የአሜሪካ ጣልቃ መግባት ሦስተኛውን የዓለም ጦርነት ይቀሰቅሳል፡ ባይደን

የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አገራቸው ዩክሬንን ለመከላከል ሠራዊቷን የምታሰማራ ከሆነ ሦስተኛው የዓለም ጦርነትን ሊያስከትል እንደሚችል አስጠነቀቁ። ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት በዚህም ምክንያት አሜሪካ ወታደሮቿን ወደ ዩክሬን እንደማትልክ አስረግጠው ገልጸዋል።

የቀጥታ ሽፋን

  1. ሩሲያ ተገደው የገቡ የሠራዊት አባላትን አሰማርታለችተባለ

    ዩናይትድ ኪንግደም የሞስኮ አስተዳደር በዩክሬን ጦርነት ሠራዊቱን ተገደው የተቀላቀሉ ወታደሮችን አሰማርቷል አለች።

    ይህ የተባለው የዩኬ መንግሥት ስለ ጦርነቱ በወቅታዊው የወታደራዊ እንቅስቃሴ ዙሪያ በሚያወጣውመግለጫ ነው።

    የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን በዚህ ሳምንት ጭምር ሰዎች ተገገው በጦርነቱ ተሳታፊ እንደማይሆኑ ቢገልጹም ሞስኮ ግን ሰዎች ያለ ፍላጎታቸው እንዲዋጉ እያደረገች ነው ስትል ዩናይትድ ኪንግደም አስታውቃለች።

    ዩናይትድ ኪንግደም ባወጣችው አጭር መግለጫ “ጉዳቶቹ እየጨመሩ ስለሄዱ ፕሬዝዳንት ፑቲን ተተኪዎችን ፍለጋ ከሩሲያ ጦር ኃይሎች እና ከሌሎች ምንጮች ለማዝመት ይገደዳሉ” ብላለች።

    በተጨማሪም ከቅርብ ቀናት ወዲህ የሩሲያ አየር ጥቃት “በከፍተኛ ደረጃ” መቀነሱን ተገልጿል።

    በሰሜን ምዕራብ ኪዬቭ የሚገኘው የሩሲያ ጦር መግፋት የቻለው በአነስተኛ መጠን ከመሆኑ ባለፈ “በዩክሬን ጦር ኪሳራ እየደረሰበት ነው” ተብሏል።

    እንደ አንድ ሪፖርት ግምት ከሆነ እስካሁን ወደ 5,000 የሚጠጉ የሩሲያ ወታደሮች ተገድለዋል።

  2. የዩክሬን ጦር ኪዬቭ አካባቢ መልሶ ማጥቃት መጀመሩ ተዘገበ

    የዩክሬን ጦር ዋና ከተማዋ ኪዬቭን ለመከላከል በሩሲያ ጦር ላይ የመልሶ ማጥቃት ዘመቻ መጀመሩን ሰስፕላይን የተባለው የዩክሬን መገናኛ ብዙሃን የሃገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስትሩን አማካሪ ጠቅሶ ዘገበ።

    ቫዲም ዴኒይሴንኮ "ሌሊቱ በጣም አስቸጋሪ ቢሆንም የዩክሬን ጦር በኪዬቭ አቅራቢያ መልሶ ማጥቃት ፈጽሟል ማለት እንችላለን” ብለዋል። አክለውም "አምስት ታንኮችን አሰለፍን።

    ጠዋት ላይ በመድፍ የታገዘ ጦርነት በምዕራባዊ የኪዬቭ ዳርቻ ነበር። አሁንም ጦርነቶች አሉ። እስካሁን ምንም ተጨማሪ ዝርዝር መረጃ የለም” ብለዋል።

    ቢቢሲ ጉዳዩን ማረጋገጥ አልቻለም።

  3. ዋይት ሃውስ ሩሲያ የኬሚካል ጥቃት ልትፈጽም ትችላለች አለ

  4. ዜሌንስኪ የሩሲያ ጦር ሆስፒታል ማጥቃቱ ‘የጦር ወንጀል ነው’ አሉ

    የዩክሬን ፕሬዝደንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ የሩሲያ ጦር ሆስፒታል ዒላማ ማድረጉ ከተዘገበ በኋላ ይህ ጥቃት የጦር ወንጀል ነው ብለዋል።

