ካናዳ በዩክሬኑ አየር መንገድ ለሞቱ ዜጎች ቤተሰብ የገንዘብ ድጋፍ ልትሰጥ ነው

የፎቶው ባለመብት, AFP via Getty Images
የካናዳው ጠቅላይ ሚንስትር ጀስቲን ትሩዶ ኢራን በስህተት መትቼ ጣልኩት ባለችው የመንገደኞች አውሮፕላን ለሞቱት ተሳፋሪ ቤተሰቦች የገንዘብ ድጋፍ እንደሚደረግ ገለፁ።
ጠቅላይ ሚንስትሩ የገንዘብ ድጋፉ የሚደረገው የካናዳ ዜጎች እና የካናዳ ቋሚ ነዋሪ ለነበሩ ሕይወታቸውን ላጡ ተሳፋሪዎች ቤተሰቦች ነው ብለዋል።
ትሩዶ ለእያንዳንዱ የሟች ቤተሰብ 25 ሺህ የካናዳ ዶላር (ከ600 ሺህ ብር በላይ ) እንደሚሰጣቸው ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚንስትር ትሩዶ ይህ ገንዘብ በሃዘን ወቅት ለሚደረጉ ጉዞዎች እና ተያያዥ ወጪዎች ቤተሰቦችን ያግዛል የሚል ተስፋ እንዳላቸው ገልፀዋል።
ኢራን በሚሳኤል መትታ በጣለችው የዩክሬን አየር መንገድ የበረራ ቁጥር 752 ተሳፍረው ከነበሩት መካከል 57ቱ የካናዳ ዜጎች ሲሆኑ፤ 29ኙ ደግሞ የካናዳ ቋሚ ነዋሪዎች ናቸው።
በቁጥር ከተጠቀሱት የካናዳ ዜጎች እና ቋሚ ነዋሪዎች መካከል አብዛኛዎቹ ትውልደ ኢራናውያን ናቸው።
"የሟች ቤተሰቦች ከፍተኛ ወጪ ከፊታቸው ተደቅኗል። ለቀብር ማስፈጸሚያ እንዲሁም ከቤተሰቦቻቸው ጋር ለመገናኘት ርቀው ይጓዛሉ። ከመቼውም በበለጠ ጊዜ የእኛን እርዳታ የሚሹት አሁን ነው" ብለዋል - ጠቅላይ ሚኒስትር ትሩዶ።
ከሟች ቤተሰቦች መካከል 20 የሚሆኑት፤ የዘመዶቻቸው አስክሬን ወደ ካናዳ እንዲመጣላቸው በጠየቁት መሠረት፤ በጥቂት ቀናት ውስጥ አስክሬናቸው ወደ ካናዳ እንደሚመጣ ጠቅላይ ሚንስትሩ አስታውቀዋል።
ትሩዶ የኢራን መንግሥት ለሟች ቤተሰቦች የገንዘብ ካሳ እንደሚከፍል የካናዳ መንግሥት ይጠብቃል ብለዋል።
ኢራን የዩክሬን የመንገደኞች አውሮፕላን የተከሰከሰው በቴክኒክ ብልሽት ነው ስትል ብትቆይም በመጨረሻ በስህተት መትታ መጣሏን ማመኗ ይታወሳል።
አውሮፕላኑ 176 ተሳፋሪዎችን ይዞ ከኢራን መዲና ቴህራን ወደ ዩክሬኗ ኪዬቭ ለመብረር እንደተነሳ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ነበር በሁለት ሚሳኤሎች ተመትቶ የወደቀው።
የኢራን ጦር አውሮፕላኑ በኢራን አብዮታዊ ጥበቃ አቅራቢያ በሚገኙ የደህንነት ሥፍራዎች እየበረረ ስለነበረ ''በሰዎች ስህተት" ተመትቶ ስለመጣሉ ተናግሯል።
ትሩዶ ኢራን የአውሮፕላኑን የበረራ መመዝገቢያ ሳጥን "ብላክ ቦክስ" በፍጥነት ለፈረንሳይ እንድትልክ ጭምር ጠይቀዋል።
የአፍጋኒስታን፣ ብሪታኒያ፣ ካናዳ፣ ስዊድን እና ዩክሬን የውጪ ጉዳይ ሚንስትሮች፤ የአውሮፕላኑ አደጋ ምርመራ በትብብር እና በግልጸኝነት እንዲከናወን ኢራንን አሳስበዋል።















