የአሜሪካ ጣልቃ መግባት ሦስተኛውን የዓለም ጦርነት ይቀሰቅሳል፡ ባይደን

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አገራቸው ዩክሬንን ለመከላከል ሠራዊቷን የምታሰማራ ከሆነ ሦስተኛው የዓለም ጦርነትን ሊያስከትል እንደሚችል አስጠነቀቁ። ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት በዚህም ምክንያት አሜሪካ ወታደሮቿን ወደ ዩክሬን እንደማትልክ አስረግጠው ገልጸዋል።

የቀጥታ ሽፋን

  1. ሁለት ሚሊዮን ሰዎች ከዩክሬን መሰደዳቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት አስታወቀ

    ሁለት ሳምንት ሊሞላው በተቃረበው የዩክሬን- ሩሲያ ጦርነት ሳቢያ ከዩክሬን የተሰደዱ ሰዎች ቁጥር ከሁለት ሚሊዮን መብለጡን የመንግሥታቱ ድርጅት ለቢቢሲ ገለጸ።

    ነገ ረቡዕ ሁለተኛ ሳምንቱን የሚደፍነው ሩሲያ በዩክሬን ላይ የከፈተችው ወረራ ከባድ ሰብአዊ ቀውስን አስከትሎ ሚሊዮኖች መኖሪያቸውን ጥለው እንዲሰደዱ ማድረጉ ተዘግቧል።

    የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የስደተኞች ጉዳይ ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዴ ይህ ከጦርነቱ መቀስቀስ በኋላ የታየው የሰዎች ስደት እጅግ ከፍተኛ መሆኑን ገልጸዋል።

    ይህ በሁለት ሳምንት ውስጥ የታየው የዩክሬናውያን ስደት በከፍተኛ መጠን እየጨመረ ሲሆን ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በአውሮፓ ውስጥ የታየ ግዙፍ መፈናቀል መሆኑን አመልክተዋል።

    በምሥራቅ በኩል የሚካሄደውን ጦርነት በመሸሽ ከዩክሬን የሚሰደዱት ሰዎች በስተምዕራብ ወደ ሚገኙት ፖላንድ፣ ሩሜኒያ፣ ስሎቫኪያ፣ ሃንጋሪ እና ሞልዶቫን ወደ መሳሰሉ የፈለሱ ሲሆን፣ የተወሰነ ቁጥር ያላቸው ስደተኞች ወደ ሩሲያና ቤላሩስ መግባታቸው ተነግሯል።

    በተባበሩት መንግሥታት መረጃ መሠረት አስካሁን ከዩክሬን የሄዱ ስደተኞችን እያስተናገዱ ያሉት አገራት የሚከተሉት ናቸው፡

    • ፖላንድ = ከ1,204,000 በላይ

    • ሃንጋሪ = 191,000

    • ስሎቫኪያ = 141,000

    • ሞልዶቫ = 83,000

    • ሩሜኒያ = 82,000

    • ሩሲያ = 99,300

    • ቤላሩስ = 453

    ሲሆኑ ከእነዚህ ባሻገር ደግሞ ከ83,000 በላይ ሰዎች ከዩክሬን ወጥተው ወደ ሌሎች የአውሮፓ አገራት መሸጋገራቸውን የመንግሥታቱ ድርጅት አመልክቷል።

  2. በሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት 13ኛ ቀን የተዘገቡ ዋነኛ ነገሮች