    በዩክሬኗ ማሪኦፖሎ ከተማ በሚገኝ የእናቶች እና ሕጻናት ሆስፒታል ላይ በደረሰ ጥቃት ቢያንስ 17 ሰዎች ሳይጎዱ አይቀሩም ተብሏል።

    “ሩሲያ ፌዴሬሽን ምን አይነት አገር ነው? የእናቶች ሆስፒታልን ፈርቶ የሚያወድም?” ሲሉ ፕሬዝደንት ዜሌንስኪ ከኪዬቭ ሆነው ባስተላለፉት ንግግራቸው ጥያቄ ሰንዝረዋል።

    ዜሌንስኪ፤ “ዛሬ ይህን የሩሲያ የጦር ወንጀል በአንድነት ሆነን ማውገዝ አለብን” ካሉ በኋላ “ይህ በሆስፒታል ላይ የደረሰው ጥቃት . . . በዩክሬናውያን ላይ የዘር ማጥፋት ወንጀል እየተፈጸመ ስለመሆኑ ማረጋገጫ ነው” ብለዋል።

  5. የዩክሬን እና የሩሲያ የሰላም ተደራዳሪዎች ቱርክ ደረሱ

    የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ እና የዩክሬኑ አቻቸው ድምትሮ ኩሌባ ለሰላም ንግግር ቱርክ ተገኝተዋል።

    ፕሬዝደንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶሃን በሚገኙበት ሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በቱርኳ አንታላይ ከተማ ዛሬ ንግግር ይጀምራሉ ተብሎ ይጠበቃል።

    የቱርኩ ፕሬዝደንት ሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የሚያደርጉት ውይይት፤ “ቋሚ ለሆነ የተኩስ አቁም ስምምነት በር የሚከፍት ይሆናል ብዬ ተስፋ አድርጋለሁ” ብለዋል።

    ሩሲያ በዩክሬን ላይ የከፈተችው ወታደራዊ ወረራ ሁለት ሳምንት ሊሞላው የተቃረበ ቢሆንም እስካሁን የተደረጉ ንግግሮች ጦርነቱን ለማስቆም የሚያስችል ይህ ነው የሚባል ውጤት አላስገኙም።

  6. አሜሪካ እስካሁን እስከ 6ሺህ የሩሲያ ወታደሮች ሳይገደሉ አይቀሩም አለች

    አሜሪካ እስካሁን ድረስ ከ5-6 ሺህ የሚሆኑ የሩሲያ ጦር አባላት ሳይገደሉ አይቀሩም አለች።

    ባለፉት 2 ሳምንታት ሲደረግ በነበረው ጦርነት የተጎዱ የሩሲያ ጦር አባላት ቁጥር ደግሞ ከ15ሺህ-18ሺህ እንደሚሆኑ ከፍተኛ የአሜሪካ መንግሥት ባለስልጣናት ለሲቢኤስ ኒውስ ተናግረዋል።

    አንድ ስማቸው ያልተገለጸ የአሜሪካ መንግሥት ባለስልጣን ደግሞ ከሁለተኛው ዓለም ጦርነት በጦር ሜዳ ከተገደሉ ሰዎች ቁጥር ጋር ሲነጻጸር ይኼኛው ከፍተኛ የሞት መጠን ነው ብለዋል።

    ዩክሬን በበኩሏ እስካሁን በተደረገው ጦርነት 12ሺህ የሩሲያ ወታደሮችን ገድያለሁ ትላለች።

    ሩሲያ ባለፈው ሳምንት እንዳስታወቀችው ዩክሬን ውስጥ ሕይወታቸው ያለፈ ወታደሮቿ ቁጥር ከ500 በታች ነው።

  7. አሜሪካ ከፍተኛ የሆነ የገንዘብ መጠን ለዩክሬን ልትለግስ ነው

    የአሜሪካ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለዩክሬን የሚሰጥን 13.6 ቢሊዮን ዶላር አጸደቁ።

    በቀጣይ ቀናት በሴኔቱም እንደሚጸድቅ የሚጠበቀው ይህ የዩክሬን ፈንድ፤ ገሚሱ ለሰብዓዊ እርዳታ አቅርቦት የሚውል ሲሆን የተቀረው ደግሞ ዩክሬን የመከላከያ ኃይሏን ታጠናክርበታለች ተብሏል።

