በኮሮናቫይረስ ምክንያት ስጋት ውስጥ የወደቀው የጃፓን የጤና ሥርዓት

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በጃፓን ውስጥ እየታየ ያለው ቁጥራቸው እየጨመረ የመጣው በኮሮናቫይረስ በሚያዙ ሰዎች ምክንያት የአገሪቱ የጤና ሥርዓት ሊንኮታኮት እንደሚችል ሃኪሞች አስጠነቀቁ።
የድንገተኛ ክፍሎች በኮሮናቫይረስ ህሙማን በመጣበባቸው ምክንያት ከባድ የጤና ችግር ያለባቸውን ሌሎች ህሙማንን ለማከም እንዳልቻሉ ባለስልጣናት ተናግረዋል።
አንድ የኮሮናቫይረስ በሽታ ምልክቶችን የሚያሳይ በሽተኛ ይዞ የነበረ አምቡላንስ በመጨረሻ የሚቀበለው እስኪያገኝ ድረስ ቁጥራቸው በርካታ ወደ ሆኑ ሆስፒታሎች ሄዶ እንደመለሱት ተነግሯል።
በመጀመሪያ ላይ የቫይረሱን ስርጭት እንደተቆጣጠረችው ሲነገርላት የቆየችው ጃፓን ዛሬ ቅዳሜ በወጣ አሃዝ መሰረት በበሽታው መያዛቸው የተረጋገጡ ሰዎች ቁጥር ከ10 ሺህ አልፏል።
ጃፓን ውስጥ እስካሁን ድረስ ከ200 ሰዎች በላይ በኮቪድ-19 ወረርሸዕኝ ምክንያት የሞቱ ሲሆን በበሽታው ክፉኛ የተጠቃችው ደግሞ ዋና ከተማዋ ቶኪዮ እነደሆነች ተነግሯል።
በከተማዋ ውስጥ በሌሎች መደበኛ ሥራዎች ላይ ተመድበው ይሰሩ የነበሩ አጠቃላይ የቀዶ ህክምና ዶክተሮች በአገሪቱ የጤና ሥርዓት ላይ የተፈጠረውን ጫና ለማቅለል ሲሉ በበሽታው በተጠረጠሩ ሰዎች ላይ በሚደረገው የምርመራ ሥራ ላይ ተሰማርተዋል።
የሐኪሞቹ ማኅበር ምክትል ለሮይተርስ እንደገለጹት አባሎቻቸው እያደረጉ ያለው "የአገሪቱ የህክምና ሥርዓትን በሚፈጠርበት ጫና ከመንኮታኮት ለመከላከል ነው" ብለዋል።
የጃፓን መንግሥትም አሽከርካሪዎች በቀጥታ መጥተው ምርመራ የሚያገኙበትን መንገድ በማመቻቸት ያለውን መመርምር አቅም ከፍ ለማድረግ እየሰራ መሆኑ ተነግሯል።
በቅርብ ሳምንታት ውስጥ ጃፓን ሌሎች አገራት ውስጥ ከተካሄደው የበሽታው ምርመራ ያነሰ ቁጥር ያለውን ብቻ ያደረገች ሲሆን፤ ይህም የበሽታውን መስፋፋት ለመከታተል አስቸጋሪ እንዳደረገው ባለሙያዎች አመልክተዋል።
ኦክስፎርድ ዩኒቨርስቲ ያወጣው መረጃ እንደሚጠቁመው ጃፓን ባለፈው ወር ያደረገችው ምርመራ ደቡብ ኮሮያ ካደረገችው 16 በመቶውን ብቻ ነው።
ደቡብ ኮሪያ ሰፊ የኮሮናቫይረስ ምርመራን በማድረግ በሽታውን በቁጥጥር ስር ማዋል የቻለች ሲሆን፤ በወቅቱ የጃፓን መንግሥት መጠነ ሰፊ ምርመራ ማካሄድ "የሃብት ብክነት ነው" ሲሉ አጣጥለውት ነበረ።














