ተዋናይቷ ቻርሊዝ ቴሮን እናቷ አባቷን የገደለችበትን ምክንያት ይፋ አደረገች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ተዋናይቷ ቻርሊዝ ቴሮን እናቷ ራሷን ለመከላከል አባቷን በሽጉጥ መግደሏ እንደማያሳፍራት በቅርቡ ተናግራለች።
አባቷ ሲገደል የ15 ዓመት ታዳጊ የነበረች ሲሆን፤ ሰካራም የነበረው አባቷ በአንድ ወቅት እሷና እናቷ የተደበቁበት ክፍል በር ለመክፈት በሽጉጥ እሩምታ አናውጦት ነበር።
"ምንም እንኳን የሽጉጥ እሩምታ ቢያርከፈክፍም በተዓምር ተርፈናል። እሷ እኛን ለመከላከል በመተኮሷ ሊሞት ችሏል" በማለት ኤንፒአር ለተባለው ሚዲያ ተናግራለች።
አክላም " ስለዚህ ጉዳይ በተደጋጋሚ በምናወራበት ወቅት የኛ ታሪክ ብቻ ሳይሆን በዚህ መንገድ ያለፉና እያለፉ ያሉ የብዙ ሰዎች ታሪክ መሆኑንም እንረዳለን" ብላለች።
በደቡብ አፍሪካ የንግድ መዲና በሆነችው ጆሃንስበርግ አካባቢ በምትገኝ የእርሻ ቦታ ያደገችው ቻርሊዝ አባቷ "ቀውስ" ነበር ትላለለች።
በየጊዜው መስከሩና፤ ተደባዳቢ መሆኑ ደግሞ ሁኔታውን ተስፋ አስቆራጭ አድርጎት ነበርም በማለት ታስረዳለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ከሰካራም ጋር መኖር እንዲህ በቀላሉ የሚረሳ ነገር አይደለም የምትለው ቻርሊዝ እስከ ህይወቷ መጨረሻም መጥፎ ጠባሳ ትቶ እንዳለፈ ታስረዳለች።
አባቷ የሞተበትንም ያችን ዕለት ስታስታውስ አባቷ በወቅቱ ሰክሮ እንደነበርና እየተንገዳገደም ሽጉጡን ይዞ መጣ።
"በወቅቱ እኔና እናቴ እኔ መኝታ ክፍል ውስጥ ነበንር፤ በሩን ገፍቶ እንዳይገባ ባለ በሌለ ኃይላችን ተጭነነው ነበር"
"ሁለታችንንም ገፍቶ እንዳይገባ እንዲሁ ተደግፈን ባለንበት ሰዓት ትንሽ ወደ ኋላ አፈገፈገና በሩ ላይ መተኮስ ጀመረ። ከተኩሱ በተአምር ማምለጥ ችለናል። እናቴም በአፀፋው ተኮሰችና ህይወታችንን አተረፈችው" ብላለች።
አባቷ ቤታቸው ውስጥ ያደረሰባቸውን ጥቃቶች በተደጋጋሚ ለብዙዎች እንደምታጋራም ተናግራለች።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የኦስካር ተሸላሚዋ ተዋናይት ከዚህ በተጨማሪ በአንድ ወቅት አንድ የፊልም ዳይሬክተር በማይሆን መንገድ እንደነካትም ተናግራለች። በወቅቱም ይቅርታ ጠይቃ መውጣቷ አሁንም ድረስ እንደ እግር እሳት የሚያንገበግባት ጉዳይ ሆኗል።
"ትክክለኛ ነገሮችን ባለማለቴ ራሴን ነው ጥፋተኛ ያደረግኩት፤ ለምንድን ነው በኃይለ ቃል ያልመለስኩለት? ለምንስ ታግሼው አለፍኩ" በማለት ራሷን ትጠይቃለች።
አዲሱ ፊልሟ ቦምብ ሼል በፆታዊ ትንኮሳዎች ላይ የሚያጠነጥን ሲሆን፤ ሜገን ኬሊ የተባለች የቴሌቪዥን አቅራቢ ገፀ ባህርይን ወክላ ትጫወታለች።
ታሪኩም በፎክስ ኒውስ ሚዲያ ይሰሩ የነበሩ ሴቶች በወቅቱ የነበረው ፕሬዚዳንት ሮጀር አላይስ አደረሰብን ስላሉት የፆታዊ ትንኮሳዎች ውንጀላ የሚያሳይ ነው።
"ፊልሙ ፆታዊ ትንኮሳ ሲባል አካላዊ ጥቃትን እንዲሁም መደፈርን ብቻ ሳይሆን ሌሎችም አይነት ትንኮሳዎች እንዳሉ የሚያሳይ ነው" ትላለች።
አክላም በቃላት የሚደረጉ ትንኮሳዎች፤ የማይሆኑ መነካካቶች እንዲሁም ስራሽን ልታጭ ትችያለሽ የሚሉ ማስፈራሪያዎች የትንኮሳው አካል ናቸው፤ እነዚህን ደግሞ ብዙዎቻችን ያጋጠሙን ናቸው" ብላለች።