    ፕሬዝደንት ባይደን የሕዝብ ተወካዮቹን ጠይቀው የነበረው የ10 ቢሊዮን ዶላር እርዳታ ቢሆንም የምክር ቤት አባላቱ በሩሲያ ላይ ያላቸውን አቋም ለማንጸባረቅ የድጋፍ መጠኑ ከፍ አድርገዋል ተብሏል።

  8. አፍሪካውያን መሪዎች ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር ተወያዩ

    አፍሪካውያን መሪዎች በዩክሬን ከባድ ጦርነት ውስጥ ከገባችውና ምዕራባውያን ተከታታይ ማዕቀብ እየጣሉባት ካለችው ሩሲያ መሪ ጋር መወያየታቸው ተነገረ።

    የሴኔጋል ፕሬዝዳንት እና የወቅቱ የአፍሪካ ሕብረት ሊቀ መንበር ማኪ ሳል ከሩሲያው አቻቸው ቭላድሚር ፑቲን ጋር ዩክሬን ውስጥ “ዘላቂ ተኩስ አቁም” ስለማድረግ መነጋገረቸው ተዘግቧል።

    የሴኔጋሉ ፕሬዝዳንት በትዊተር ሰሌዳቸው ላይ “እንደ አፍሪካ ሕብረት ሊቀ መንበርነቴ ከፕሬዝዳንት ፑቲን ጋር ዘላቂ የተኩስ አቁም ስለሚደረግበት ሁኔታ በመወያየቴ ደስ ብሎኛል” ሲሉ አስፍረዋል።

    ጨምረውም "ፕሬዝዳንቱ ስላዳመጡኝና ግጭቱን ለማስቆም የሚያስችለውን ድርድር ለመቀጠል ፈቃደኝነታቸውን ስላሳዩ አድናቆቴን መግለጽ እፈልጋለሁ” ብለዋል።

    ማኪ ሳል ከቭላድሚር ፑቲን ጋር መወያየታቸውን ካሳወቁ የአፍሪካ መሪዎች መካከል ሁለተኛው ሲሆኑ ቀደም ሲል የግብፁ ፕሬዝዳንት አብዱል ፋታህ አል-ሲሲ ተመሳሳይ ውይይት ማድረጋቸው ተገልጿል።

    የግብፁ ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት መሪዎቹ ያደረጉት ውይይት በዩክሬን ውስጥ ስለተከሰተው ቀውስ እና በሁለቱ አገራት መካከል ያለውን ግንኙነት በማጠናከር ላይ ያተኮረ ነው ብሏል።

    ከሁለት ሳምንት በፊት የሩሲያ ወታደሮች ወደ ዩክሬን ዘልቅ መግባታቸውን ተከትሎ የአፍሪካ ሕብረት የዩክሬን የግዛት አንድነት እና ዓለም አቀፍ ሕግ እንዲከበር ባወጣው መግለጫ ላይ ጥሪ አቅርቦ ነበር።

    የምዕራብ አፍሪካ አገራት የኢኮኖሚ ማኅበር ኤኮዋስ ደግሞ ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈጸመችው ወረራ አውግዟል።

  9. ሩሲያ ከቅርብ ጊዜ በኋላ እዳዋን መክፈል አትችልም ተባለ

    አንድ አገራት ያለባቸውን ብድር መልሶ የመክፈል አቅም የሚመዝን ኤጀንሲ ሩሲያ በቅርቡ ያለባትን እዳ መልሳ የመክፈል አቅም አይኖራትም ሲል ገለጸ።

    ሞስኮ እዳዋን መክፈል ይከብዳታል የተባለው በዩክሬን ላይ ወረራ መፈጸሟን ትከትሎ ምዕራባውያን አገራት በርካታ ማዕቀቦችን ከጣሉባት በኋላ ነው።

    የሩሲያ የብድር መክፈል አቅም መዳከም ማለት ባለሃብቶች የሩሲያ መንግሥት ቦንድን ከመግዛት እንዲቆጠቡ ያደርጋቸዋል።

    ሩሲያ ከሁለት ሳምንት በፊት በዩክሬን ላይ ወታደራዊ ጥቃት መክፈቷን ተከትሎ ምዕራባውያን ተከታታይ ምጣኔ ሀብታዊና ሌሎች ማዕቀቦችን እየጣሉ ነው።

  10. የቱርኩ ፕሬዝዳንት ኤርዶዋን ዩክሬን እና ሩሲያን ሊያደራድሩ ነው

    የሩሲያ እና የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ነገ ሐሙስ በቱርኳ አንታሊያ ከተማ ሲገናኙ ፕሬዝደንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶዋን እንደሚያደራድሯቸው ተገለጸ።

