በኒውዚላንድ እሳተ ገሞራ ፍንዳታ የሟቾች ቁጥር 16 ደረሰ

ታትሟል

ባለፈው ሳምንት በኒውዚላንድ ባጋጠመው የእሳተ ገሞራ ፍንዳታ የሟቾች ቁጥር ወደ 16 ከፍ ማለቱ ተዘግቧል። ከአደጋው ከባድ ጉዳት ደርሶበት የነበረ አንድ ግለሰብ ሕይወቱ ማለፉን ፖሊስ አስታውቋል።

ማንነቱ ያልተገለጸው ይህ ግለሰብ ለህክምና ወደ አውስትራሊያ ተወስዶ ነበር። እስካሁን 20 የሚደርሱ ሰዎች ከፍተኛ ቃጠሎ ደርሶባቸው በሞትና በሕይወት መካከል ይገኛሉ።

በተጨማሪም ዛሬ እሳተ ገሞራው ወደ ፈነዳበት ደሴት በመሄድ የሌሎች ሁለት ሰዎችን ሬሳ ለማግኘት የተደረገው ጥረት ሳይሳካ ቀርቷል።

በአካባቢው ፍለጋ የሚያደርጉ ስምንት ፖሊሶች ለ 75 ደቂቃዎች ያክል ቢሰማሩም ምንም ነገር ሊገኝ እንዳልቻለ ምክትል ፖሊስ ኮሚሽነሩ ማይክ ክለመንት ለጋዜጠኞች ገልጸዋል።

'' ምንም እንኳን ፍለጋችንን አጠናክረን ብንቀጥልም ተጨማሪ የሟቾችን ሬሳ ማግኘት አልቻልንም'' ብለዋል።

እስካሁን የተገኙ የሟቾች ሬሳ ላይ ምርመራ እየተደረገ ሲሆን ከሟቾች መካከል አንድ ኒውዚላንዳዊ የ 24 ዓመት አስጎብኚ እንደሚገኝበት ተገልጿል። አንዲት 15 ዓመት አውስትራሊያዊና የ 53 ዓመት አባቷ እንዲሁም ሌላ የ 51 ዓመት አውስትራሊያዊ ከሟቾች መካከል ናቸው።

የሌሎቹን ሟቾች ማንነት ለመለየት ደግሞ ተጨማሪ ምርመራዎች እንደሚያስፈልጉ ተገልጿል።

እሳተ ገሞራው በደሴቲቱ ድንገት ሲፈነዳ 47 ሰዎች በጉብኝት ላይ የነበሩ ሲሆን ከእነሱም መካከል 24 አውስትራሊያውያን፣ ዘጠኝ አሜሪካውያን፣ አምስት ኒውዚላንዳውያን፣ አራት ጀርመናውያን፣ ሁለት ቻይናውያን፣ ሁለት እንግሊዛውያን እና አንድ ከማሌዢያ ናቸው።