አውስትራሊያዊው 20 ካንጋሮዎችን በመኪና ገጭቶ በመግደሉ ተከሰሰ

ታትሟል

የ19 ዓመቱ አውስትራሊያዊ በሚያሽከረክረው መኪና 20 ካንጋሮዎችን ገጭቶ ግድሏል ተብሎ በፖሊስ ቁጥጥር ሥር ዋለ።

እሁድ ዕለት ከሲድኒ ከተማ በስተደቡብ በሚገኝ ከከተማ ወጣ ብሎ ባለ መንገድ ላይ ነው ትናንሽ ካንጋሮዎችን ጨምሮ 20ዎቹ በመኪና ተገጭተው ሞተው የተገኙት።

በካንካሮዎቹ ላይ ጥቃቱ የተፈጸመው በምሽት ላይ በአንድ ሰዓት ጊዜ ውስጥ እንደሆነ ፖሊስ ጥርጣሬውን ገልጿል።

በመኪና ካንጋሮዎቹን ገድሏል ተብሎ የተጠረጠረው ወጣትም ከድርጊቱ ከቀናት በኋላ ተይዞ በበርካታ እንስሳት ላይ በተፈጸመ የጭካኔ ድረጊት ክስ ተመስርቶበታል።

በአውስትራሊያዋ የኒውሳወዝ ዌልስ ሕግ መሠረት በእንስሳት ላይ በሚፈጸም የጭካኔ ተግባር የተከሰሰ ግለሰብ እስከ አምስት ዓመት በሚደርስ እስራትና የ15 ሺህ ዶላር ቅጣት ይጣልበታል።

ከሲድኒ 540 ኪሎ ሜትሮች ርቀት ላይ በሚገኘው ሥፍራ ላይ የተፈጸመውን ድርጊት የዱር እንስሳት ተንከባካቢዎች "አሰቃቂ" ሲሉ ገልጸውታል። ጨምረውም አንዳንድ የአካባቢው ነዋሪዎችም በጠዋት ሲነቁ በአካባቢያቸው የሞቱ ካንጋሮዎችን አግኝተዋል ብለዋል።

"ድርጊቱ ግልጽ የጭካኔ ጭፍጨፋ ነው" ሲሉ ጄን ጊብሰን ለአውስትራሊያ ዜና ማሠራጫ ተቋም ተናግረዋል።

በካንጋሮዎች ላይ ከተፈጸመው ከዚህ ጥቃት በእናታቸው ማቀፊያ ውስጥ የነበሩ ሦስት ትንንሽ ካንጋሮዎች በሕይወት መትረፋቸውም ተነግሯል።

ጥቃቱን ፈጽሟል ተብሎ የተጠረጠረው ግለሰብም በቀጣዩ ኅዳር ፍርድ ቤት ይቀርባል ተብሏል።

ባለፉት ሁለት የፈረንጆች ዓመታት በአውስትራሊያ ውስጥ ከ57 ሺህ የሚበልጡ በእንስሳት ላይ የተፈጸሙ የጭካኔ ተግባራት የሚጠቁሙ ቅሬታዎች መመዝገባቸውን ለእንስሳት ደህንነት የሚሰራ አንድ ተቋም ያወጣው መረጃ አመልክቷል።