የኡጋንዳው ፕሬዝደንት ሙሴቬኒ 'አትክልት በልቼ' 30 ኪሎ ቀንሻለሁ ይላሉ

ታትሟል

የኡጋንዳው ፕሬዝደንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ካሳቫ፣ 'አይሪሽ' ድንችና የሃገሬን አትክልት በመብላቴ 30 ኪሎ ግራም ቀንሻለሁ ሲሉ ለቢቢሲ ተናገሩ።

"እኔ ሁሌም አቋሜ የተስተካከለ ሰው ነኝ። ነገር ግን ዶክተሮቼ አመጋገቤ ትክክል እንዳልሆነ ሲነግሩኝ አስተካክዬ ይኸው ሸንቀጥ ብያለሁ።" ብለዋል።

የ75 ዓመቱ ሙሴቬኒ ሳያስቡት ክብደታቸው 106 ኪሎ ግራም ገብቶ እንደነበር ይናገራሉ። ማሕበራዊ ድረ ገፆች ላይ ሰዎች ደክሟቸዋል ሲሉ የሰጡትን አስተያየትም ውድቅ አድርገዋል።

ሙሴቬኒ ከቁም ነገር ሳይቆጥሩት ኖሮ ሰውነታቸው ውስጥ ብዙ ስብ ተከማችቶ እንደነበረ፤ አሁን ግን የስብ ጉዳት ገብቷቸው ክብደታቸውን እንደቀነሱ ነው የሚያስረዱት።

ፕሬዝደንቱ አሁን ክብደታቸው 76 መሆኑን ከቁመታቸው [170 ሴንቲ ሜትር] ጋር አብሮ የሚሄድ እንደሆነ ይናገራሉ። ሙሴቬኒ በምን ያህል ጊዜ ይህን ያህል ክብደት እንደቀነሱ ግልፅ አላደረጉም።

"ካሳቫ ነው የምመገበው። እኔ የናንተ አውሮፓውያንን ምግብ አልበላም፤ የእስያ ምግብም አልበላም። የራሳችንን ምግብ ነው የምወደው። ካሳቫ፣ ሙዝ፣ ጥራጥሬና አትክልት ነው የምመገበው።"

"ንጋት ላይ ትንሽ ነገር እመገባለሁ። ምሳ አልበላም። ውሃ እጠጣለሁ። አሊያም ስኳር የሌለው ቡና እጠጣለሁ። ምክንያቱም ስኳር ጥሩ አይደለም - በጣም መጥፎ ነው። ከዚያ ምሽት 1፡00 አካባቢ ሁለት 'አይሪሽ' ድንች እበላለሁ። የአየርላንድ ድንች በውስጡ ትንሽ ቅባት ነው ያለው። ከዚያ በርካታ አትልክት በመብላት ሆዴን እደልለዋለሁ።"

ሙሴቬኒ ምን ያህል ምግብ እንደሚመገቡ በግልፅ ይፋ ያደረጉት ነገር የለም። ቢሆንም ስኳርን ማስወገዳቸው ትልቅ ለውጥ ሊያመጣ ይችላል ይላሉ ባለሙያዎች።

የቢቢሲ ጤና ዘጋቢዋ ፊሊፓ ሙሴቬኒ ምሳ እየዘለሉ ነው ማለት ምግብ ቀንሰዋል ማለት ነው፤ በዚያ አትልክት መመገባቸው በጣም ጤናም ነው ትላለች። ካሳቫ እና ድንች በውስጣቸው ብዙ ሙቀት ሰጭ ንጥረ-ነገሮች አሉ። ምንም እንኳን ድንችና ካሳቫ ክብደት ይቀንሳሉ ማለት ባይቻልም።

በፈረንጆቹ 2015 ኦባማ ኢትዮጵያን በጎበኙ ጊዜ ሙሴቬኒን አግኝተው 'ወጣት ትመስላለህ' እንዳሏቸው የሚያወሱት ፕሬዝደንቱ፤ "የኡጋንዳ ምግብ ስለምበላ ነው ብዬ ሳልነግረው ረሳሁት» ይላሉ።

ሙሴቬኒ ኡጋንዳውያን የአውⶂፓውያንን ምግብ ወዲያ ብለው የራሳቸውን ምግብ እንዲመገቡ መክረዋል።

ለ34 ዓመታት ኡጋንዳን የመሩት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ለስድስተኛ ጊዜ ለመወዳደር በዝግጅት ላይ ናቸው።