አልጄሪያ ሁለት የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሮቿን አሰረች

የታሰሩት ሚኒስትሮች

የፎቶው ባለመብት, EPA

ታትሟል

አንድ የአልጄሪያ ፍርድ ቤት ሁለት የቀድሞ ሚኒስትሮችን ከከባድ የሙስና ወንጀል ምርመራ ጋር በተያያዘ በእስር እንዲቀጡ ፈረደባቸው።

አህመድ ኦያህያ የ 15 ዓመት እስር የተበየነባቸው ሲሆን አብደልማሊክ ሴላል ደግሞ 12 ዓመት በእስር ቤት እንዲያሳልፉ ብያኔ ተላልፎባቸዋል። ሁለቱም የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሮች ከአንድ የመኪና አምራች ኩባንያ ጋር በተያያዘ ስልጣናቸውን ያለአግባብ ተጠቅመዋል የሚል ክስ ነበር የቀረበባቸው።

የቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትሮቹ ለፍርድ ሲቀርቡ አልጄሪያ ነጻነቷን ከፈረንሳይ ቅኝ ግዛት ካገኘችበት የአውሮፓውያኑ 1962 ጀምሮ ይህ የመጀመሪያው እንደሆነ ተገልጿል።

አህመድ ኦያህያ እና አብደልማሊክ ሴላል ለረጅም ዓመት አልጄሪያን የመሩት የፕሬዝዳንት አብደላዚዝ ቡተፍሊካ ወዳጆች የነበሩ ሲሆን ፕሬዝዳንቱ ባለፈው ዓመት ሚያዝያ ላይ ከስልጣን መልቀቃቸው ይታወሳል።

የአልጄሪያ ዜጎች ፕሬዝዳንቱ ከስልጣን ከለቀቁ በኋላም ፈጣን የሆኑ ለውጦች በሀገሪቱ መምጣት እንዳለባቸው በማስጠንቀቅ ተቃውሞ ላይ ናቸው። በስልጣን ላይ ያለው ፓርቲም በሙስና የተዘፈቀ እንደሆነ ዜጎች ያምናሉ።

አህመድ ኦያህያ እና አብደልማሊክ ሴላል በሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር፣ ስልጣንን ያለአግባብ መጠቀም እና ለአንድ የመኪና አምራች ኩባንያ ጥቅም በማስገኘት በሚሉ ክሶች ከተጠረጠሩ 19 ተከሳሾች መካከል ናቸው።

አብደልሰላም ቡኮሬብ የተባሉ አንድ የሚኒስትሮች ካቢኔ አባል ደግሞ በሌሉበት ጥፋተኛ መሆናቸው ተረጋግጦ የ 20 ዓመት እስር ተፈርዶባቸዋል። ሰውዬው በሀገር ውስጥ ስለሌሉም ዓለማቀፍ የእስር ትእዛዝ እንደቀጣባቸው ታውቋል።

ብያኔ የተሰጣቸው ሀላፊዎች በ 10 ቀናት ውስጥ ይግባኝ ማለት ይችላሉ ብሏል ፍርድ ቤቱ።

ከመኪና አምራች ድርጅቶች ጋር በተያያዘ በአልጄሪያ ምርመራ የተጀመረው በአውሮፓውያኑ 2014 ሲሆን ትልልቅ ኮርፖሬሽኖችና የውጭ ሀገር ባለሃብቶች የሚሳተፉበት ነው። በዘርፉ ፍቃድ የሚሰጣቸውም የቀድሞው ፕሬዝዳንት ቡተፍሊካ ቅርብ ሰዎች ብቻ እንደነበር በስፋት ይነገራል።

በሀላፊዎቹ ላይ ብያኔው የተላለፈው ፕሬዝዳንት አብደላዚዝ ቡተፍሊካ ከስልጣን ከወረዱ በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ከሚካሄደው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ ሁለት ቀናት አስቀድሞ ነው።