    ሩሲያ ዩክሬንን ከወረረች ዛሬ ማክሰኞ 13ኛ ቀኑ ነው። በዛሬው ዕለት ጦርነቱን በተመለከተ የተከሰቱ ዋና ዋና ነገሮች እነሆ።

    • ከሁለት ሚሊዮን በላይ ሰዎች ጦርነቱን በመሸሽ ከዩክሬን መሰደዳቸውን የተባበሩት መንግሥታት አስታወቀ።
    • ባለሥልጣናት ሰኞ ዕለት በተፈጸመ የአየር ጥቃት 21 ሰዎች ተገድለውባቸዋል ከተባሉት ኢርፒን እና ዩሚ ነዋሪዎች በተመቻቸላቸው የማለፊያ መስመር ለቀው እየወጡ ናቸው።
    • የዩክሬን ባለሥልጣናት በከበባ ስር ካለችው ደቡባዊቷ የማሪዎፖል ከተማ ነዋሪዎች በሚወጡባቸው መተላላፊያ መስመሮች ላይ የሩሲያ ኃይሎች የከባድ ጥቃት እየፈጸሙ ነው ሲሉ ከሰሱ።
    • ሩሲያ በምዕራባዊያን ለሚጣልባት ማዕቀብ ምላሽ ለአውሮፓ የምትልከውን የጋዝ አቅርቦት እንደምታቋርጥ ዛተች።
    • ግዙፉ የነዳጅ አቅራቢ ሼል በዩክሬን ላይ ወረራ ከተፈጸመ በኋላ ባለፈው ሳምንት ከሩሲያ ድፍድፍ ነዳጅ በመግዛቱ ይቅርታ የጠየቀ ሲሆን ከዚህ በኋላ ከሩሲያ መግዛቱን እንደሚያቆም ቃል ገብቷል።
    • የዩናይትድ ኪንግደም የመከላከያ ሚኒስትር ቤን ዋላስ በዩክሬን ላይ ከበረራ ነጻ ቀጠናን ማወጅ የማይሆን መሆኑን ገለጹ። ነገር ግን አገራቸው ለዩክሬን ሁሉንም አይነት ድጋፍ እንደምታቀርብ ተናግረዋል
  3. ፖላንድ ለዩክሬናውያን ስደተኞች የሚቀርበው እርዳታ በቂ አይደለም አለች

    የፖላንድ ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በአገሪቱ ተጠልለው ለሚገኙ ስደተኞች የአውሮፓ ሕብረት እያቀረበ የሚገኘው እርዳታ በቂ አይደለም አሉ።

    ባለሥልጣኑ የአውሮፓ ሕብረት ስደተኞችን ለተቀበሉ አገራት ለመስጠት ያቀደው 500 ሚሊዮን ዩሮ በቂ አይደለም ብለዋል።

    “በግልጽ ይህ የገንዘብ መጠን በቂ አይደለም፤ በተለይ ደግሞ ወደ ተቀባይ አገራት ሲከፋፈል” ብለዋል ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ፓዎል ጃብሎስኪ።

    የሩሲያ ወረራን ተከትሎ 2 ሚሊዮን ሰዎች ዩክሬንን መልቀቃቸውን የመንግሥታቱ ደርጅት ያስታወቀ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 1.2 ሚሊዮን የሚሆኑት ወደ ፖላንድ የሸሹት ናቸው።

    ምክትል የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የአውሮፓ ሕብረት የሚሰጠውን የገንዝብ እርዳታ መጠን ያሰላው ፖላንድ 1 ሚሊዮን ተፈናቃዮችን ልታስተናግድ ትችላለች በሚል መሆኑን ገልጸዋል።

  4. ተመድ ከዩክሬን የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር 2 ሚሊዮን ደርሷል አለ

    የተባበሩት መንግሥታት የሩሲያን ወረራ ተከትሎ ከዩክሬን የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከ2 ሚሊዮን መሻገሩን በትዊተር ገጻቸው ላይ አስታወቀ።

    የተመድ የሰብዓዊ የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፊሊፖ ግራንዲ የስደተኞቹን ሁኔታ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ በአውሮፓ ምድር የተከሰተ ቀውስ ብለውታል።

    አብዛኛው ስደተኞቹ ወደ ጎረቤት አገር ፖላንድ ተሰደዋል። የፖላንድ ባለስልጣናት እንደሚሉት ከሆነ እስካሁን ድረስ 90 በመቶ ዩክሬናውያን የሆኑ 1.2 ሚሊዮን ተፈናቃዮችን ተቀብለዋል።

