የኤምፓየሩ ተዋናይ ጀሲ ስሞሌት በአዳዲስ ክሶች ፍርድ ቤት ሊቀርብ ነው

የፎቶው ባለመብት, EPA
በኤምፓየር ተከታታይ የቴሌቪዥን ፊልም የሚታወቀው አሜሪካዊው ተዋናይ ጀሲ ስሞሌት ለፖሊስ ሐሰተኛ ወንጀል ሪፖርት በማድረግ ስድስት አዳዳዲስ ክሶች እንደሚቀርቡበት የኤሎኖይስ ልዩ አቃቤ ህግ አስታወቀ።
ተዋናዩ የዘረኝነት እንዲሁም የተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪ ጥቃት በባለፈው ዓመት በቺካጎ እንደደረሰበት አስታውቆ ነበር።
ባለስልጣናቱ በበኩላቸው ምንም አይነት ጥቃት እንዳልደረሰበትና ታዋቂነቱን ለመጨመር እንዳቀነባበረው ቢናገሩም ተዋናዩ ግን የዘረኝነት ጥቃት ደርሶብኛል በማለት ይከራከራል።
ጀሲ ስሞሌት ያልተገባ ባሕርይ በሚል ስድስት አዲስ ክሶች እንደሚጠብቁት ልዩ አቃቤ ህግ ዳን ዌብ በመግለጫቸው አሳውቀዋል።
የተከሰተው ምንድን ነው?
ባለፈው ዓመት ጥር ላይ ጀሲ ስሞሌት ዘረኝነት ላይ ያተኮረና በተመሳሳይ ፆታ አፍቃሪነቱ ጭምብል ባጠለቁ ሁለት ግለሰቦች ጥቃት እንደደረሰበት ለቺካጎ ፖሊስ ሪፖርት ማድረጉን ተከትሎ ምርመራ ተጀመረ።
ፖሊሶች ሪፖርት በተደረገላቸው መሰረት ፊቱ ላይ በቡጢ መነረት፣ የማይታወቅ ኬሚካል እንደተረጨበትና አንገቱም በገመድ መታነቁን ነው።
ተዋናዩ ለፖሊስ እንደተናገረው በትራምፕና በደጋፊዎቻቸው በተደጋጋሚ የሚናገሩትን "አሜሪካን ታላቅ እናደርጋታለን" የሚለውን መፈክር ሲደጋግሙ ነበር ብሏል።
ታዋቂ ሰዎች እንደ ቫዮላ ዴቪስ፣ ጃኔል ሞኔ፣ ቲ አይ እንዲሁም የኤምፓየር ተዋናዮች ዘረኝነትን በመጠየፍ እንዲሁም ለተዋናዮቹ ያላቸውን ድጋፍ በትዊተር ገፃቸው አስፍረው ነበር።
ጀሲ እንዴት ሊታሰር በቃ?
ያልተጠበቀው ሆነና ጀሲ ስሞሌት ራሱ ለእስር ተዳረገ።
ሁለት ወንድማቾች ጥቃቱን እንዲያቀነባብሩ ገንዘብ ከፍለሃቸዋል በሚል ነው ለእስር የተዳረገው፤ በደሞዙ ስላልተደሰተ ታዋቂነቱን ለመጨመር ያደረገው ነው ተብሎ ነበር።
ነገር ግን ፍርድ ቤቱ ክሶቹን በሙሉ ውድቅ ካደረጋቸው በኋላ በነፃ አሰናብቶታል።
በፍርድ ቤቱ ውሳኔ ግን የቺካጎ ፖሊስም ሆነ ከንቲባው ደስተኛ አልነበሩም፤ እንዴት በነፃ ይሰናበታልም በሚል ተችተዋል።
ከዚያ በኋላ ጉዳዩን በጥልቀት እንዲመረምር ልዩ አቃቤ ህግ የተመደበ ሲሆን ለቺካጎ ፖሊስ የጥላቻ ወንጀል ደርሶብኛል በሚል ሐሰተኛ ምስክርነት ሰጥቷልም በሚል እንደገና ፍርድ ቤት ሊያቀርበው ነው።
ተዋናዩ ከአስራ ሁለት ቀናት በኋላ ፍርድ ቤት የሚቀርብ ሲሆን፤ የከተማው አስተዳደር በበኩሉ ሠራተኞቼ ይህንን ጉዳይ በመመርመር አላስፈላጊ ጊዜ በማባከናቸው 130 ሺህ ዶላር ይከፈለኝ ያለ ሲሆን ጀሲ ስሞሌትም በአስተዳደሩ ላይ ክስ መስርቷል።












