሉ። ይህ ደግሞ ለበርካታ ቀጣሪዎች ተቀዳሚው ምርጫ ያደርገዋል።

ሌላው ቀርቶ ሰዎች እራሳቸው ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በኋላ ብዙ ሰዎች የተሰበሰቡበት አካባቢ መገኘት ምቾት ላይሰጣቸው ይችላል። በዚህም ምክንያት ሮቦቶች የሚያስተናግዱበትና ምግብ የሚያበስሉበትን ምግብ ሊመርጡ ይችላሉ።

አንድ ዓለም አቀፍ አማካሪ ቡድን በሰራው ጥናት መሰረት በፈረንጆቹ 2030 በአሜሪካ ከሚገኙ ስራዎች አንድ ሶስተኛው በሮቦቶች ይያዛል።

ነገር ግን እንደ ኮሮና ያሉ ወረርሽኞች ከዚህም በቀረበ ጊዜ ሮቦቶችን እንደምንመለከታቸው ማሳያ ናቸው።

ኮሮና