ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የኮሮናቫይረስ ስርጭትን በመቆጣጠር ረገድ አፍሪካ ከእስያ አገራት ምን ትማራለች?
በአውሮፓና በአሜሪካ በኮሮናቫይረስ የሚያዙና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው። ይህንንም ተከትሎ አገራት የበረራ እገዳ፣ የትምህርት ቤት መዘጋትና የእንቅስቃሴ ገደብ አስተላልፈዋል።
ከበርካታ ሳምንታት በፊት ግን ወረርሽኙ በርካታ የእስያ አገራትን አጥቅቶ ነበር። አንዳንዶቹ አገራት በቀላሉ ቫይረሱን በቁጥጥር ሥር ማዋል በመቻላቸው ተደንቀዋል።
ከእነዚህም አገራት መካከል ሲንጋፖር፣ ሆንግ ኮንግ እና ታይዋን የሚገኙበት ሲሆን በአንጻራዊነት ለቻይና ካላቸው ቅርበት አንጻር ሲታይ በእነዚህ አገራት በቫይረሱ የተያዙና የሞቱ ሰዎች ቁጥር በጣም ትንሽ ነው።
እነዚህ አገራት ምን የተለየ ነገር ቢያከናውኑ ነው የቫይረሱን ስርጭት በቀላሉ መቆጣጠር የቻሉት? አፍሪካ ከእነዚህ አገራትስ የምትማረው ይኖር ይሆን?
ትምህርት አንድ፡ ወረርሽኙን የምር መውሰድና በፍጥነት ወደተግባር መግባት
የጤና ባለሙያዎች የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር በአንድ ድምጽ የሚስማሙበት ነገር አለ። ይኸውም በሰፊው መመርመር፣ በቫይረሱ የተያዙትን ለይቶ ማቆያ ማስገባት፣ እና ማህበራዊ ርቀትን መጠበቅ የሚሉት ናቸው
እነዚህ ተግባራት በምዕራቡ አለም በተለያየ መጠን ተግባራዊ እየተደረጉ ቢሆንም አገራቱ ግን በፍጥነት ወደተግባር ባለመግባታቸው ይመሳሰላሉ።
ለዚህም ዩናይትድ ኪንግደምንና አሜሪካን የሚጠቀሱ ሲሆን በቻይና ወረርሽኙ ከተከሰተ ሁለት ድፍን ወራት አልፎ ምንም አይነት ዝግጅት አላደረጉም ነበር ተብሏል። ሁለቱ አገራት፣ ቻይና ሩቅ መስላቸውና ቫይረሱን ሩቅ አድርገው ገምተው መዘናጋታቸው ዛሬ ለገቡበት አጣብቂኝ ዳርጓቸዋል።
ቻይና የመጀመሪያው ስለበሽታው ለዓለም ጤና ድርጅት ያስታወቀችው ከፈረንጆቹ አዲስ አመት አንድ ቀን ቀደም ብሎ ነበር። በዚህ ወቅት በሽታው ከሰው ወደ ሰው ስለመተላለፉ ምንም ማረጋገጫ አልተሰጠም አልተሰማምም። ነገር ግን በሶስት ቀናት ውስጥ ሲንጋፖር፣ ታይዋን፣ ሆንክ ኮንግ በድንበሮቻቸው ቫይረሱን ለመለየት የሚያስችላቸውን ምርመራ ጀመሩ። ታይዋን በአውሮፕላን ከዉሃን ወደ አገሯ የሚመጡ መንገደኞችን ከአውሮፕላን ሳይወርዱ መመርመር ጀምራ ነበር።
ቀናት በጨመሩ ቁጥር ተመራማሪዎች ሰዎች የቫይረሱን ምልክት ሳያሳዩ ረዥም ጊዜ ሊቆዩ እንደሚችሉ ደረሱበት። ያም ቢሆን እነዚህ አገራት ወረርሽኙን በአጭር ቀጩት።
