ይህ ዝቅተኛ ዳታን በመጠቀም ጽሑፍ ብቻ የሚቀርብበት የቢቢሲ አማርኛ ድረ ገጽ ነው
የአሜሪካ ጣልቃ መግባት ሦስተኛውን የዓለም ጦርነት ይቀሰቅሳል፡ ባይደን
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አገራቸው ዩክሬንን ለመከላከል ሠራዊቷን የምታሰማራ ከሆነ ሦስተኛው የዓለም ጦርነትን ሊያስከትል እንደሚችል አስጠነቀቁ። ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት በዚህም ምክንያት አሜሪካ ወታደሮቿን ወደ ዩክሬን እንደማትልክ አስረግጠው ገልጸዋል።
የቀጥታ ሽፋን
ሩሲያ በሊቪዮቭ ወታደራዊ ማሰልጠኛ ላይ ጥቃት ፈፀመች- የዩክሬን ባለሥልጣናት
ሩስያ ከፖላንድ ድንበር አቅራብያ የሚገኝ የዩክሬን ወታደራዊ ማሰልጠኛ ላይ ጥኣት መሰንዘሯ ተሰማ።
የሊቪዮቭ ወታደራዊ አስተዳደር በያቮሪቭ የሚገኘው ዓለም አቀፉ ሰላም ጠባቂ እና ደህንነት ማዕከል በሩሲያ ኃይሎች ጥቃት እንደተፈፀመበት ገለፀዋል።
ይህ ከሊቪዮቭ ከተማ 30 ኪሎ ሜትር የሚርቀው ማዕከል የተመሰረተው እኤአ በ2007 ሲሆን ለሰላም ማስከበር የሚመለመሉ የዩክሬን ወታደሮች ማሰልጠኛ ነው።
ማዕከሉ በተደጋጋሚ ዓለም አቀፍ ወታደሮችን ከተለያየ ዓለም የሚመጡ ወታደሮችን እየተቀበለ ያስተናግዳል። የኔቶ ሰነድ እንደሚያሳየው ማዕከሉ ለዩክሬን እና ለሌሎች ወታደሮች ፈንጂ ማምከን እና ስለ ፈንጂ ደህንነት ስልጠና የሚሰጥበት ስፍራ ነው።
እንደ ቢቢሲ ባልደረባ ዘገባ ከሆነ ይህ ማዕከል በዩክሬን ከሚገኙ ሁት ዓለም አቀፍ ወታደራዊ ልምምድ ከሚደረግባቸው ስፍራዎች መካከል አንዱ ነው።
በተጨማሪም ማዕከሉ ከፖላንድ ድንበር 17 ኪሎ ሜትሮች ብቻ ርቆ የሚገኝ ነው።
ወደ ሞልዶቫ የሚገቡ ዩክሬኒያውያን ቁጥር ጨምሯል
ከዩክሬን ጦርነት የሸሹ በርካታ ዜጎች ወደ ሞልዶቫ እየገቡ መሆኑ ተገለፀ። የሞልዶቫ ባለሥልጣናትም የዓለም አቀፍ መንግሥታትን እርዳታ እንዲያደርግላኣቸው ጠይቀዋል።
ከቢቢሲ ጋር ቃለመጠይቅ ያደረጉት የአገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ናታሊያ ጋቭሪሊታ “አሁን ከ270 ሺህ በላይ ድንበራችንን አቋርጠው ገብተዋል” ብለዋል።
እስካሁን ድረስ ከ100 ሺህ በላይ ሰዎች በአገሪቱ ለመቆየት መወሰናቸውን በመጥስም “ይህ እንደ ሞልዶቫ ላለ አገር ትልቅ ቁትር ነው” ብለዋል።
ሞልዶቫ 2. 5 ሚሊየን ሕዝብ ብቻ ያላትበዩክሬን እና በሮማንያ መካከል የምትገኝ አነስተኛ አገር ናት።
ሞልዶቫ በምጣኔ ኃብት እጅጉን የተጎዳች አገር ስትሆን በአሁኑ ወቅት የስደተኞች ወደ ግዛቲቱ መግባት በጦርነቱ ምክንያት የተባባሰውን የኢኮኖሚ አለመረጋጋት እንዳያባብሰው ተሰግቷል።
“ ከሌሎች አገራት እርዳታ ያስፈልገናል” ሲሉም ተቅላይ ሚኒስትሯ ጥሪ አቅርበዋል።
18ኛ ቀኑን ስለያዘው የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት አንደንድ መረጃዎች
እስካሁን ድረስ 1ሺህ 300 ያህል የዩክሬን ወታደሮች ስለ መሞታቸው የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ቮሎድሚር ዜሌንስኪ ተናግረዋል
