በሕንድ ከእነ ነፍሷ ተቀብራ የተገኘችው ጨቅላ ሙሉ በሙሉ አገገመች

ታትሟል

በህይወት ሳለች ሸክላ ውስጥ ተደርጋ ተቀብራ የተገኘችው ጨቅላ ሙሉ በሙሉ ማገገሟን ሐኪሟ አስታወቁ።

ከሁለት ሳምንት በፊት ነበር ጨቅላዋ ከእነ ህይወቷ ሸክላ ውስጥ ተደርጋ ተቀብራ ከተገኘች በኋላ ወደ ሆስፒታል የተወሰደችው።

ጨቅላዋ ሆስፒታል ስትደርስ በደሟ ውስጥ ከፍተኛ መጠን ያለው ባክቴሪያ በመኖሩ ህይወቷ አጣብቂኝ ውስጥ እንደነበረ ሐኪሟ ተናግረዋል።

የህጻናት ሃኪሙ ራቪ ካህና ጨቅላዋ በአሁኑ ሰዓት የክብደት መጠኗ እና አተነፋፈሷ መስተካከሉን አስረድተዋል።

የወላጆቿ ማንነት እስካሁን ያልታወቀ ሲሆን፤ የጤናዋ ሁኔታ አስተማማኝ ደረጃ ላይ ሲደርስ ለማደጎ ልትሰጥ እንደምትችል ተጠቁሟል።

በወቅቱ አበሂናንዳን ሲንጋህ የተባሉ የፖሊስ ኃላፊ ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት፤ ጨቅላዋ የተገኘችው አንድ የአከባቢው ነዋሪዎች እንደተወለደች የሞተች ጨቅላን ለመቅበር እየቆፈሩ ሳሉ የህጻን የለቅሶ ድምጽ ከሰሙ በኋላ ነበር።

ፖሊስ እንዳለው ጨቅላዋ 90 ሴንቲ ሜትር ጥልቀት ባለው ጉድጓድ ሸክላ ውስጥ ተደርጋ ነበር የተቀበረችው።

ሐኪሞች ጨቅላዋ ግዜዋ ሳይደርስ በ30ኛው ሳምንት እንደተወለደች እና ወደ ሆስፒታል ስትመጣ 1.1 ኪ.ግ ብቻ እንደምትመዝን ተናግረዋል።

ከሁለት ሳምንታት የህክምና ክትትል በኋላ ጨቅላዋ በአሁኑ ሰዓት 2.7 ኪ.ግ እንደምትመዝን እና ፈሳሽ ነገር እየወሰደች እንደሆነ ሐኪሞች አስታውቀዋል።

ጨቅላዋ በሸክላው ውስጥ ከሶስት እስከ አራት ለሚሆኑ ቀናት ተቀብራ ሳትቆይ እንዳልቀረች ሐኪሙ ዶ/ር ካሃን ግምታቸውን ያስቀምጣሉ። "ህጻናት ሲወለዱ በውስጣቸው ስብ ይዘው ነው። ይህም በአደጋ ግዜ ህይወታቸውን ለማቆየት ይረዳቸዋል" ይላሉ ዶ/ር ካሃን።

ሌሎች ባለሙያዎች ግን ከዶ/ር ካሃን በተለየ መልኩ ጨቅላዋ በዛ ሁኔታ ውስጥ ተቀብራ የቆየችው ግፋ ቢል ከሶስት እስከ አራት ሰዓታት ብቻ ነው ይላሉ።

ጨቅላዋ የተቀበረችበት ሸክላ ክፍተት ስለነበረው እና አፈሩ በኃይል ስላልተደለደለ አየር ይደርሳት ነበር ተብሏል።

ፖሊስ ጨቅላዋን የጣሉት ማንነታቸው ያልታወቁ ግለሰቦች ላይ የወንጀል ምረመራ ጀምሯል። ፖሊስ ይህን ወንጀል የፈጸሙት የህጻኗ ወላጆች ሳይሆን አይቀርም ብሏል።

የፖሊስ ጥርጣሬን ያጠናከረው ደግሞ የጨቅላዋ ወላጅ እኔ ነኝ ብሎ የመጣ ጠያቂ ሰው ባለመኖሩ ነው።