ናይሮቢ ውስጥ የመማሪያ ክፍል ተደርምሶ 7 ተማሪዎች ሞቱ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 1 ደቂቃ

በኬንያዋ መዲና ናይሮቢ ውስጥ የሚገኝ አንድ ትምህርት ቤት ዛሬ ጠዋት ተደርምሶ ሰባት ህፃናት በአደጋው ሕይወታቸው እንዳለፈ ባለሥልጣናት ተናገሩ።

የኬንያ ቀይ መስቀል እንዳለው በዋና ከተማዋ ዳርቻ ላይ በሚገኝ ትምህርት ቤት ላይ ነው በሳምንቱ የመጀመሪያ የትምህርት ቀን አደጋው የደረሰው።

በአደጋው ቁጥራቸው በውል ያልታወቁ ተማሪዎች በፍርስራሾች ውስጥ ተቀብረው እንደሚገኙ የተነገረ ሲሆን የአደጋ ጊዜ ነፍስ አድን ሠራተኞች በአደጋው ስፍራ ላይ መሰማራታቸውም ተነግሯል።

ፕሬሺየስ ታለንት ቶፕ በተባለው በዚህ ትምህርት ቤት ላይ የደረሰው አደጋ የተከሰተው ተማሪዎች የእለቱን ትምህርት ለመጀመር ወደ መማሪያ ክፍላቸው ከገቡ ከጥቂት ደቂቃዎች በኋላ ነው።

በአደጋው ጉዳት የደረሰባቸው ተማሪዎች በከተማዋ ውስጥ ወደሚገኘው የኬንያታ ብሔራዊ ሆስፒታል መወሰዳቸውን የሃገሪቱ ቀይ መስቀል ገልጿል።

አደጋው ያጋጠመው ጠዋት አንድ ሰዓት ከመሆኑ ጥቂት ቀደም ብሎ መሆኑ የተነገረ ሲሆን በወቅቱ እርዳታ ለመስጠት ቀድመው የደረሱት በአካባቢው የሚገኙ ነዋሪዎች ናቸው ተብሏል።

ከትምህርት ቤቱ አቅራቢያ የሚኖሩ ሰዎች እንደተናገሩት ተማሪዎቹን ከፍርስራሾች ስር የማውጣቱ ሥራ አሁንም የቀጠለ ሲሆን በክስተቱ የተቆጡ ነዋሪዎችም የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በስፍራው ለመድረስ መዘግየታቸውን አማረው ተናግረዋል።

ስምንት መቶ ተማሪዎች ያሉት የዚህ የትምህርት ቤት ርዕሰ መምህር ሞሰስ ንዲራንጉ ለአደጋው መከሰት በትምህርት ቤቱ አቅራቢያ እየተገነባ ያለው የፍሳሽ መስመር የሕንፃውን መሠረት አዳክሞት ሊሆን እንደሚችል ተናግረዋል።