አራት ዩኒቨርሲቲዎች ከ470 በላይ ተማሪዎችና ሠራተኞች ላይ እርምጃ ወሰዱ

ታትሟል

የ2012 የትምህርት ዘመን ከተጀመረ ከአምስት ወራት አይበልጥም። ይሁንና ከወራት በፊት በወልዲያ ዩኒቨርሲቲ የተከሰተውን የተማሪዎች ግጭት ተከትሎ በተለያዩ ዩኒቨርሲቲዎች ግጭቱ ተስፋፍቶ የሞትና የአካል ጉዳት ያደረሱ ግጭቶች ሲስተናገዱ ቆይተዋል። የመማር ማስተማር ሂደቱም በከፍተኛ ሁኔታ ተስተጓጉሏል።

ዩኒቨርሲቲዎቹም በግጭቱ ተሳትፎ አላቸው ያሏቸውን ተማሪዎችና የአስተዳደር ሰራተኞች ላይ እርምጃ መውሰድ መጀመራቸው ተሰምቷል።

ርምጃ ከወሰዱት ዩኒቨርሲቲዎች መካከል የጎንደር ዩኒቨርስቲ አንዱ ነው። ዩኒቨርሲቲው በፌሰስቡክ ገጹ ባሰፈረው መረጃ መሰረት በዩኒቨርሲቲው በተከሰተው አለመረጋጋት የመማር ማስተማር ሂደቱ ሲቆራረጥ ቆይቷል።

ተቋሙ ከተለያዩ አካላት ጋር ባደረጋቸው ውይይቶችም አንዳንድ መምህራን፣ ተማሪዎች፣ የአስተዳደር ሰራተኞች እና የጤና ባለሙያዎች የተከሰተውን ሁከት በማነሳሳት፣ የህይወት እና የአካል ጉዳት እንዲደርስ በተለያዩ ደረጃዎች አሉታዊ አስተዋፅኦ በማድረግ፣ በተደጋጋሚ ምክር ቢሰጣቸውም ችላ በማለት ሁከት እንዲስፋፋ በማሰብ ሰራተኞችን በማነሳሳት እና ቀስቃሽ መልእክቶችን በመበተን ተሳታፊ ሲሆኑ መቆየታቸውን መረዳት ችያለው ብሏል ዩንቨርሲቲው።

በመሆኑም ታህሳስ 22/2012 ዓ.ም የዩኒቨርሲቲው ሴኔት ባካሄደው አስቸኳይ ስብሰባ 2 ተማሪዎች ለአንድ አመት፣ 39 ተማሪዎች ለሁለት አመት፤ እንዲሁም 11 ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ ከትምህርት ገበታቸው (ከዩኒቨርሲቲው) እንዲሰናበቱ መወሰኑን ገልጿል።

ከዚህም በተጨማሪ ለ7 መምህራን ቀላል የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ፣ ለ3 መምህራን የመጨረሻ የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ፣ ለ3 መምህራን እና ለ8 የአስተዳደር ሰራተኞች እንዲሁም የጤና ባለሙያዎች ሙሉ በሙሉ ከስራ እንዲሰናበቱ ወስኗል።

ሌላኛው ግጭት ተነስቶ ሁለት ተማሪዎች የሞቱበት ወሎ ዩኒቨርሲቲ የመማር ማስተማር ስራውን አውከዋል ያላቸውን 335 ተማሪዎች፣ የአስተዳደር ሰራተኞችና መምህር ላይ ርምጃ ወስዷል።

የዩኒቨርሲቲው ፕሬዚዳንት ዶክተር አባተ ጌታሁን ለኢዜአ እንደገለጹት በብሔርና በኃይማኖት ሽፋን በተፈጠረ አለመረጋጋት የመማር ማስተማር ስራው ባለፉት ወራት ውስጥ ለሶስት ጊዜ መቋረጡን አውስተዋል።

