ኡጋንዳ፡ መብረቅ አራት ብርቅዬ የተራራ ገመሬዎችን ገደለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በኡጋንዳ አንዲት ነፍሰ ጡር ገመሬን ጨምሮ አራት ገመሬዎች በመብረቅ መገደላቸውን የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣናት ቡድን አስታውቀዋል።
የሶስት ትልልቅ ገመሬዎችና አንድ ትንሽ ገመሬ አስከሬን በማጊህንጋ ብሄራዎ ፓርክ የተገኘ ሲሆን፤ ሰውነታቸውም ላይ የመጠባበስና የመቃጠል ምልክቶች ታይተዋል ተብሏል።
ግሬተር ቪሩንጋ ትራንስባውንደሪ ኮላቦሬሽን የተባለ ድርጅት ለዝርያው ትልቅ ኪሳራ ነው ብሏል።
የተራራ ገመሬዎች ተብለው የሚጠሩት እነዚህ ገመሬዎች ቁጥራቸው አንድ ሺ ብቻ ነው።
ዝርያው በኮንጎ፣ ሩዋንዳና ኡጋንዳ በተከለሉ ቦታዎች ይገኛሉ።
ሟቾቹ አራት ገመሬዎች ሂርዋ ተብሎ የሚጠራ የቤተሰብ አባላት ስብስብ፤ ሲሆን አስራ ሰባት አባላት እንዳሉትም ባለስልጣናቱ አስታውቀዋል።
የሂርዋ ቤተሰብ 13 አባላት በጤንነት ላይ እንደሚገኙና በሰላም እንደሚገኙም ተዘግቧል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የሂርዋ ቤተሰብ አባላት የሩዋንዳን ድንበር ተሻግረው ወደ ኡጋንዳ የገቡት ባለፈው አመት ሲሆን በማጊንጋ ብሔራዊ ፓርክም መኖሪያቸውን አድርገዋል።
ማጊንጋ የተራራ ሰንሰለት ኡጋንዳ፣ ሩዋንዳንና ኮንጎን ያገናኛል።
ከአስከሬናቸው ናሙና ተወስዶ ለበለጠ ምርመራ የተላከ ሲሆን በሶስት ሳምንት ውስጥም የአሟሟታቸው ዝርዝር ሁኔታ ይፋ ይደረጋል ተብሏል።
ባለፈው አመት ነው የተራራ ገመሬ ሊጠፉ ከተቃረቡ ዝርያዎች ዝርዝር ውስጥ የወጣው፤ ከዚያም በኋላ አደኖችን በመቆጣጠርና ክትትል በማድረግ ቁጥራቸውን ከፍ በማድረግ ከፍተኛ ውጤትም ማምጣት እንደተቻለም ተነግሯል።












