ሞተዋል የተባሉት የቱርከሜንስታን ፕሬዝደንት ብሬድይሙክሃሜዶቭ በአደባባይ ታዩ

ታትሟል
የንባብ ጊዜ: 1 ደቂቃ

የቱርከሜንስታን ፕሬዝደንት ጉርባንጉለይ የመሞታቸው ዜና በስፋት ከተናፈሰ በኋላ ዛሬ በቴሌቪዥን መስኮት ብቅ ብለዋል።

ፕሬዝደንቱ ዛሬ ጠዋት በቴሌቪዥን ብቅ ያሉት በሃገራቸው እየተካሄደ የሚገኘውን የምጣኔ ሃብት ፎረም በይፋ በከፈቱበት ወቅት ነበር።

ባለፉት አራት ሳምንታት ሃገር ውስጥ እና መቀመጫቸውን ውጪ ያደረጉ የተቃዋሚ መገናኛ ብዙሃን ፕሬዝደንቱ በኩላሊት ህመም ምክንያት ህይወታቸው ማለፉን በስፋት ሲዘግቡ ነበር።

ብሔራዊው የቴሌቪዥን ጣቢያ በበኩሉ ዘገባዎቹ ውሸት መሆናቸውን ለማስተባበል የፕሬዝደንቱን ምሰል ደጋግሞ ቢያሳይም፤ ምስሎቹ መች እንደተቀረጹ ማወቅ ባለመቻሉ በህዝቡ ዘንድ ከፍተኛ ጥርጣሬን ፈጥሮ ነበር።

ይሁን እንጂ የመሞታቸው ዜና በስፋት የተናፈሰባቸው ፕሬዝደንት ዛሬ ጠዋት በሃገራቸው እየተካሄደ የሚገኘውን የምጣኔ ሃብት ፎረም በይፋ ሲከፍቱ የሩሲያ፣ አዘርባጃን፣ ካዛኪስታን እና የኢራን መሪዎችን የእንኳን ደህና መጣችሁ ብለዋል።

ፕሬዝደንቱ ሞተዋል ሲል በቅድሚያ የዘገበው ከሃገር ውጪ የሚገኝ አነስተኛ የዜና ወኪል ነበር። ከዚያም ይህ ያልተጣራ ሪፖርት በሩሲያ ቋንቋ በሚዘግቡ መገናኛ ብዙሃን ሰፊ ትኩረትን በማግኘቱ የፕሬዝደንቱ መሞት በስፋት ተዘገበ።

በማህብራዊ ሚደያዎችም የመሞታቸው ዜና በስፋት ተሰራጭቶ ነበር።

የቱርኬሚስታን ብሔራዊ ቴሌቪዥን ጣቢያ ዜናውን ለማስተባበል ፕሬዝደንቱ ፈረስ ሲጋልቡ እና መኪና ሲያሽከረክሩ የሚያሳይ ምስል ቢያስመለክትም፤ ምስሉ መች እንደተቀረጽ ማወቅ ባለመቻሉ ከፍተኛ ጥርጣሬን ፈጥሮ ነበር።

ቱርኬሚስታን በዓለማችን የመረጃ ነጻነት ከሌለባቸው ሃገራት መካከል አንዷ ናት። 'ሪፖርተርስ ዊዝአውት ቦርደርስ' የተሰኘው ቡደን ቱርኬሚስታን ከሰሜን ኮሪያ በመቀጠል የመረጃ ነጻነት የሌለባት ሃገር ሲል ይፈርጃታል።