ባለፉት ሁለት ወራት ሰላማዊ የመማር ማስተማር ስራው እንዳይቀጥል ፍላጎት ያላቸውን 332 ተማሪዎች፣ ሁለት የአስተዳደር ሰራተኞችና አንድ መምህር ላይ እርምጃ መወሰዱንም አስታውቀዋል።

ከነዚህ መካከል 12 ተማሪዎችና ሁለት የአስተዳደር ሰራተኞች በህግ ቁጥጥር ስር ውለው ጉዳያቸው እየታየ መሆኑን የገለጹት ፕሬዝዳንቱ አንድ መምህር ከስራ መታገዱን አመልክተው ለ320 ተማሪዎች ደግሞ የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸው መሆኑን ገልጸዋል።

እርምጃ የተወሰዳባቸው ተማሪዎች፣ የአስተዳደር ሰራተኞችና መምህሩ በዩኒቨርስቲው ውስጥና ውጭ ሁከትና ብጥብጥ እንዲፈጠር ምክንያት ሆነው መገኘታቸው በተጨባጭ ማስረጃ የተረጋገጠባቸው መሆናቸውን አብራርተዋል።

በድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲም ግጭቶች በተደጋጋሚ ተነስተው በተለያዩ ጊዜያት የተማሪዎች ሕይወት ማለፉ ይታወሳል። በተፈጠረው የጸጥታ ችግር የተለያየ ተሳትፎ በነበራቸው ተማሪዎች ላይ ርምጃ መውሰዱን ዩኒቨርሲቲው አስታውቋል።

በዚህም መሰረት ሁለት ተማሪዎች ሙሉ በሙሉ፤ ሰባት ተማሪዎች እያንዳንዳቸው ለሶስት ዓመት፣ ስምንት ተማሪዎች እያንዳንዳቸው ለሁለት ዓመት ከትምህርት ገበታቸው የታገዱ ሲሆን አንድ ተባሮ የነበረ (በወቅቱ የዩኒቨርሲቲው ተማሪ ያልነበረ) ነገር ግን በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ውስጥ ተሳታፊ የነበረ ዩኒቨርሲቲው ክስ መስርቶበት በህግ ተጠያቂ እንዲሆን ወስኗል።

የጅማ ዩኒቨርሲቲ ሌላኛው በግጭት ሲታመስ የነበረ ተቋም ነው። ይህንን ተከትሎም የዩኒቨርሲቲው ሴኔት ታኅሳሥ 27/2012 ዓ/ም ባደረገው ስብሰባ ባለፉት ሁለት ወራት ከተፈጠረዉ አለመረጋጋት ጋር በተገናኘ ትምህርት እንዲስተጓጎል ፍላጎት ባላቸዉና ሁኔታዎችን በመጠቀም ችግር የፈጠሩ 51 ተማሪዎችን በመለየት እርምጃ መውሰዱን ገልጿል።

በዚህም 31 ተማሪዎች የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ የተሰጣቸዉ ሲሆን 20 ተማሪዎች ላይ ከ1 አመት እሰከ ሙሉ በሙሉ ከትምህርት መርሃ-ግብር ማገድ የሚደርስ የዲሲፕሊን ቅጣት ርምጃ መወሰዱን ዩኒቨርሲቲው በፌስቡክ ገጹ አስፍሯል።

ከተቋማዊ ለዉጥ ሂደቱ ጋር በተገናኘ በአስተዳደርና ተማሪዎች አገልግሎት ዙርያ የምክትል ፕሬዝዳንት እና የ3 ዳይሬክተሮች እንዲሁም በሌሎች ዘርፎችም የ3 ሃላፊዎችን ለዉጥ አድርጌያለሁ ብሏል ጅማ ዩኒቨርሲቲ።

አራቱ ዩኒቨርሲቲዎች በአጠቃላይ ባለፉት ሁለት ወራት በተከሰቱት ግጭቶች ተሳትፎ ነበራቸው ባሏቸው ከ470 በላይ ተማሪዎችና የአስተዳደር ሰራተኞች ላይ እርምጃ ወስደዋል።