  5. ሩሲያ ብዙ ማዕቀብ የተጣለባት አገር ሆነች

    ሩሲያ በርካታ ማዕቀብ የተጣለበት አገር መሆኗን አንድ ሪፖርት አመለከተ።

    በምዕራባውያን አገራት የሚጣሉ ማዕቀቦችን የሚከታተለው 'ካስቴሉም' የተሰኘው ድርጅት ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ መፈጸሟን ተከትሎ ኢራን እና ሶሪያን በመብለጥ በርካታ ማዕቀብ የተጣለባት አገር ሆናለች ብሏል።

    ሩሲያ ዩክሬንን ከመውረሯ ቀደም ብሎ 2 ሺህ 754 ማዕቀቦች ተጥለውባት የነበረ ሲሆን፤ በኪዬቭ ላይ ወረራ ከፈጸመች በኋላ ደግሞ ተጨማሪ 2 ሺህ 778 ማዕቀቦች ተጥለውባታል።

    በአሁኑ ወቅት ሩሲያ ላይ የተጣለው ማዕቀብ 5 ሺህ 532 መድረሱ ተገልጿል።

    ዩናይትድ ስቴትስ ሩሲያ ላይ ከተጣሉት ማዕቀቦች 21 በመቶ በመሸፈን ከፍተኛውን ድርሻ ይዛለች።

    የአውሮፓ ሕብረት እና ዩናትድ ኪንግደም ደግሞ ሩሲያ ላይ ከተጣሉት ማዕቀቦች መካከል 18 በመቶ የሚሆነውን ማዕቀብ ጥለዋል።

    እንደ ድርጅቱ ከሆነ ከሩሲያ በመቀጠል ኢራን 3 ሺህ 616 ማዕቀቦችን በማስተናገድ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።

    ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ መፈጸሟን ተከትሎ አገራት እና ተቋማት ሞስኮ ላይ ተፈጻሚ የተደረጉ መጠነ ሰፊ ማዕቀቦችን ሲያስተዋውቁ ነበር።

  6. ሩሲያ ነዳጇ ላይ ማዕቀብ ከተጣለባት ለአውሮጳ የምታቀርበውን የተፈጥሮ ጋዝ እንደምታቋርጥ ዛተች

  7. ዜሌንስኪ ጦርነቱን 'ለማሸነፍ' በኪዬቭ እቆያለሁ አሉ

    የዩክሬኑ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜለንስኪጦርነቱን ለማሸነፍ ከኪዬቭ አልወጣም አሉ።

    ዜሌንስኪ አዲስ ባጋሩት ተንቀሳቃሽ ምስል በሚደናዋ በሚገኘው መስሪያቤታቸውእንደሚቆዩ ገልጸዋል።

    "አልደበቅም። ማንንም አልፈራም። ይህንን ጦርነት ለማሸነፍ እስካስፈልገ ድረስ ... (እቆያለሁ)!" ብለዋል።

    መልዕክቱ ሰኞ አመሻሽ ላይ ስለመቀረጹ ለማረጋገጥ ዜለንስኪ በዋና ከተማው እምብርት ከሚገኘው ቢሯቸው ኪዬቭን በምሽት አሳይተዋል።

  8. ማክሮን እና ሾልስ ከዢ ጋር ሊነጋገሩ ነው

    የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን እና የጀርመኑ ቻንስለርኦላፍ ሾልስ በጋራ ከቻይናው ፕሬዝዳንት ዢ ጂንፒንግ ጋር ዛሬ የስልክ ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    ውይይቱ በሩስያ እና በዩክሬን ግጭት ላይ የአውሮፓ መሪዎች በቻይና ላይ የሚያደርጉትን ጫና መጨመሩን ያሳያል ተብሏል።

    የአውሮፓ ሕብረት የውጭ ፖሊሲ ሃላፊ ጆሴፍቦሬል ወረራው ከጀመረ ለሁለተኛ ጊዜ ከቻይናው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዩጋር ሰኞ ዕለት ተወያይተዋል።

