በኮሮናቫይረስ ምክንያት ስፔንና ፈረንሳይ በዜጎቻቸው ላይ ጠንከር ያለ እገዳ አስተላለፉ.

ታትሟል

ሁለቱ የአውሮፓ ኅብረት ኃያላን አገራት ስፔንና ፈረንሳይ፤ ጣሊያንን ተከትለው በዜጎቻቸው ላይ ጠንካራ የሚባል እገዳን ጥለዋል።

በስፔን ሰዎች ምግብና መድሃኒት ለመግዛት ወይም ደግም ወደ ሥራ ቦታ ለመሄድ ካልሆነ በስተቀር ከቤት እንዳይወጡ ተከልክለዋል። 191 ዜጎቿ በበበሽታው ምክንያት የሞቱባት ስፔን ከጣሊያን በመቀጠል በቫይረሱ ክፉኛ የተጠቃች አውሮፓዊት አገር ነች።

91 ዜጎቿ በኮሮናቫይረስ የሞቱባት ሌላኛዋ አውሮፓዊት አገር ፈረንሳይ ደግሞ ካፌዎችን፣ ሬስቶራንቶችን፣ ሲኒማዎችንና በርካታ ሱቆችን ዘጋግታለች።

ከሁሉም የአውሮፓ አገራት በላቀ መልኩ 1440 ሰዎችን በኮሮናቫይረስ የተነጠቀችው ጣሊያን፤ ከባለፈው ሰኞ ጀምራ ዜጎቿ ከቤት እንዳይወጡ አድርጋለች።

በአሁኑ ወቅት ከየትኛውም አካባቢ በላቀ መልኩ አውሮፓ የወረርሽኙ ሁነኛ የመስፋፋፊያ ቦታ መሆኗን የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።

የዓለም ጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም፤ አገራት የሕዝብ መሰባሰብንና እንቅስቃሴን ለመግታት ጠንካራ ርምጃዎችን እንዲወስዱ ጠይቀዋል።

አጠቃላይ ዓለም አቀፋዊ ያለው መረጃ፡

  • አውስትራሊያ ከዛሬ ጀምሮ ማንኛውም ወደ ግዛቷ የሚገባ ሰው ራሱን ለ14 ቀናት ለይቶ እንዲያቆይ አዛለች። ኒውዚላንድም ቀደም ሲል ተመሳሳይ ርምጃ ወስዳለች።
  • የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ከኮሮናቫይረስ ነጻ መሆናቸው በምርመራ ተረጋግጧል። ባለፈው ሳምንት አንድ ዝግጅት ላይ አብረዋቸው የተገኙ ሰዎች ቫይረሱ የተገኘባቸው መሆኑን ተከትሎ ነው ምርመራ ያደረጉት።
  • አየርላንድና ታላቋ ብሪታኒያን ጨምሮ የአውሮፓ ኅብረት የኮሮናቫይረስ እገዳን ከመጪው ማክሰኞ ጀምረው ሊተገብሩ ነው።
  • ታላቋ ብሪታኒያ በ24 ሰዓታት ውስጥ በቫይረሱ የሞቱ ሰዎች ቁጥር በእጥፍ በመጨመሩ 21 ደርሷል። ይህንንም ተከትሎ ከ200 በላይ የሚሆኑ ሳይንቲስቶች ጠንካራ እርምጃ እንዲወሰድ ደብዳቤ ጽፈዋል።
  • ታላቋ ብሪታኒያ ወሳኝ ጉዞዎች ካልሆኑ በስተቀር ወደ ስፔን የሚደረገውን ማንኛውንም ጉዞ እንድታቋርጥ ተነግሯታል።
  • ካናዳ በውጭ የሚኖሩ ዜጎቿ ወደ አገራቸው እንዲመለሱ ጥሪ አቅርባለች።
  • ቺሊ በመርከብ ተጉዘው የመጡ 1300 ዜጎቿን በለይቶ ማቆያ አስቀምጣለች።
  • በእስራኤል ከዛሬ ጀምሮ የንግድ ተቋማት በከፊል ይዘጋሉ ተብሏል።
  • በቻይና ከሌላ አገር ከሚመጡ ዜጎች መካከል የሚገኘው የቫይረሱ ተጠቂዎች አሃዝ በአገር ውስጥ ካለው አዲስ የተጠቂዎች ቁጥር አንጻር ለመጀመሪያ ጊዜ የላቀ ሆኖ ተገኝቷል።
  • ደቡብ ኮሪያ 76 አዲስ በበሽታው የተያዙ ሰዎችን እንዳገኘች ይፋ ስታደርግ ይህም አንድ ወር በሚጠጋ ጊዜ ውስጥ ከአንድ መቶ በታች ተጠቂዎችን ሪፖርት ስታደርግ የመጀመሪያዋ ነው።