ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የቀድሞው የፓኪስታን መሪ በአገር ክህደት ሞት ተፈረደባቸው
የቀድሞው የፓኪስታን ወታደራዊ መሪ የነበሩት ጄነራል ፔርቬዝ ሙሻራፍ፤ ኢስላማባድ ውስጥ በተሰየመ ልዩ ፍርድ ቤት የሞት ፍርድ ተበየነባቸው።
በጄነራሉ ላይ የቀረበውን ከፍተኛ የአገር ክህደት ወንጀል በሦስት ዳኞች ሲመለከት የነበረው ፍርድ ቤት፤ ለስድስት ዓመታት ሲታይ በቆየው ክስ ላይ ውሳኔ ሰጥቷል።
ጄነራል ሙሻራፍ በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ከ20 ዓመታት በፊት ሥልጣን ጨብጠው ለሰባት ዓመታት ፓኪስታንን መርተዋል።
ሞት የተፈረደባቸው ሙሻራፍ እንደ አውሮፓዊያኑ በ2016 ለህክምና ወደ ዱባይ እንዲሄዱ ተፈቅዶላቸው በአሁኑ ጊዜ እዚያው ይገኛሉ።
በጄነራሉ ላይ የቀረበው ክስ በ2007 (እአአ) የአገሪቱን መተዳደሪያ ሕገ መንግሥት በማገድና በሥልጣን ላይ ለመቆየት ሲሉ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጃቸው ነው።
በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ ጄነራል ሙሻራፍ ከሚታከሙበት ሆስፒታል ባስተላላፉት የቪዲዮ መልዕክት፤ የቀረበባቸውን ክስ "መሰረተ ቢስ" ሲሉ አጣጥለውት ነበር።
ጄነራል ሙሻራፍ ሕገ መንግሥቱን በማገድ ለፍርድ የቀረቡ የመጀመሪያው ወታደራዊ መሪ እንደሆኑ ተነግሯል።
በጄነራሉ ላይ የተላለፈው የሞት ፍርድ የተወሰነው ዛሬ በተካሄደና ጉዳዩን ሲመለከቱ ከነበሩት ሦስት ዳኞች ሁለቱ ውሳኔውን ደግፈውት ነው።
ስለጄነራል ሙሻራፍ በጥቂቱ
ጄነራል ፔርቬዝ ሙሻራፍ እንደ አውሮፓዊያኑ በ1998 የፓኪስታንን ጦር ሠራዊት እንዲመሩ ተሹመው የነበረ ሲሆን በቀጣዩ ዓመት በተደረገ ጦርነት ሰበብ ከወቅቱ የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናዋዝ ሸሪፍ ጋር አለመግባባት ተፈጥሮ በመፈንቅለ መንግሥት ስልጣን ያዙ።
ጄነራል ሙሻራፍ ለሰባት ዓመት የፓኪስታን ፕሬዝዳንት ሆነው በቆዩበት ጊዜ ከበርካታ የግድያ ሙከራዎችና የተለያዩ ሴራዎች ለማምለጥ ችለዋል።
ሙሻራፍ በአሜሪካ ላይ የተፈጸመውን የመስከረም አንዱን የሽብር ጥቃት ተከትሎ በአገር ውስጥ ተቃውሞ ቢገጥማቸውም አሜሪካ የከፈተችውን "ጸረ ሽብር ጦርነትን" በመደገፋቸው በዓለም አቀፍ ደረጃ እውቅናን አግኝተዋል።
ጄነራሉ ስልጣናቸውን ለቀው ከፓኪስታን ከወጡ ከአምስት ዓመት በኋላ በምርጫ ለመሳተፍ ቢመለሱም እንዳይወዳደሩ ተከልክለው በርካታ ክሶች ቀርበውባቸው ነበር።
የአገር ክህደት ክስ ከተመሰረተባቸው በኋላ ጄነራሉ ፍርድ ቤት ሁለት ጊዜ ብቻ የቀረቡ ሲሆን ጊዜያቸውን ያሳልፉ የነበረው ኢስላማባድ ውስጥ በሚገኘው እርሻቸውና በሠራዊቱ ሃኪም ቤት ውስጥ ነበር።
ጄነራል ሙሻራፍ ከአምስት ዓመት በፊት ወደ ሌላኛዋ የፓኪስታን ከተማ ካራቺ በመሄድ ኑሯቸውን አድርገው በመቆየት በ2016 (እአአ) ፓኪስታንን ለቀው አሁን ወደሚገኙባት ዱባይ ሄደዋል።