    በንግግራቸው መሠረት ቦሬል "ቻይና ግጭትን ላለማበረታታት እና ውይይቶችን ለመደገፍ ዝግጁ ስለመሆኗ" እና ሠላማዊ ዜጎች ለቀው መውጣት የሚያስችላቸውን ሰብዓዊ ኮሪደሮችን ለመመስረት በሚደረገው ጥረት ድጋፍ ዙሪያ ዋንግን ጠይቀዋል።

    ቻይና በጥቃቱ “ማዘኗን” ጠቅሳ በውጭ ፖሊሲዋ መርሆቿ መሠረት ሞስኮን ለማውገዝም ሆነ ለመቃወም ምንም አላለችም።

  9. የሩሲያ እና ዩክሬን ሦስተኛ ዙር ንግግር ያለውጤት ተጠናቀቀ

    ሩሲያ እና ዩክሬን ያካሄዱት ሦስተኛው ዙር ንግግር ይህ ነው የሚባል ውጤት ሳይመዘገብበት ተጠናቀቀ።

    ሮይተርስ የዜና ወኪል አንድ የዩክሬን ተደራዳሪን ጠቅሶ እንደዘገበው አጠቃላይ ሁኔታውን ሊያሻሽል የሚችል ስምምነት ላይ መድረስ አልተቻለም።

    የሩሲያ ተደራዳሪ ደግሞ፤ ከውይይቱ ይጠበቅ የነበረው ውጤት አልተገኘም ስለማለታቸው የሩሲያ ቴሌቪዥን ጣቢያ ዘግቧል።

    የዩክሬን ፕሬዝደንት አማካሪ እና ተደራዳሪ በበኩላቸው፤ ንጹሃንን ከግጭት ቀጠና ለማስወጣት ሰብዓዊ መተላለፊያ መንገድን በተመለከተ “ትንሽ አዎንታዊ” ውጤት ተገኝቷል ብለዋል።

    ሁለቱም አካላት ንግግራቸውን በቤላሩስ እንደሚቀጥሉ አስታውቀዋል።

  10. ዩክሬን አንድ ከፍተኛ የሩስያ ጦር መሪ ተገደሉ አለች

    በካርኪቭ አቅራቢያ በተካሄደ ጦርነት የሩሲያ ጦር ከፍተኛ አዛዥ መገደላቸውን የዩክሬን ጦር የስለላ አገልግሎት አስታወቀ።

    ቢቢሲ ጉዳዩን ከገለልተኛ ወገን ማረጋገጥ ያልቻለ ሲሆን የሩሲያ ባለስልጣናትም በጉዳዩ ዙሪያ አስተያየት አልሰጡም።

    የዩክሬን መከላከያ ሚኒስቴር ባወጣው መግለጫ መሠረት ቪታሊ ጌራሲሞቭ፤ የሜጀር ጄኔራል ማዕረግ ያላቸው ሲሆን የ41ኛው የሩሲያ ማዕከላዊ ዕዝ ምክትል ዋና አዛዥ ነበሩ።

    በርካታ ከፍተኛ የሩሲያ የጦር መኮንኖችም መገደላቸውን እና ቀሪዎቹም መቁሰላቸውን ገልጿል ይሄው የዩክሬን ተቋም።

    የዩክሬን የስለላ ድርጅት እንዳስታወቀው ጌራሲሞቭ በሁለተኛው የቺቺን ጦርነት እና በሶሪያ የሩሲያ ወታደራዊ ዘመቻ ወቅት መሳተፋቸውን ገልጿል። "ክራይሚያን ለመመለስ" ባደረጉት አስተዋጽኦም ሜዳልያ አግኝተዋል።

    የዩክሬን ባለስልጣናት የጌራሲሞቭ ነው ያሉትን ፎቶ በትዊተር ይፋ ያደረጉ ሲሆን “ተወግዷል” የሚለው ቃል ከስሩ በቀይ ቀለም አስፍረዋል።

  11. የዓለም ባንክ ለዩክሬን 700 ሚሊዮን ዶላር ፈቀደ

    የዩክሬን መንግሥት ደሞዝ እና ጡረታን ለመክፈል የሚያስቸለውን የ723 ሚሊየን ዶላር የአደጋ ጊዜ ፋይናንስ የዓለም ባንክ አጸደቀ።

