አወዛጋቢው የቀድሞ መከላከያ ሚኒስትር የሲሪላንካ ፕሬዝዳንት ሆነው ተመረጡ

ታትሟል

የዘር መከፋፈል እጅጉን ጉልህ በሆነባት ሲሪላንካ ፕሬዘዳንታዊ ምርጫ የቀድሞ የአገሪቱ መከላከያ ሚኒስትር ጎታባያ ራጃፓክሳ 50.25 በመቶ ድምፅ በማግኘት አሸናፊ ሆኑ።

ተቀናቃኛቸው ሳጂዝ ፕሪማዳስም ሽንፈታቸውን አምነው ተቀብለዋል።

ድል የቀናቸው ራጃፓክሳ ከፍተኛ ድምፅ ያገኙት ሲናሊዝዎች በሚበዙበት አካባቢ ሲሆን ተቀናቃኛቸው ፕሪማዳስ ደግሞ ታሚሎች አብላጫ በሆኑበት በሰሜናዊ ሲሪላንካ ነው አብዛኛውን ድምፅ ያገኙት።

በያዘነው ዓመት [2019] ዓመት መጀመሪያ ላይ በሲሪላንካ ከአይ ኤስ ጋር ግንኙነት አላቸው የተባሉ ታጣቂዎች ቤተክርስቲያኖች እና ስመ ጥር ሆቴሎች ላይ ከፍተኛ ጥቃት ሰንዝረው ከ250 ሰዎች በላይ መግደላቸው ይታወሳል።

ስለዚህም ብሄራዊ ደህንነትን ማረጋገጥ የሲሪላንካ ፖለቲካዊ ሁለንተና ሆኗል።

አሁን በምርጫው አሸናፊ የሆኑት የአገሪቱ የቀድሞ መከላከያ ሚኒስትር ደግሞ ራሳቸውን ለዚህ ትክክለኛው ሰው አድርገው አቅርበው ተሳክቶላቸዋል። ቢሆንም ግን እኚህ ሰው ሁለት ሚኒሊዮን በሚበልጠው የአገሬው ታሚል ህዝብ እይታ አወዛጋቢ የሚባሉ ናቸው።

እሳቸውና የአገሪቱ የቀድሞ ፕሬዝዳንት የነበሩት ወንድማቸው ማሂንዳ ራጃፓስካ እንደ አውሮፓውያኑ አቆጣጠር በ2009 በታሚል ታይገር አማፅያን ላይ የተደረገውን ጦርነት የመሩ ሰዎች ናቸው።

ያም ለአስርታት ከታሚል ታይገር ጋር የተደረገው ጦርነት ማብቂያና የታሚል ታይገር ፍፃሜም ሆኗል።