ኬኒያ፡ "ምክር ቤቱ የህፃናት ማቆያ አልነበረውም" የተባረሩት የፓርላማ አባል

የፎቶው ባለመብት, Chris Thairu
ኬኒያ ውስጥ ረቡዕ ዕለት ጨቅላ ልጃቸውን የሕዝብ እንደራሴ ምክር ቤት አቅፈው በመምጣታቸው ከምክር ቤት እንዲወጡ የተደረጉት የፓርላማ አባል ምክር ቤቱ ሕፃናት ማቆያ አለው መባሉን አስተባበሉ።
ዙሌካ ሐሰን ከምክር ቤቱ እንዲወጡ ከተደረገ በኋላ ምክትል አፈጉባዔው ምክር ቤቱ ጨቅላ ህፃናት ላላቸው አባላት ማቆያና መንከባከቢያ የሚሆን ማቆያ እንዳለ ገልጠው ነበር።
አለ የተባለውን ሥፍራ የምክር ቤት አባሏ ከጎበኙ በኋላ "ይህ ቦታ ከዚህ ቀደም እንዳልነበረ አረጋግጥላችኋለሁ" ሲሉ ለቢቢሲ ገልፀዋል።
"አንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት ይህ የህፃናት ማቆያ ከዚህ ቀደም ነበር በማለት ሊያዋርዱኝ እንደሞከሩ አውቃለሁ። ከነበረ ግን እንዴት እኔ ሳላውቅ ቀረሁ?" ሲሉ የፈጠረባቸውን ግርምት ተናግረዋል።
እርሳቸው ከምክር ቤቱ እንዲወጡ ከተደረገ በኋላ ማቆያው በፍጥነት እንደተመቻቸና እንዲሟላ መደረጉን ይናገራሉ።
"በማቆያው ያሉት ቁሳቁሶች እጅግ በጣም አዲስ መሆናቸውን ማየት ይቻላል። የእቃዎቹ ሽታ ገና ከማሸጊያቸው እንደወጡ መሆኑን ያሳብቃል። ከዚህ በፊት በእጅ ያልተነኩ ወይም ጥቅም ላይ ያልዋሉ እንደነበሩ መመስከር ቀላል ነው" ሲሉ ገልጠዋል።
ከረፈደ በኋላም ቢሆን እንኳ ለእርሳቸውና ለባልደረቦቻቸው መሟላቱ እንዳስደሰታቸው ግን አልሸሸጉም።
"አሁን ለአንድ ወር ያህል እረፍት ላይ ነን፤ ከእረፍት ስንመለስ ግን ልጄን ይዤ ለመምጣት ደስተኛ ነኝ" ሲሉም አክለዋል።
የምክር ቤት አባሏ የአምስት ወር ጨቅላ ልጃቸውን ወደ ምክር ቤቱ ስብሰባ ይዘው ለመምጣት የተገደዱት ቤት ውስጥ ማቆየት ስላልቻሉና ምክርቤቱም የህፃናት ማቆያ ስለሌለው መሆኑን ተናግረው ነበር።
በዚህም የተነሳ በምክር ቤት ውስጥ የምክር ቤቱ ወንድ አባላት የጮሁባቸው ሲሆን ድርጊታቸውንም አሳፋሪ ሲሉ ገልፀውት ነበር።
በ2017 የኬኒያ ሕግ አውጪዎች፤ ቀጣሪዎች ለሠራኞቻቸው ጨቅላ ህፃናቶቻቸውን ጡት የሚያጠቡበትና የሚንከባከቡበት ክፍል እንዲገነቡ የሚያስገድድ ሕግ አውጥተው ነበር።















