ፕሬዝዳንት ሙሴቬኒ ለትራምፕ ያላቸውን ፍቅር ገለፁ

ታትሟል

ስለ ስደተኞች ጉዳይ በተደረገ ስብሰባ ላይ ትራምፕ የአፍሪካ አገራትን በጅምላ "ቆሻሻ" ማለታቸውን ተከትሎ የአፍሪካ ህብረት ለእዚህ ዘረኛ ንግግራቸው ይቅርታ ይጠይቁ ባለ በቀናት ውስጥ የኡጋንዳው ፕሬዝዳንት ዩዌሪ ሙሴቬኒ ትራምፕን አድንቀዋል።

"አሜሪካ ከመቼውም የበለጠ ምርጥ መሪ አግኝታለች"ሲሉም ለትራምፕ ያላቸውን ፍቅር ሙሴቬኒ ገልፀዋል።

ሙሴቬኒ ይህን ያሉት በኡጋንዳ መዲና ካምፓላ የምሥራቅ አፍሪካ አገራት ህግ አውጪዎች ስብሰባ ላይ ነው።

"ትራምፕን አፈቅራቸዋለው ምክንያቱም አፍሪካዊያንን በግልፅ ይናገራሉ። አፍሪካውያን የራሳቸውን ችግር መፍታት ይኖርባቸዋል። አፍሪካውያን ደካሞች ናቸው"ብለዋል ሙሴቬኒ።

ይህ ንግግራቸው ብዙ የአፍሪካ አገራት መሪዎች ስለ ትራምፕ ካላቸው አስተያየት ጋር የሚቃረን ነው። ብዙዎቹ የአፍሪካ መሪዎች ትራምፕን በዘረኛ ንግግራቸው አውግዘዋል።

የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮንም አፍሪካውያን በትራምፕ ላይ መቆጣታቸው ትክክል እንደሆነና እሳቸውም ይህን ስሜት እንደሚጋሩ አስታውቀው ነበር።

ትራምፕ "ቆሻሻ" ካሏቸው አገራት መካከል አንዷ በሆነችው ሄቲ ውስጥ ደግሞ ሰዎች ተቃውሟቸውን ለማሰማት አደባባይ ወጥተዋል።

በኡጋንዳ የአሜሪካ አምባሳደር ዲቦራ ማላክ ትራምፕን በዘረኛ ንግግራቸው ከወቀሱ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ሙሴቬኒ ትራምፕን ማሞካሸታቸው ብዙዎችን አስገርሟል።