    ባንኩ እንዳስታወቀው ገንዘቡ ከዩናይትድ ኪንግደም፣ ኔዘርላንድስ፣ ስዊድን፣ ጃፓን፣ ዴንማርክ፣ ላትቪያ፣ ሊቱዌኒያ እና አይስላንድ የተገኘ የገንዘብ ድጋፍን ያካተተ መሆኑን ገልጿል።

    የዓለም ባንክ አክሎም በሚቀጥሉት ወራት ለዩክሬን እና ለጎረቤት አገራት ተጨማሪ ሦስት ቢሊዮን ዶላር ለመልቀቅ እየሠራ መሆኑን አስታውቋል።

  12. ሩሲያ ጦርነቱን ለማቆም ለዩክሬን ቅድመ ሁኔታዎችን አቀረበች

    ሩሲያ በዩክሬን ውስጥ እያካሄደች ያለውን “ልዩ ወታደራዊ ዘመቻን” ለማቆም ቅድመ ሁኔታዎችን አስቀመጠች።

    ሩሲያ እንዳለችው ለቀረቡት ቅድመ ሁኔታዎች ዩክሬን አዎንታዊ ምላሽ የምትሰጥ ከሆነ እየተካሄደ ያለው ወታደራዊ ዘመቻ “በማንኛውም ሰዓት” ሊቆም ይችላል።

    የሩሲያ መንግሥት ቃል አቀባይ ዲሚትሪ ፔስኮፍ እንደተናገሩት፣ ዩክሬን ሩሲያ ከዓመታት በፊት በወረራ የያዘቻትን ክራይሚያን እንደ ሩሲያ ግዛት እውቅና አንድትሰጥ ጠይቀዋል።

    እንዲሁም ለዚህ ሁሉ ጦርነት እንደመነሻ ለሆኑትና ከማንም ቀድማ ሩሲያ እውቅና ለሰጠቻቸው ዶኔትስክና ሉሃንስክ ለተባሉት ምሥራቃዊ ግዛቶቿ የነጻ አገርነት አውቅናን እንድትሰጥ ቅድመ ሁኔታ አቅርባለች።

    የክሬምሊን ቃል አቀባይ ፔስኮቭ ጨምረውም ዩክሬን ሕገ መንግሥቷን በማስተካከል ኔቶን ወደ መሳሰሉ ማኅበራት ለመግባት ያላትን ፍላጎት እንድትተውም ሩሲያ ፍላጎት እንዳለት አመልክተዋል።

    እነዚህ ቅድመ ሁኔታዎች የሚሟሉ ከሆነ ሩሲያ በዩክሬን ውስጥ እያካሄደችው ያለው አገሪቱን “ከወታደራዊ እንቅስቃሴ ነጻ የማድረግ ዘመቻ” እንደምታጠናቅቅና እየተወሰደ ያለውም ወታደራዊ እርምጃም “ወዲያውኑ ይቆማል” ሲሉ ተናግረዋል።

    ቃል አቀባዩ አክለውም ሩሲያ እያካሄደችው ባለው ወታደራዊ ዘመቻ በዩክሬን ላይ ምንም አይነት ተጨማሪም የግዛት የይገባኛል ጥያቄ እንደሌላትም አመልክተዋል።

    ሩሲያ አሁን እንደራሷ ግዛት እንዲታወቅላት የጠየቀችው ክራይሚያን ከስምንት ዓመት በፊት ከዩክሬን በወረራ የነጠቀቻት ቁልፍ ግዛት ናት።

    ከክራይሚያ ወረራ ሳምንታት በኋላ ደግሞ በምሥራቅ ዶኔትስክና ሉሃንስክ የዩክሬን ግዛቶችን ለመገንጠል የሚታገሉትን አፍቃሬ ሩሲያ ቡድኖችን በመደገፍ አሁን ለደረሱበት አብቅታቸዋለች።

