በእንግሊዝ የ39 የሰዎች አስክሬን 'ኮንቴይነር' ውስጥ ተገኘ

ታትሟል

በደቡብ ምስራቅ እንግሊዝ ኢሴክስ በምትባል ከተማ የ39 ሰዎች አስክሬን 'ኮንቴይነር ውስጥ ተገኘ።

'ወተርግሌድ ኢንደስትሪያል ፓርክ' በሚባለው አካባቢ የሰዎቹ አስክሬን በመታየቱ ፖሊስ የተጠራ ሲሆን ፖሊስ በበኩሉ ጉዳዩን እያጣራሁ ነው ብሏል።

ከጉዳዩ ጋር በተያያዘም የ25 ዓመቱ የመኪናው አሽከርካሪ በቁጥጥር ሥር መዋሉ ታውቋል። የኢሴክስ ከተማ ፖሊስ እንዳስታወቀው ተሽከርካሪው ከቡልጋሪያ ተነስቶ በ 'ሆሊሄድ' በኩል እንግሊዝ ገብቷል።

እስካሁን በተገኘው መረጃ መሠረት 38 ጎልማሶችና አንድ በአስራዎቹ እድሜ ክልል ውስጥ የሚገኝ ታዳጊ ሬሳዎች ተገኝተዋል። የሟቾችን ማንነት ለመለየትም ረጅም ጊዜ የሚፈጅ ምርመራ እየተካሄደ ነው።

''የከባድ መኪናውን ተሽከርካሪ በቁጥጥር ሥር አውለነዋል። አሁንም ነገሮች እሰከሚጣሩ ድረስ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ይቆያል፤ ምርመራችንም የሚቀጥል ነው'' ብለዋል የከተማዋ የፖሊስ ኃላፊ።

ጠቅላይ ሚኒስትር ቦሪስ ጆንሰን በበኩላቸው በተፈጠረው አሳዛኝ ሁኔታ መደንገጣቸውን ገልጸዋል።

''ስለጉዳዩ ተከታታይ መረጃ እየደረሰኝ ነው፤ ቢሮዬም ከኢሴክስ ፖሊስ ጋር በመተባበር በትክክል ምን እንደተፈጠረ ለማጣራት እንሰራለን። በዚሁ አሳዛኝ አጋጣሚ ቤተሰባቸውንና የሚወዷቸውን ሰዎች ላጡ አብረናችሁ ነን ለማለት እፈልጋለሁ። '' ብለዋል።

ከዚህ በፊት እ.አ.አ. በ2000 58 ቻይናውያን ስደተኞች በተመሳሳይ መኪና ተጭነው አስክሬናቸው ተገኝቶ ነበር። የመኪናው አሽከርካሪ ነው የተባለ የኔዘርላንድስ ዜግነት ያለው ግለሰብም ታስሮ ነበር።