ትምህርት ሁለት፡ ምርመራውን በርካታ ሰዎች ላይ ማካሄድና ተደራሽ ማድረግ
በደቡብ ኮሪያ ቫይረሱ ያለባቸው ሰዎች በብዛት መገኘት የጀመሩት በአንድ ጊዜ ነበር። ነገር ግን ወዲያውኑ ደቡብ ኮሪያ ምርመራ ማድረግ ጀምራለች። እስካሁን ድረስም ከ290ሺህ በላይ ሰዎችን መመርመር ችላለች። በየቀኑ በነፃ 10ሺህ ሰዎችን ትመረምራለች።
ይህ የደቡብ ኮሪያ ተግባር ከተመራማሪዎችና ከባለስልጣናት አድናቆትን ተችሮታል።
በተነፃፃሪ በአሜሪካ ምርመራው እጅጉን ዘግይቷል። መጀመሪያ አካባቢ የመመርመሪያ ኪቶቹ ስህተት ነበረባቸው። በርካታ ሰዎች ለመመርመር ተቸግረው ነበር። ምንም እንኳ ነፃ ምርመራ በሕግ የተደነገገ ቢሆንም ለመመርመር ግን ውድ ዋጋ ይጠየቅ ነበር።
በዩናይትድ ኪንግደምም ቢሆን ሆስፒታል ታመው የመጡት ብቻ ምርመራ ይደረግላቸው ነበር። መለስተኛ ምልክት ያሳዩ የነበሩ ሕሙማን ምርመራ ለማግኘት ፈተና ሆኖባቸው ቆይቷል።
በርግጥ በአንዳንድ አገራት የመመርመሪያ ኪት አልተሟላም። ቢሆንም ግን በርካታ ሰዎችን መመርመር ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅትም ሆነ የዘርፉ ባለሙያዎች ያሰምሩበታል።
አክለውም ወደ ሆስፒታል የሚመጡትን ብቻ ሳይሆን ምልክቱ የሚታይባቸውንና ለሌሎች ሊያሰራጩ የሚችሉ ሰዎችን መመርመር እጅግ አስፈላጊ ነው ብለዋል።
ትምህርት ሦስት፡ ንክኪዎችን መፈለግና ለይቶ ማቆያ ማስገባት
መመርመር ብቻ በቂ አይደለም ይላሉ የጤና ባለሙያዎች። ተመርምረው ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ከእነማን ጋር ንክኪ እንደነበረባቸው መለየት ወሳኝ ነው።
በሲንጋፖር የወንጀል ምርመራ ባለሙያዎች የመንገድ ላይ ደህንነት ካሜራን በመጠቀም ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች ከማን ጋር ግንኙነት ወይንም ንክኪ እንደነበረባቸው በመለየት ስራ ውስጥ ተሳትፈው 6ሺህ ሰዎችን አግኝተዋል።
ከዚያም ምርመራ እንዲያደርጉ፣ ውጤታቸው ነፃ እስኪሆን ድረስ ራሳቸውን ነጥለው እንዲቀመጡ አድርገዋል።
በሆንክኮንግ ንክኪዎችን የመለየት ተግባሩ ግለሰቡ የበሽታውን ምልክት ማሳየት ሳይጀምር ሁለት ቀን ቀደም ብሎ ነው የሚካሄደው።
በሆንክ ኮንግ ከሌላ አገራት የሚመጡ መንገደኞች እግራቸው ላይ እንቅስቃሴያቸውን የሚያሳይ እግረ ሙቅ እንዲያደርጉ ሲደረግ፣ በሲንጋፖር ደግሞ ራሳቸውን ነጥለው በቤት የሚቀመጡ ሰዎች በቀን ለበርካታ ጊዜያት ይደወልላቸው ነበር፣ የት እንዳሉ የሚያሳይም ፎቶ ተነስተው እንዲልኩም ይደረግ ነበር።
