ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የጠፋ ህፃን ተቀብሮበታል በሚል ያልተጣራ ወሬ የናይጀሪያው ቤተክርስቲያን ተቃጠለ
ታትሟል
በደቡብ ምዕራብ ናይጀሪያ አኩሬ ከተማ የአንድ ዓመት ህፃን ልጅ በማምለኪያው ቦታ ተቀብሯል በሚል ያልተጣራ ወሬ ሰልፈኞቹ ቤተ ክርስቲያኑን አቃጥለውታል ።
ህፃኑ በቤተክርስቲያኗ ውስጥ ከእናቱ ጋር የታየው ባለፈው ወር ሲሆን፤ ከቤተ ክርስቲያኗም ሳይወጣ በዚያው የውሃ ሽታ ሆኖ ቀርቷል።
የአይን እማኞች እንደገለፁት ፖሊስ በቁጣ የነደዱትን ሰልፈኞች ለመበተንም ሙከራ በሚያደርግበት ወቅትም ሁለት ሰዎችን አቁስሏል።
ፖሊስ በበኩሉ አንድ አባላቸው እንደተገደለ ገልጿል።
ልጁ ቤተክርስቲያኗ ውስጥ እንዴት ሊጠፋ ቻለ የሚለው ጉዳይ እስካሁን ምላሽ ያላገኘ እንቆቅልሽ ሲሆን የህፃኑ እናት ሞዱፔ ኮላዌሌ ለቢቢሲ እንደተናገረችው ተገድሎ ይሆኗል የሚል ጥርጣሬ አላት።
የቤተ ክርስቲያኗ መስራች አልፋ ባባቱንዴ ከህፃኑ መጥፋት ጋር ተያይዞ ባለፈው ሳምንት በቁጥጥር ስር የዋለ ሲሆን፤ እስካሁንም የልጁን መጥፋት አስመልክቶ ምንም ከማለት ተቆጥቧል ተብሏል።
የቢቢሲ ዩርባ ዘጋቢ ቴሚቶፕ አዴዴጂ ከቦታው እንደዘገበው የልጁ አስከሬን አልተገኘም።