    የቱርኩ ፕሬዝደንት ሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች የሚያደርጉት ውይይት፤ “ቋሚ ለሆነ የተኩስ አቁም ስምምነት በር የሚከፍት ይሆናል ብዬ ተስፋ አድርጋለሁ” ብለዋል።

    ቱርክ ምንም እንኳ የሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) አባል አገር ብትሆንም፤ ኤርዶዋን የሩሲያን እና የዩክሬን ወረራን በተመለከተ ከምዕራባውያኑ የተለየ አቋም ለመያዝ እየሞከሩ ነው።

    ኤርዶዋን ከዚህ ቀደም በዩክሬን ላይ የተፈጸመውን ወረራ እንደማትቀበል ገልጸው፤ የሩሲያን የደኅንነት ስጋት ግን እጋራለሁ በማለት ምዕራባውያን ሩሲያ ላይ የጣሏቸውን ጥበቅ ማዕቀቦችንም ተቃመዋል።

    የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ በመጪው ሐሙስ ከዩክሬኑ አቻቸው ዲሚትሮ ኩሌባ ጋር ቱርክ ውስጥ ተገናኝተው እንደሚወያዩ እየተጠበቀ ነው።

    ሩሲያ በዩክሬን ላይ የከፈተችው ወታደራዊ ወረራ ሁለት ሳምንት ሊሞላት የተቃረበ ሲሆን፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ የሁለቱ አገራት ባለሥልጣናት ቤላሩስ ውስጥ ለሦስት ጊዜ ተወያይተዋል። ነገር ግን አስካሁን ጦርነቱን ለማስቆም የሚያስችል ይህ ነው የሚባል ውጤት አልተገኘም።

  11. ዓለም ለነዳጅ እና ለጋዝ ፍላጎቱ ሩሲያ ላይ ምን ያህል ጥገኛ ነው?

  12. ከዩክሬን ከተሰደዱት 2 ሚሊዮን ሰዎች 800 ሺህዎቹ ህጻናት ናቸው ተባለ

    የተባባሩት መንግሥታት ድርጅት የሕጻናት አድን ድርጅት ሴቭ ዘ ችልድረንከዩክሬን ከተሰደዱት 2 ሚሊዮን ሰዎች መካከል 800 ሺህዎቹ ህጻናት ናቸውአለ።

    ብዙዎቹ ሕጻናት ጉዞውን በራሳቸው እያደረጉ ሲሆን ያለአጃቢ እየሸሹም ነው ሲል ኤጀንሲው አስጠንቅቋል።

    “ወላጆች ልጆቻቸውን ለማዳን በጣም ተስፋ አስቆራጭ እና ልብ የሚሰብሩ እርምጃዎችን እየወሰዱ ነው። ልጆቻቸውን ከጎረቤቶቻቸው እና ከጓደኞቻቸው ጋር ከዩክሬን ውጭ ደኅንነት ወዳለባቸው አካባቢዎች እየላኩ እነሱ ቤታቸውን ለመጠበቅ በዛው መቆየትን ይጨምራል” ሲሉ መንግስታዊ ያልሆነው ድርጅት ባለድረባ የሆኑት ኢሪና ሳጎያን ተናግረዋል።

    ከዩክሬን ተነስቶ ለብቻው ስሎቫኪየ የደረሰው የ11 ዓመት ታዳጊ ልጅ ጉዳይ የበርካቶችን ቀልብ ስቦ ነበር።

    ሐሰን የተባላው ታዳጊ ወላጅ እናቱ እናቷን ጥላ መሸሽ ባለመቻሏ የ11 ዓመቱ ታዳጊ ለብቻው ከዩክሬን ለመውጣት ተገዷል።

    ሐሰን በባቡር 1,200 ኪሎ ሜትር አቆራርጦ ስሎቫኪያ መድረስ ችሏል። ሐሰን ስሎቫኪያ የደረሰው ሁለት አነስተኛ ሻንጣዎችን፣ ፓስፖርቱን እና የዘመዶቹን ስልክ ቁጥር በእጁ ጽፎ ነው።