በሲንጋፖር ቤት ራሱን ነጥሎ መቀመጥ ሲኖርበት ያላደረገ ጠበቅ ያለ ቅጣት ይጠብቀዋል።
በምዕራቡ ዓለም ግን ከግለሰቦች ነፃነትና ከቆዳ ስፋታቸው አንጻር እንዲህ አይነት እርምጃን ለመተግበር አስቸጋሪ ነው።
ትምህርት አራት፡ አስቀድሞ ማህበራዊ ርቀትን መጠበቅን ተግባራዊ ማድረግ
ማህበራዊ ርቀትን መጠበቅ ወረርሽኙን ለመቆጣጠር ምርጡ መላ ተድረጎ ይወሰዳል። ነገር ግን ተግባራዊ ለማድረግ በዘገዩ ቁጥር ተፈፃሚነቱን ለማረጋገጥ እጅጉን መልፋት ይጠይቃል።
የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ መነሻ ናት ተብላ የምትጠራዋ የቻይናዋ ዉሃን ከተማ የእንቅስቃሴ ገደብ ከመጣሏ በፊት አምስት ሚሊዮን ሰዎች ከተማዋን ለቅቀው ወጥተው ነበር።
ይህም መንግሥትን በሰው ልጅ ታሪክ ውስጥ ትልቁ የተባለውን የእንቅስቃሴ ገደብ ለመጣል አስገድዶታል።
ጣሊያንም ሆኑ ስፔን ከተሞቻቸውን ከእንቅስቃሴ በማቀብ ዜጎቻቸው ከቤታቸው ውልፊት እንዳይሉ ያዘዙት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር በሺዎች ሲቆጠር ነው።
በተቃራኒው ግን ሲንጋፖር ትምህርት ቤቶች አልተዘጉም ነበር። በርግጥ ሕዝባዊ ስብሰባዎች ተከልክለው ነበር። ሆንግ ኮንግ ትምህርት ቤቶችን የዘጋች ሲሆን ሠራተኞችም ከቤታቸው እንዲሰሩ ብታደርግም ምግብ ቤቶችና መጠጥ ቤቶች ክፍት ነበሩ።
ይህ ለምን ሆነ ብለው የሚጠይቁ ቢኖሩ፣ ባለሙያዎች መልሳቸው ማህበራዊ ርቀትን መጠበቅን በፍጥነት ተግባራዊ ማድረጋቸው ለዚህ ረድቷቸዋል በማለት ምላሻቸውን ይሰጣሉ።
አሁን እንቅስቀሴ የገደቡ አገራት፣ ትምህርት ቤት፣ ሕዝባዊ ስብሰባ የከለከሉ መንግሥታት ቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከጨመረ በኋላ በመሆኑ ከባድ እርምጃ የሚሉትን እንዲወስዱ አስገድዷቸዋል።
ማህበራዊ ርቀትን መጠበቅ በመንግሥታት ውሳኔ ላይ የተመሰረተ ቢሆንም ዜጎች ትዕዛዙን ተቀብለው ተግባራዊ ማድረግ አለማድረጋቸውም አስተዋጽኦው የጎላ ያደርገዋል። ለዚህም ነው የሚተላለፉ መልዕክቶችና የግለሰቦች አመለካከት ወሳኝ የሚሆኑት።
ትምሀርት አምስት፡ ሕዝቡ በቂ መረጃ እንዲኖረው እንዲሁም ከመንግሥት ጎን እንዲሰለፍ ማድረግ
እንደ ኮሮናቫይረስ ያሉ ወረርሽኞችን ለመከላከል እና በቁጥጥር ሥር ለማዋል ሕዝብን ከጎን ማሰለፍ ካልተቻለ የመንግሥት እርምጃና ፖሊሲ ከንቱ ነው የሚሆነው።
ስለዚህ ይላሉ የጤና ባለሙያዎች መንግሥት ፖሊሲዎች በሳይንሳዊ ማስረጃዎች ላይ የተደገፉ መሆናቸውን ማሳየት ይጠበቅበታል።
ለዚህም አስረጅ አድርገው የሚያቀርቧት ቻይናን ነው። ቻይና በዉሃን የተፈጠረውን ለመሸፋፈን ሞክራ ነበር።