    ሩሲያ ከሳምንታት በፊት ለሁለቱ ግዛቶች የነጻ አገርነት አውቅናን ሰጥታለች።

  13. ከ1ሺህ 200 በላይ ንጹሃን ተጎድተዋል- ተመድ

    የሩሲያ የዩክሬን ወረራን ተከትሎ ከ1200 በላይ ንጹሃን ሰዎች መጎዳታቸውን የተባበሩት መንግሥታት የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽን አስታወቀ።

    ባለፉት ሁለት ሳምንታት ጉዳት ካጋጠማቸው መካከል 406 የሚሆኑት ሕይወታቸው ያለፈ ሲሆን 801 ሰዎች ደግሞ የተለያየ መጠን ያለው ጉዳት ደርሶባቸዋል ብሏል ከፍተኛ ኮሚሽኑ።

    እንደ ኮሚሽኑ ከሆነ ከፍተኛ ጉዳት ያጋጠመው ሩሲያ እውቅና በሰጠቻቸው እና በምስራቅ ዩክሬን በሚገኙት ዶኔስክ እና ሉሃንስክ ግዛቶች ነው።

    “ጉዳት የደረሰባቸው ትክክለኛው የሰዎች ቁጥር ከዚህ በላይ ሊሆን ይችላል” በማለት የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽኑ ግምቱን አስቀምጧል።

    ተመድ እስካሁን ድረስ ጦርነቱን ተከትሎ ከ1.7 ሚሊዮን በላይ ዩክሬናውያን መኖሪያቸውን ጥለው መሰደዳቸውን ተገልጿል።

  14. ቻይና ሩሲያ እና ዩክሬንን ለማደራደር ፍቃደኛ ነኝ አለች

    የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አገራቸው ጦርነት ውስጥ የሚገኙት ሩሲያ እና ዩክሬን ወደ ሰላም እንዲመጡ ለማደራደር ዝግጁ መሆኗን ገልጹ።

    ከዚህ ቀደም ሁለቱን አገራት ለማደራደር በተዋጊዎቹ በኩል ተቀባይነት ከሚኖራቸው ግለሰቦች መካከል የቀድሞ የጀርመኗ ቻንስለር አንጌላ መርክል እና የቻይናው ዢ ተጠቃሽ ናቸውሲባል ቆይቷል።

    የቻይና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዋንግ ዩበሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ መንግሥታቸው “ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር በመሆን ቀውሱን ለመፍታት የሽምግልናው አካል ለመሆን” ፈቃደኛ መሆኑን ተናግረዋል።

    ቻይና እስካሁን ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈጸመችውን ጥቃት “ወረራ” ብላ ከመጥራት ተቆጥባለች።

    አንዳንድ ተንታኞች ቤጂንግ ይህንን ግጭት የጂኦፖለቲካዊ ጥቅምን ለማስገኘት እየተጠቀመችበት እንደሆነ ይጠቅሳሉ።

    ለሩሲያ የኢኮኖሚ ድጋፍ በማድረግም ፑቲንንከማገዝ ባለፈ ለጦርነቱ አሜሪካን እየወቀሰች ነው ይላሉ።

    ከአንድ የሩሲያ ጋዜጠኛ ስለ ማዕቀብ የተጠየቁት ዋንግ፤ቻይና እና ሩሲያ "የቀዝቃዛው ጦርነት አስተሳሰብን ለማደስ የሚደረገውን ሙከራ" በጋራ ይቃወማሉ ብለዋል።

    የዩክሬን ጦርነትን በተመለከተ ቻይና የሚነሱባት ሁለት ጥያቄዎች አሉ።

    የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ወረራውን እንዲያቆሙ ለማሳመን በቂ አቅም አለት? እንዲሁም ቤጂንግ ጦርነቱን ለማስቆም ከሩሲያ ጋር ያላትን ግንኙነት ምን ያህል መጠቀም ትፈልጋለች? የሚሉት ናቸው።

    የቻይና መንግሥት ለዩክሬን ጦርነት የመፍትሄ አካል እንዲሆን መፍትሔው በክሬምሊን የፀደቀ መሆን አለበት።