ለመታሰር ብሎ ሰው የገጨው የእድሜ ልክ እስራት ተፈረደበት

ታትሟል

መኪና ውስጥ የሚኖረው ግለሰብ ለመታሰር ብሎ ሳይክል ነጂ በመግጨቱ የእድሜ ልክ እስራት ተፈረደበት።

ግለሰቡ ሥራ አጥ ሲሆን፤ የሚኖረውም መኪና ውስጥ ነበር። እስር ቤት ለመግባት በማሰብ ሆነ ብሎ በሳይክል የሚጓዝ ሰው ከገጨ በኋላ ነው በጀርመን ፍርድ ቤት የእድሜ ልክ እስራት የተፈረደበት።

ባለ ሳይክሉ ክፉኛ ጉዳት ደርሶበታል።

ግለሰቡ በኮምፒውተር ሳይንስ ዘርፍ ውስጥ ይሠራ ነበር። ሥራውን ካጣ በኋላ ግን ያለውን ገንዘብ ባጠቃላይ አውሮፓን በመዞር አባክኖታል። የ62 ዓመቱ ግለሰብ ሥራ እንዲሁም መኖሪያ ቤትም የለውም።

ግለሰቡ ሳይክል ነጂውን ከመግጨቱ በፊት፤ እስር ቤት ቢገባ ሊያገኝ የሚችለውን "ጥቅም" ሲያጠያይቅ ነበር ተብሏል። ግለሰቡ እስር ቤት ቢገባ፤ መጠለያ እንዲሁም ምግብ እንደሚያገኝም በማሰብ ነበር ባለ ሳይክሉን የገጨው።

ፍርድ ቤቱ እንዳለው፤ ግለሰቡ "ስግብግብ በመሆኑ" የ48 ዓመቱን ባለ ሳይክል ገጭቷል። ክስ የቀረበበትም በግድያ ሙከራ ነው።

የፍርድ ቤቱ ቃል አቀባይ እንዳሉት፤ ግለሰቡ በድርጊቱ ጸጸት ስለተሰማው የጡረታ ገንዘቡን ለባለ ሳይክሉ መታከሚያ ለማዋል ተስማምቷል።