ስለወረርሽኙ ለመናገር የሞከሩ የሕክምና ባለሙያዎችንም ቀጥታለች።
በዚህ መካከል በዉሃን ትልልቅ ስብሰባዎች ተካሂደዋል። በኋላም ቫይረሱን ለመቆጣጠር ከተማዋን በሙሉ ከእንቅስቃሴ ውጪ ወደማድረግና የሕክማና ተቋማትን አቅም በፍጥነት ወደማሳደግ በመግባቷ ወረርሽኙን ልትቆጣጠር ችላለች።
ይህ ሁሉ የሆነው ግን መጀመሪያ ላይ ለቫይረሱ የሰጠችው ምላሽ ዘገምተኛ በመሆኑ ነው ይላሉ።
በአሜሪካም ቢሆን ስለኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ፕሬዝደንት ትራምፕ ከሕክምና ባለሙያዎች ጋር በሃሳብ ይለያዩ ነበር።
እንደ ሆንክ ኮንግ ባሉ የእስያ አገራት ግን ማህበረሰቡን ስለወረርሽኙ ለማንቃት ቴክኖሎጂዎችን ይጠቀሙ ነበር።
ደቡብ ኮሪያ ዜጎች በአካባቢያቸው በቫይረሱ የተያዘ መኖር አለመኖሩን በሞባይል አጭር መልዕክት ታሳውቅ ነበር።
በሲንጋፖርም ቢሆን መረጃዎች በፍጥነት ይደርሱ ነበር።
ትምህርት ስድስት፡ የግለሰቦች አመለካከት ወሳኝ ነው
እሲያውያን ከመንግሥታቸው የሚመጣን ውሳኔና ትዕዛዝ ተግባራዊ ለማድረግ አያመነቱም። በሆንክ ኮንግ ዜጎች መንግሥታቸው ላይ ተቃውሞ ቢያሰሙም በአገራቸው ግን ይኮራሉ። እናም ሁሉም ወረርሽኙን እንደ ብሔራዊ አደጋ ቆጥረውት ነበር ተብሏል።
ሌላው ሆንግ ኮንጋውያን በግለሰብ ደረጃ ሃላፊነት እንዳለባቸው የሚያምኑ ዜጎች መሆናቸውን የሚናገሩ ባለሙያዎች አሉ። ለዚህ ደግሞ ምክንያታቸው ከዚህ ቀደም የሳርስ ወረርሽኝ በከፍተኛ ሁኔታ የጎዳቸው መሆኑ አንዱ ነው።
በዓለም ላይ እጅን በተደገጋጋሚ በሳሙናና በውሃ መታጠብ የሚጠይቁ ወረርሽኞች ተከስተው ያውቃሉ የሚሉት ባለሙያዎቹ በቅርብ ጊዜ የተከሰተው ኢቦላን በመጥቀስ ትልቁ ፈተና የነበረው ዜጎች እጃቸውን በተደጋጋሚ እንዲታጠቡ ማድረግ እንደነበር ያስታውሳሉ።
ግለሰቦች የሚወስኑት ውሳኔ ለራሳቸው ብቻ ሳይሆን አብረዋቸው የሚኖሩና ለሌሎችም የሞት የሽረት ጉዳይ ይሆናል ሲል የዓለም ጤና ድርጀት ማስጠንቀቁ ይታወሳል።
ይህ ሁሉ እርምጃ ተወስዶም ቢሆን ግን የዓለም ዜጎች ልባቸው እርፍ የሚለው ክትባት ሲገኝ ብቻ ይመስላል። ለእርሱ ደግሞ 18 ወራት መጠበቅ ግድ ነው።
ለረዥም ጊዜ ከተሞችን እንቅስቀሴ አልባ አድርጎ መቀመጥ ዜጎች እንዲሰላቹ ማድረግ ብቻ ሳይሆን የአገራትንም ምጣኔ ሀብት ያሽመደምዳል።
ስለዚህ ከእስያ አገራት በመማር የባህሪ ለውጥ ማምጣትና በሕክምና ባለሙያዎችና በዓለምጤና ድርጅት የሚሰጡ ምክሮችን ተግባራዊ ማድረግ ራስን ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል ወሳኝ ነው።