    ከዩክሬን ከሚወጡት ስደተኞች ውስጥ ከግማሽ በላይ የሚሆኑት ወደ ፖላንድ፣ ከዚያም ወደ ሃንጋሪ እና ስሎቫኪያ ይሄዳሉ።

  13. የሩሲያ እና የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በቱርክ ሊገናኙ ነው

    የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ከዩክሬኑ አቻቸው ዲምትሪ ኩሌባ ጋር በቱርክ እንደሚገናኙ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታወቀ።

    ከሩሲያ ወረራ በኋላ የሁለቱ አገራት ከፍተኛ ባለስልጣናት ፊት ለፊት ሲገናኙ ይህ የመጀመሪያው ይሆናል።

    ላቭሮቭ ወደ ቱርክ አንታላይ ከተማ አቅንተው ከዩክሬኑ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር እንደሚገናኙ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ተናግረዋል።

    ሁለቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በቱርክ ለንግግር የጋበዟቸው የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትር መሆናቸውም ተመልክቷል።

    የሁለቱ አገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ነገ ሐሙስ መጋቢት 1 እንደሚገናኙ ተገልጿል።

  14. በዩክሬን ለሚሰማሩ ቅጠረኛ ወታደሮች በቀን እስከ 2ሺህ ዶላር ለመክፈል ማስታወቂያ ወጣ

  15. ሳዑዲ እና ኢሚሬትስ ለባይደን ምላሽ ሳይሰጡ መቅረታቸው ተሰማ

    ዋይት ሃውስ ይፋዊ ባልሆነ መንገድ ፕሬዝደንት ጆ ባይደን ከሳዑዲ አረቢያ እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች መሪዎች ጋር በስልክ እንዲነጋገሩ ያደረገው ጥረት ሳይሳካ መቅረቱን ዎል ስትሪት ጆርናል ዘገበ።

    ባይደን የባህረ ሰላጤ አገራቱን መሪዎች ለማነጋገር ጥረት ማደረግ የጀመሩት ለዩክሬን ዓለም አቀፍ ድጋፍ ለማሰባሰብ እና የነዳጅ ዋጋ ጭማሪን ለመግታት አልመው ነበር ተብሏል።

    ዎል ስትሪት ጆርናል የመካከለኛው ምስራቅ አገራት እና የአሜሪካ መንግሥት ባለስልጣናት ነገሩኝ ብሎ እንደዘገበው ከሆነ፤ የሳዑዲው ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሰልማን እና የተባበሩት አረብ ኤሜሬትሱ ሼይክ ሞሐመድ ቢን ዛይድ አል-ናህያን ከባይደን ጋር እንዲነጋገሩ ከዋይት ሃውስ የቀረበላቸውን ጥያቄ ውድቅ አድርገዋል።

    ሳዑዲ ከባይደን ጋር ለመነጋገር ፍላጎት ያጣችው፤ በየመን በሚካሄደው ጦርነት፣ እያበለጸገች ላለችው የኒውክሌር ኃይል ድጋፍ ስለምትፈልግ፤ እና ልዑል አልጋ ወራሽ ሞሐመድ ቢን ሰልማን በአሜሪካ ያለመከሰስ መብት እንዲረጋገጥ ፍላጎት ስላላት መሆኑን የሳዑዲ ባለስልጣናት ለዎል ስትሪት ተናግረዋል።

    ሞሐመድ ቢን ሰልማን እአአ 2018 ላይ በኢስታንቡል በሳዑዲ ቆንስላ ውስጥ ከተገደለው ጋዜጠኛ ጀማል ኻሾግጂ ጋር በተያያዘ ሕጋዊ ጉዳዮች አሉባቸው።

    ባይደን ከዚህ ቀደም ሳዑዲ አረቢያ ለምትፈጽመው የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ‘አስከፍላታለሁ’ ብለው ነበር።

  16. ባለፉት 24 ሰዓታት የሩሲያ ጥቃት ተቀዛቅዟል- ዩክሬን

    የዩክሬን ጦር የሩስያ ወረራ 13ኛ ቀንን በማስመልከት ዕለታዊውን “የወታደራዊ ዘመቻ መረጃ” ይፋ አድርጓል።

    ባለፉት 24 ሰዓታት "ጠላት በዋነኛነት በሚሳኤል እና በቦንብ በሲቪል መሠረተ ልማቶች ላይ ከሚያደርሳቸው ጥቃቶችን በስተቀር የማጥቃት ዘመቻው ፍጥነት ተቀዛቅዟል” ሲል የዩክሬን ጦር ሃይሎች በመግለጫው አስታውቋል።

