የኢራኑ ፕሬዝዳንት ወንድም በሙስና ታሰሩ

የፕሬዝዳንቱ ወንድም ሆሲን ፌሬይዱን

የፎቶው ባለመብት, AFP

ታትሟል

የኢራኑ ፕሬዝዳንት ሃሰን ሩሃኒ ወንድም በሙስና አምስት ዓመት ተፈርዶባቸው የእስር ጊዜያቸውን መጀመራቸው ተነገረ።

የፕሬዝዳንቱ ወንድምና የቅርብ አማካሪ የነበሩት ሆሲን ፌሬይዱን የእስር ጊዜያቸውን ለመጀመር ዋና ከተማዋ ቴህራን ወደሚገኘው ኤቪን እስር ቤት ዛሬ መግባታቸውን ጠበቃቸው ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙኃን ተናግረዋል።

የፕሬዝዳንቱ ወንድም ባለፈው ግንቦት "ጉቦ ሲቀበሉ" ተገኝተዋል ተብለው ነበር የተያዙት። በዚህም ሳቢያ የሰባት ዓመት እስር ተፈርዶባቸው ነበር።

ነገር ግን ይግባኝ ሰሚ ፍርድ ቤት ጉዳያቸውን ከተመለከተ በኋላ እስሩን ወደ አምስት ዓመት ዝቅ ያደረገው ሲሆን፤ በተጨማሪ ደግሞ በሕገ ወጥ መንገድ ያገኙትን ማንኛውንም ንብረት ለመንግሥት እንዲያስረክቡና 27 ሚሊዮን ዶላር የገንዘብ ቅጣት ጥሎባቸዋል።

ሆሲን ፌሬይዱን ምንም አይነት ጥፋት አለመፈጸማቸውን የገለጹ ሲሆን፤ ለዘብተኛ መሆናቸው የሚነገርላቸው የፕሬዝዳንቱ አንዳንድ ደጋፊዎች ደግሞ በአገሪቱ የሕግ አስፈጻሚ ተቋማት ውስጥ ያሉ አክራሪዎች ፕሬዝዳንቱን ለማሳጣት የወሰዱት እርምጃ ነው ይላሉ።

ሕግ አስፈጻሚው ግን ይህንን እና ሌሎች ጉዳዮችን በሚመለከትበት ጊዜ ምንም ዓይነት ፖለቲካዊ ጣልቃ ገብነት እንደሌለ አስተባብሏል።

ፕሬዝዳንት ሩሃኒ ቀደም ሲል በተመረጡባቸው ሁለት ምርጫዎች ወቅት ባደረጉት የምርጫ ቅስቀሳ ሙስናን ለማስወገድ ቃል ገብተው የነበረ ቢሆንም ፈተና ገጥሟቸው ቆይቷል።