ዩሮ 2020፡ እነማን አለፉ? እነማንስ አልተሳካላቸውም?

የአውሮፓ እግር ኳስ ዋንጫ 24 ቡድኖች ይሳተፉበታል። 17 ቡድኖች ማለፋቸውን አረጋግጠዋል። 7 አገራት ለተቀረው ኮታ ይፋለማሉ።
እንግሊዝ ሐሙስ ምሽት ያደረገችውን ጨዋታ 7 ለምንም በማሸነፍ ማለፏን አረጋግጣለች። ዌልስ እና አየርላንድ ሪፐብሊክ ከምድባቸው ሁለተኛ ሆነው ለማለፍ እየተፋለሙ ነው።
ስኮትላነድና ሰሜን አየርላንድ መጋቢት ላይ በሚካሄደው የጥሎ ማለፍ ውድድር ይሳተፋሉ።
ያለፉ አገራት
ኦስትሪያ፣ ቤልጂዬም፣ ክሮኤሽያ፣ ቼክ ሪፐብሊክ፣ እንግሊዝ፣ ፊንላንድ፣ ፈረንሳይ፣ ጀርመን፣ ጣልያን፣ ኔዘርላንድስ፣ ፖላንድ፣ ፖርቹጋል፣ ሩስያ፣ ስፔን፣ ስዊድን፣ ቱርክ እና ዩክሬን ማለፋቸውን ያረጋገጡ ሃገራት ናቸው።
ዴንማርክ፣ ሃንጋሪ እና ስዊትዘርላንድ ደግሞ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ያሉ ናቸው። ስሎቫኪያ፣ ዌልስ እና የአየርላንድ ሪፐብሊክ የማለፍ ዕድል ያላቸው አገራት ናቸው።
የአውሮፓ ዋንጫ የምድብ ድልድል በያዝነው ወር መገባደጃ ላይ ይወጣል። ስድስት አገራት የቡድን አባት ይሆናሉ። እንግሊዝ፣ ቤልጂዬም፣ ጣልያንና እና ዩክሬን አራቱ የምድብ አባት መሆናቸውን ያረጋገጡ አገራት ናቸው።
ከጀርመን፣ ስፔን እና ፈረንሳይ መካከል አንድ ቡድን ብቻ የቡድን አባት የመሆን ዕድል አለው። የአውⶂፓ ዋንጫ ባለድል ፖርቹጋል የቡድን አባት የመሆን ዕድል የለውም።
ዛሬም የሚቀጥለው የአውሮፓ ዋንጫ ማጣሪያ ጨዋታ እነማን ሊያልፉ እንደሚችሉ ፍንጭ ይሰጣል።
ከምድብ 'ሀ' እንግሊዝና ቼክ ሪፐብሊክ ማለፋቸውን ያረጋገጡ አገራት ናቸው። ከምድብ 'ለ' ደግሞ ዩክሬንና ፖርቹጋል። ምድብ 'ሐ' ጀርመንና ኔዘርላንድስ ማለፋቸው ቢታወቅም ሦስተኛ ላይ ያሉት ሰሜን አየርላንዶች ቀጣይ መጋቢት በሚካሄደው ጥሎ ማለፍ በመሳተፍ ተሳታፊነታቸውን ማረጋገጥ አለባቸው።
ምድብ 'መ' ማን ይለፍ ማን ውሉ ያልታወቀበት ምድብ ነው። ከአንድ እስከ ሦስተኛ ደረጃ የሚገኙት ዴንማርክ፣ ስዊትዘርላንድ እና የአየርላንድ ሪፐብሊክ የማለፍ ዕድል አላቸው። ሁለት አገራት ማለፋቸው ከለየ ሦስተኛው ሃገር ወደ ጥሎ ማለፍ ይሄዳል።
ምድብ 'ሠ' ስፔንና ስዊድን ቲኬታቸውን ቆርጠዋል። ምድብ 'ረ' በተመሳሳይ ሁለት ቡድኖች ብቻ አልፈዋል፤ ፖላንድና ኦስትሪያ። የምድብ 'ሸ' መሪ ፈረንሳይ ቱርክን አስከትላ አልፋለች።
ሦስተኛ ደረጃ ላይ ያለችው አይስላንድ የጥሎ ማለፍ ተፎካካሪ ትሆናለች። ምድብ 'ቀ' ቤልጂዬም እና ሩስያ ተያይዘው ሲያልፉ ስኮትላንድ የጥሎ ማለፍ አድማቂ እንደምትሆን ይገመታል። የመጨረሻው ምድብ 'በ' ጣልያንና ፊንላንድ አልፈዋል።
ዛሬ የአየርላንድ ሪፐብሊክ ከዴንማርክ የሚያደርጉት ጨዋታ ከሌላው በበለጥ በጉጉት ይጠበቃል። ነገ ደግሞ የዌልስና ሃንጋሪ ጨዋታ ተጠባቂ ነው።













