የቻይና ቴሌቪዢን በኦዚል ምክንያት የአርሰናልን የቀጥታ ጨዋታ አቋረጠ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የቻይናው የዜና ተቋም ሲሲቲቪ እሁድ የተካሄደውን የአርሰናልና የማንቸስተር ሲቲ ጨዋታን እንዳይተላለፍ አግዶታል። ምክንያቱ ደግሞ የአርሰናሉ ሜሱት አዚል በቻይና ስለሚገኙ ሙስሊሞች በማህበራዊ ሚዲያ አስተያየቱን በመስጠቱ ነው።
ኦዚል በቻይና ስለሚገኙ ኡጉር ሙስሊሞች የሰጠው አስተያየት መነጋገሪያ ከመሆን አልፎ ቡድኑ አርሰናል ጉዳዩ እኔን አይመለከተኝም የሚል መግለጫ እንዲያወጣም አስገድዶት ነበር።
የአርሰናል እግር ኳስ ክለብ ''አርሰናል እንደ ድርጅት ከፖለቲካ ጋር ምንም ግንኙነት የለውም'' ብሏል።
አክሎም '' ሜሱት ኦዚል በማህበራዊ ሚዲያ ያስተላለፈውን መልእክት ተከትሎ የአርሰናል እግር ኳስ ክለብ ጉዳዩ እንደማይመለከተውና የኦዚል የግል ሃሳብ መሆኑን መግለጽ እንፈልጋለን'' ብሏል።
የቻይና እግር ኳስ ማህበር በበኩሉ የአርሰናሉ ተጫዋች የሰጠው አስተያየት ተቀባይነት የሌለውና የበርካታ ቻይናውያን ኳስ አፍቃሪዎችን ስሜት የጎዳ ነው ብሏል።
ሲሲቲቪ ጣቢያም እሁድ የተካሄደውና የባለፈው ዓመት ሻምፒዮኖቹ ማንቸስተር ሲቲዎች አርሰናልን 3 ለባዶ ያሸነፉበትን ጨዋታ በመተው ቶተንሃምና ዎልቭስ ያደረጉትን ጨዋታ አስተላልፏል።
ሜሱት ኦዚል በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ባሰፈረው መልእክት የኡጉር ሙስሊሞችን ''እስራትና ስቃይን መቋቋም የሚችሉ ተዋጊዎች'' ብሎ በማድነቅ፤ ቻይና እና ዝምታን መርጠዋል ያላቸው ሌሎች ሙስሊሞችን ተችቷል።
ቻይና በሚሊየን የሚቆጠሩ የኡጉር ሙስሊም ማህበረሰቦችን ያለፍርድቤት ትእዛዝ አስራለች፤ በማጎሪያ ካምፖችም ታሳቃያቸዋለች በማለት አንዳንድ የሰብአዊ መብት ተሟጋቾች ይከሳሉ።
ቻይና ማዕከላቱ ሀይማኖታዊ አክራሪነትን ለመዋጋት የሚረዱ የቴክኒክና ስልጠና ማስተማሪያዎች እንጂ ማጎሪያ ካምፖች አይደሉም በማለት በተደጋጋሚ ገልጻለች።












