82 ስደተኞች በደቡባዊ ጣልያን ላምፔዱሳ ደሴት ደረሱ

ታትሟል

በባህር ላይ ለስድስት ቀናት ሲጓዙ የነበሩ 82 ስደተኞች ደቡባዊ ጣልያን ላምፔዱሳ ደሴት ደረሱ።

ጣልያን ስደተኞቹን ይዛ የመጣችውን መርከብ ወደ ድንበሯ እንድትገባ የምትፈቅድ መሆኑን በመግለጽ ስደተኞቹ ከመርከቧ ከወረዱ በኋላ ወደ ተለያዩ የአውሮፓ ሃገራት እንዲዘዋወሩ እንደሚደረግ አስታውቃለች።

ውሳኔው በጣልያን በቅርቡ ስልጣን የያዘው የጥምረት ቡድን ለስደተኞች ያለውን የተሻለ አመለካከት የሚያሳይ ነውም ተብሎለታል።

የቀድሞው የሀገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትሩ ማቴዎ ሳልቪኒ ማንኛውም ስደተኞችን ጭኖ የሚመጣ መርከብም ሆነ ጀልባ ወደ ጣልያን እንዳይገባ በመከልከል ነበር የሚታወቁት።

የጣልያኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሉዊጂ ዲ ማቲዮ ለአንድ የሃገሪቱ ቴሌቪዥን እንደተናገሩት ''ደህንነቱ የተጠበቀው የባህር መንገድ በእኛ በኩል እንዲሆን ያደረግነው ከአውሮፓ ህብረት ጋር በደረስነው ስምምነት ሲሆን አብዛኛዎቹን ስደተኞችም የምንቀበል ይሆናል'' ብለዋል።

የጀርመኑ የሃገር ውስጥ ጉዳዮች ሚኒስትሩ ሆርስት ሲሆፈር በበኩላቸው ወደፊት በሚደረጉ ስምምቶች መሰረት ሃገራቸው ጣልያን ከሚደርሱ ስደተኞች 25 በመቶ የሚሆኑት እንደምትቀበል አስታውቀዋል።

አክለውም ''እጅግ አስከፊ'' ያሉትን የስደት ጉዞ ለማስቀረት ጊዜው አሁን ነው ብለዋል።

ከ82ቱ ስደተኞች መካከል ደግሞ ፈረንሳይና ጀርመን እያንዳንዳቸው አንድ አራተኛ የሚሆኑትን ለመቀበል መስማማታቸውን ኤኤፍፒ ዜና ወኪል ዘግቧል።

በደቡባዊ ጣልያን ላምፔዱሳ ደሴት ከደረሱት ስደተኞች መካከል 58ቱ ወንዶች ሲሆኑ ስድስቱ ሴቶች እንዲሁም 18 የሚሆኑት ደግሞ ታዳጊዎች መሆናቸው ታውቋል።