    ሩሲያ ኪዬቭ፣ ሱሚ፣ ካርኪቭ፣ ማሪዮፖል፣ ሚኮላይቪቭ እና ቼርኒሂቭ ከተሞችን በመክበብ በቁጥጥር ስር ከማዋል ባለፈ በሩሲያ እና በኃይል በያዘችው የክራይሚያ ባሕረ ገብ መሬት መካከል የመሬት የግንኙነት መስመር ለመፍጠር ትኩረት ሰጥታ እየሠራች ነው ብሏል።

    የሩሲያ ጦር ከፍተኛ ኪሳራ እየደረሰበት መሆኑን እና "የመስክ ላይ ነዳጅ ማደያዎችን" በማዘጋጀት የነዳጅ አቅርቦትን ለማሳደግ እየሞከረ ነው ብሏል።

    ቢቢሲ የሪፖርቱ ትክክለኛነት ከገለልተኛ አካል ማረጋገጥ አልቻለም።

  17. የቢቢሲ ጋዜጠኞች ከሩሲያ ስርጭታቸውን ጀመሩ

    ጥብቅ የሆነ የሞስኮ አዲስ የመገናኛ ብዙሃን ህግ መውጣቱን ተከትሎ ሥራቸውን ያቆሙት በሩሲያ የሚገኙ የቢቢሲ ጋዜጠኞች ከቀናት በኋላ ስርጭታቸውን በድጋሚ ጀምረዋል።

    በአዲሱ ህግ መሠረት ስለ ሩሲያ ጦር "የውሸት" ዜና አሰራጭቷል የተባለ ግለሰብ እስከ 15 ዓመት የሚደርስ እስራት ይጠብቀዋል።

    በዚህ ምክንያት በርካታ የምዕራባውያን የዜና አውታሮችም ሥራቸውን አቁመዋል። የኒው ዮርክ ታይምስ ማክሰኞ ዕለት ሠራተኞቹን ከሩሲያ እያስወጣ መሆኑን አስታውቋል።

    ቢቢሲ "በጥንቃቄ ከተወያየ በኋላ" ሥራውን ለመቀጠል መወሰኑን አስታውቋል።

    በመግለጫውም “ከሩሲያ በአስቸኳይ መዘገብ ካለው አስፈላጊነት ጋር ተያይዞ የአዲሱን ህግ አንድምታ ተመልክተናል” ሲል አስታውቋል።

  18. የፑቲን ዕቅድ ኪዬቭን በሁለት ቀናት መያዝ ነበር- ሲአይኤ

    የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን በዩክሬን ላይ ወረራ በፈጸሙ ወቅት መዲናዋን ኪዬቭን በ48 ሰዓታት ውስጥ የመቆጣጠር ዕቅድ ነበራቸው ሲሉ የሲአይኤ ኃላፊ ዊሊያም በርንስ ተናገሩ።

    የአሜሪካው የስለላ ተቋም ዳይሬክተር ትናንት ማክሰኞ ለሕዝብ ተወካዮች የደህኅንነት ኮሚቴ አባላት ሲናገሩ፤ ፑቲን በቀጣይ ቀናት ጦራቸውን በማጠናከር የከፋ የኃይል እርምጃ ሊወስዱ ይችላሉ ሲሉ አስጠንቅቀዋል።

    “ፑቲን በአሁኑ ሰዓት የተበሳጩ እና ትዕግስት ያጡ ይመስለኛል” ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ፑቲን የጦር ኃይላቸውን በሁለት እጥፍ አሳድገው በዩክሬን ጦር ላይ ጠንካራ ጥቃት ለመክፈት እየተዘጋጁ ነው ብለዋል።

    በዚህ የፑቲን እርምጃም በንጹሃን ዩክሬናውያን ላይ ከፍተኛ ጉዳት ሊደርስ እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል።

    ሩሲያ በዩክሬን የፈጸመችው ወረራ ለክሬምሊን መሪው “ጥልቅ የሆነ ግላዊ ቁርጠኝነት ነው” ሲሉ ዊሊያም በርንስ ገልጸውታል።

  19. ኮካ ኮላ፣ ማክዶናልድስ እና ስታርባክ ከሩሲያ ገበያ ወጡ

    በዩክሬን የደረሰው ወረራ ምክንያት በማድረግ እንደ ማክዶናልድስ፣ ኮካ ኮላ እና ስታርባክስን ያሉ ግዙፍ ኩባንያዎች በሩሲያ ያላቸውን ሥራ ካቆሙ ድርጅቶች ዝርዝር ውስጥ ተካተዋል።

