የአየር ጠባይ ለውጥ ላይ የሚመክረው ስብሰባ ለአፍሪካ ምን ይዞ ይሆን?

ታትሟል

አፍሪካ በዓለማቀፍ ደረጃ ወደ አየር ከሚለቀቀው ካርቦን 4 በመቶ ለሚሆነው ብቻ ተጠያቂ ብትሆንም አህጉሪቱ በከፍተኛ ደረጃ ለአየር ጸባይ ለውጥ ተጋላጭ ነች።

ያደጉት ሀገራት የካርቦን ልቀታቸውን የመቀነስ ጉዳይ ለዓመታት እያጨቃጨቃቸው ቢሆንም ለአፍሪካ ግን ጥያቄው ሌላ ነው።

አፍሪካ ትኩረቷን ያደረገችው ከአየር ጸባይ ለውጥ ጋር ተያይዘው ከሚመጡ ተፈጥሮአዊ አደጋዎች ራስን መከላከልና ከለውጡ ጋር ተስማምተው ውጤታማ መሆን የሚችሉ የግብርና ምርቶችን ማግኘት ላይ ነው።

ነገር ግን ይህ ተግባር አፍሪካ ለብቻዋ የምትወጣው ባለመሆኑ ከፍተኛ እርዳታ ያስፈልጋል።

በስፔኗ መዲና ማድሪድ የሚካሄው የተባበሩት መንግሥታት የአየር ጸባይ ለውጥ ላይ ያተኮረ ስብሰባ ከመካሄዱ በፊት ካርቦን የሚለቁ ሀገራት ልቀታቸውን በእቅድ ደረጃ ከተያዘው በአምስት እጥፍ መቀነስ እንዳለባቸው ሳይንቲስቶች አሳስበዋል። ይህ የማይሆን ከሆነ ደግሞ ዓለማችን በቅርቡ ከባድ የሆነ የአየር ጸባይ ለውጥ ያጋጥማታል ብለዋል።

አንድ የተባበሩት መንግሥታት ጥናት እንደጠቆመው በአውሮፓውያኑ 2050 ከሰሀራ በታች ያሉ የአፍሪካ ሀገራት ከአየር ጸባይ ለውጥ ጋር በተያያዘ ለሚያጋጥሟቸው ችግሮች እስከ 50 ቢሊየን ዶላር የሚደርስ ገንዘብ ያስፈልጋቸዋል።

''እኛ አፍሪካውያን የገንዘብ ምንጭ፤ የቴክኖሎጂ ሽግግር እና የአቅም ግንባታ ያስፈልገናል። ይሄ ደግሞ ላደጉት ሀገራት ከባድ የሚባል አይደለም'' ብለዋል ከአፍሪካ ግሩፕ የመጡት ተደራዳሪ ቶሲ ምፓኑ ምፓኑ።

በዓለማችን ካሉ 47 እጅግ ደሀ ሀገራት 33ቱ በአፍሪካ ሲሆን የሚገኙት በአየር ጸባይ ለውጥ ለሚደርስባቸው ጉዳት ከሀብታም ሀገራት የተገባላቸው ገንዘብ እስካሁን በበቂ ሁኔታ አልተሰጣቸውም።

33 ያደጉ ሀገራትን የሚወክለው ኢኮኖሚያዊ ትብብርና ልማት (ኦኢሲዲ) የተባለው ድርጅት በበኩሉ በአየር ጠባይ ለውጥ ለሚጎዱ ሀገራት የሚደረገው ድጋፍ በአውሮፓውያኑ 2013 ከነበረው 37.9 ቢሊየን ዶላር በ 2017 ወደ 54.5 ቢሊየን ዶላር ከፍ ማለቱን ገልጿል።

ውጤታማ ያልሆነ አስተዳደርና ከፍተኛ ሙስና ደግሞ ድጋፎቹ በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዳይውሉ እንዳደረጉ ተገልጿል።

ከሰሞኑ በተለይ ደግሞ በምስራቅ አፍሪካ እየታየ ያለው ከባድ ዝናብ አፍሪካ ምን ያክል እየተጎዳች እንደሆነ ማሳያ ነውም ተብሏል።

ኢትዮጵያን ጨምሮ በምስራቅ አፍሪካ ሀገራት እየጣለ ባለው ከባድ ዝናብ ባስከተለው ጎርፍና የመሬት መንሸራተት በመቶዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ሕይወታቸውን አጥተዋል፤ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ደግሞ ከመኖሪያቸው ተፈናቅለዋል።

ለነዚህ ሁሉ ሚቲዎሮሎጂካል ክስተቶች ምክንያቱ የሕንድ ውቅያኖስ ነው ብለዋል ተመራማሪዎች።

'ሴቭ ዘ ችልድረን' በበኩሉ ተለዋዋጭ የአየር ንብረት በሚሊዮኖች ለሚቆጠሩ አፍሪካውያን ለረሀብ መጋለጥ ምክንያት እንደሆነ ገልጿል።

አክሎም በከባድ አውሎ ነፋስና ድርቅ ምክንያት 33 ሚሊዮን ሰዎች እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ሁኔታ ውስጥ የሚገኙ ሲሆን አስቸኳይ የምግብ እርዳታም ያስፈልጋቸዋል ብሏል።

በሰሞኑ ዝናብ ምክንያትም በአፍሪካ በብዛት ለምግብነት የሚውሉት የስንዴና የበቆሎ ምርቶች ከጥቅም ውጪ ሆነዋል። በተለያዩ ሃይቆች ላይ የሚደረጉ የአሳ ማጥመድ ስራዎችም ተቀዛቅዘዋል፤ የአሳ ምርትም በእጅጉ ቀንሷል።

በማደግ ላይ ያሉ ሀገራትን ወክለው በስብሰባው የሚካፈሉ ተደራዳሪዎች እንደገለጹት ከአየር ጸባይ ለውጥ ጋር ተያይዞ ለሀገራት የሚሰጠው ድጋፍ እዚህ ግባ የሚባል ባለመሆኑ ያደጉት ሀገራት ትኩረታቸውን ወደ አፍሪካ ማድረግ አለባቸው ብለዋል።

የአፍሪካ ተደራዳሪዎች በማድሪዱ ስብሰባ ከፍተኛ ድጋፍ ለማግኘትና የካርቦን ልቀትን ለማስቀነስ እየጣሩ ቢሆንም አስደሳች የሚባል ለውጥ እንዳልተገኘ ግን እየተገለጸ ነው።