ብሩንዲ፡ የ6 ዓመቱ የዩቲዩብ ኮከብ ኮሜዲያን በወባ በሽታ ሞተ

የፎቶው ባለመብት, Facebook/Kacaman
በብሩንዲ በዩቲዩቡ በሚያቀርባቸው የኮሜዲ ሥራዎቹ የሚታወቀው የ6 ዓመቱ ህፃን በወባ በሽታ ሕይወቱ ማለፉን ሥራ አስኪያጁ ገለፁ።
ካካማን በሚል ስም የሚታወቀው ህፃን ዳርሲይ ኢራኮዜ በኢንተርኔትና በቲያትር ቤቶች በሚያቀርባቸው ኮሜዲ ሥራዎቹ ይታወቃል።
ህፃኑ ባለፈው ረቡዕ ባጋጠመው የወባ ህመም በሕክምና ሲረዳ ቆይቶ በማግስቱ ሕይወቱ ማለፉ ተገልጿል።
ዳርሲይ ከታዋቂው ብሩንዲያዊው ኮሜዲያን ኪጊንጊ ጋር ባለፈው ነሐሴ ወር መጀመሪያ ላይ ለመጨረሻ ጊዜ እንደተወነ ተነግሯል። ከጊኪንጊ ጋር በድጋሜ የኮሜዲ ሥራዎችን ለማቅረብም እቅድ ይዞ እንደነበር ተገልጿል።
ኪኪንጊ ለቢቢሲ እንደገለፀው የህፃኑ ሞት ለእርሱና ለብሩንዲ የመዝናኛ ኢንዱስትሪ ትልቅ ኪሳራ ነው ብሏል።
የዳርሲይንን ሞት ተከትሎ በብሩንዲ ያለው ከፍተኛ ቁጥር ያለው የወባ በሽታ ህሙማን በባለስልጣናት ዘንድ መነጋጋሪያ ሆኗል።
እንደ የዓለም አቀፉ ጤና ድርጅት መረጃ ከሆነ ከባለፈው ጥር ወር ጀምሮ በብሩንዲ ከአምስት ሚሊየን በላይ የወባ ታማሚዎች የተመዘገቡ ሲሆን በዚህ ዓመት ብቻ ከ1800 በላይ የሚሆኑት በበሽታው ሕይወታቸው አልፏል።
የወባ በሽታ በአፍሪካ ገዳይ ከሆኑ በሽታዎች አንዱ ሲሆን በየቀኑ ከ2500 በላይ ለሚሆኑ ሕፃናት ሞት ምክንያት እንደሆነም የተባበሩት መንግሥታት ኤጀንሲ (ዩኒሴፍ) አስታውቋል።
የዓለም የጤና ድርጅት አክሎም በብሩንዲ በወባ በሽታ የሚሞቱት ሰዎች ቁጥር በዲሞክራቲክ ኮንጎ በኢቦላ ከሚሞቱት ቁጥር ጋር ይስተካከላል ብሏል።
የአገሪቱ የጤና ጥበቃ ሚንስትር ታዴ ዲኩማና ለጋዜጠኞች እንደተናገሩት በዓመት 4.3 ሚሊየን ሕሙማን የተመዘገቡ ሲሆን ከዚህ መካከል የሟቾች ቁጥር 1400 ነው ብለዋል።
ቁጥሩ እየቀነሰ ሲሆን ከሁለት ዓመት በፊት 4.9 ሚሊየን ሰዎች በወባ የተያዙ ሲሆን የሟቾቹ ቁጥርም 4300 ነበር ሲሉ ሚንስትሩ አስታውሰዋል።
የዓለም ጤና ድርጅት ከሁለት ዓመት በፊት፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ 220 ሚሊየን የሚጠጉ በወባ የተያዙ ሰዎች መመዝገባቸውንና 435 ሺህ ሞት ተመዝግቧል ብሎ ነበር።
ከእነዚህ መካከል 90 በመቶ የሚሆነው ሞትና ህመም የተመዘገበው በአፍሪካ ነው።