    ማክዶናልድስ በሩሲያ የሚገኙ ወደ 850 የሚጠጉ ሬስቶራንቶቹን በጊዜያዊነት እየዘጋ መሆኑን አስታውቋል። ስታርባክስ በበኩሉ 100 የሚደርሱ የቡና መሸጫ ሱቆቹ እንደሚዘጉ ገልጿል።

    ማክዶናልድስ እርምጃውን “በዩክሬን እየተከሰተ ላለው የሰው ልጅ ስቃይ ምላሽ ነው” ብሏል።

    ኮካ ኮላ ማክሰኞ ዕለት እንዳስታወቀው ሁለት በመቶ የሆነውን ገቢውን ከሚያስገኝለት የሩሲያ ገበያ እየወጣ መሆኑን አስታውቋል።

    ኩባንያው በሩሲያ የጠርሙስ እና የማከፋፈያ ንግድ ውስጥ 20 በመቶ የሚጠጋ የባለቤትነት ድርሻ አለው።

    የስታርባክስ ምርቶች መላክን ጨምሮ በሃገሪቱ ውስጥ ያለውን የንግድ እንቅስቃሴ እንደሚያቆም ደግሞ ስታርባክስ አስታውቋል።

    ኩባንያው ፈቃድ አግኝተው በስሙ የሚሠሩ ከመቶ በላይ የቡና ሱቆች ለጊዜው ይዘጋሉ።

    ፈቃዱን ያገኘውና በኩዌት የሚገኘው አልሻያ ግሩፕ ወደ 2,000 ለሚጠጉ ሠራተኞቹ ደሞዝ መክፈሉን ይቀጥላል ሲል ስታርባክ አስታውቋል።

  20. የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ከቫቲካን ጋር ለሰላም ስላለው ተስፋ ተነጋገሩ

    የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ አገራቸው ዩክሬን ውስጥ እያካሄደችው ያለውን ወታደራዊ ዘመቻን በተመለከተ የካቶሊክ ቤተክርስቲያን ማዕከል ከሆነችው ከቫቲካን ባለሥልጣናት ጋር መነጋገራቸው ተዘገበ።

    በዚህ ውይይት ላቭሮቭ ከዩክሬን አንጻር የሩሲያን አቋም ማስረዳታቸው የተጠቀሰ ሲሆን፣ በሞስኮ እና በኪዬቭ መካከል ሌላ ዙር የሰላም ንግግር እንደሚደረግ ያላቸውን ተስፋ ገልጸዋል።

    ላቭሮቭ "ግጭቱን ለማስቆም ለቀውሱ ምክንያት በሆኑ ቁልፍ ጉዳዮች ላይ ከስምምነት ለመድረስ” አገራቸው ፍላጎት እንዳላት መናገራቸውን የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ይፋ አድርጓል።

    የካቶሊካ ቤተክርስቲያን ሊቀ ጳጳስ የሆኑት አቡነ ፍራንሲስ ባለፈው እሁድ ቫቲካን ውስጥ በሚገኘው የቅዱስ ጴጥሮስ አደባባይ ለተሰበሰቡ ምዕመናን የዩክሬኑን ጦርነትን አስመለክተው እንደተናገሩት፣ ጦርነቱ “ሞትን፣ ውድመት እና ስቃይን” አስከትሏል ብለዋል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ የሩሲያው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌይ ላቭሮቭ በመጪው ሐሙስ ከዩክሬኑ አቻቸው ዲሚትሮ ኩሌባ ጋር ቱርክ ውስጥ ተገናኝተው እንደሚወያዩ እየተጠበቀ ነው።

    ሩሲያ በዩክሬን ላይ የከፈተችው ወታደራዊ ወረራ ሁለት ሳምንት ሊሞላት የተቃረበ ሲሆን፣ በዚህ ጊዜ ውስጥ የሁለቱ አገራት ባለሥልጣናት ቤላሩስ ውስጥ ለሦስት ጊዜ ተወያይተዋል። ነገር ግን አስካሁን ጦርነቱን ለማስቆም የሚያስችል ይህ ነው የሚባል ውጤት አልተገኘም።