•በአገሪቱ ደቡብ ምስራቅ አካባቢ፣ ማሪውፖል፣ የሞስኮ ወታደሮች ተጨማሪ ቦታዎችን ስለመቆጣጠራቸው ተሰምቷል። ቅዳሜ እለት በአንድ የአሜሪካ ኩባንያ የተነሳ የሳተላይት ምስል እንደሚያሳየው የሩሲያ ወታደሮች በተቆጣጠሯት እና በአገሪቱ ምስራቃዊ ክፍል በምትገኘው የወደብ ከተማ ከፍተኛ የመሰረተ ልማት ውድመት ተከስቷል።
•የዩክሬን ባለስልጣናትም በቅርብ የምትገኘውን እና በጦርነቱ ከፍተኛ ውድመት ያስተናገደችውን አነስተኛዋን ከተማ፣ ቮልኖቫክህ፣ ወታደሮቻቸው ለቅቀው መውጣታቸውን ተናግረዋል።
•የሩሲያ ወታደሮች በተቆጣጠሯት ሜሊትፖል ከንቲባውን ማገታቸውን ተከትሎ ከፍተኛ ተቃውሞ ገጥሟቸዋል
•የዩክሬን ባለሥልጣናት የሩሰያ ወታደሮች በኪየቭ አቅራብያ አካባቢውን ለቅቀው እየወጡ በነበሩ ሴቶች እና ሕጻናት ላይ በተኮሱት ከባድ መሳሪያ ሰባት ሰዎች መሞታቸውን አስታውቀዋል። ሞስኮ እስካሁን ድረስ በጉዳዩ ላይ ምላሽ አልሰጠችም።
•የፖላንድ ድንበር ጠባቂዎች ጦርነቱ ከተጀመረ ጊዜ አንስቶ ከ1.6 ሚሊየን በላይ ሰዎች ከዩክሬን ወደ ፖላንድ ማቋረጣቸውን ገልፀዋል።
•የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የሩሲያ አቻቸው፣ ቭላድሚር ፑቲን ጦርነቱን ለማቆም ምንም ምልክት አለማሳየታቸውን ተናግረዋል። ፕሬዝዳንት ማክሮን፣ ከጀርመኑ እና የሩሲያ አቻዎቻቸው ጋር 75 ደቂቃ የፈጀ የስልክ ውይይት አድርገው ነበር።
•የሩሲያው ውጪ ጉዳይ ሚኒስትር በበኩላቸው ለዩክሬን የጦር መሳሪያ የሚያቀርቡ ምዕራባውያን የሩሲያ ጦር ዒላማ ሊሆኑ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።
አሜሪካ የሩሲያን የአልማዝ ማዕድንና ቮድካ መጠጥ አገደች
ግዙፍ የሩሲያ ሠራዊት ከኪዬቭ አቅራቢያ እንደሚገኝ ዩኬ አስታወቀች
ከፍተኛ ቁጥር ያለው የሩሲያ ሠራዊት ወደ ዩክሬን ዋና ከተማ ኪዬቭ እየተቃረበ መሆኑን የዩናይትድ ኪንግደም (ዩኬ) መከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።
ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ አዲስ ባገኘው የደኅንነት መረጃ መሠረት “ግዙፍ” ያለው የሩሲያ ጦር ሠራዊት ከዋና ከተማዋ ኪዬቭ ማዕከላዊ ክፍል በ25 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ እንደሚገኝ አመልክቷል።
ጨምሮም ከዋና ከተማ ኪዬቭ በስተሰሜን ተሰባስቦ የነበረው የሩሲያ ኃይል ወደ ተለያዩ አቅጣጫዎች መሰራማረቱን ጠቅሶ፣ ይህም ሠራዊቱ “ዋና ከተማዋን ለመክበብ የሚያደርገውን ሙከራ ለማገዝ” ይሆናል ብሏል።
"በሩሲያ ኃይሎች ላይ ከባድ ጉዳትን ያደረሰውን ከዩክሬናውያን በኩል የሚሰነዘረውን መልሶ ማጥቃት ለመቀነስ የሚደረግ ሙከራም ሊሆን ይችላል” ብሏል የዩናይትድ ኪንግደም የመከላከያ መሥሪያ ቤት።
ሁለት ሳምንት ባለፈው የሩሲያ ጥቃት በአሁኑ ጊዜ ከዋና ከተማዋ ኪዬቭ በተጨማሪ ቼርንሂቭ፣ ኻርኪቭ፣ ማርዩፖል እና ዩሚ ከተሞች በሩሲያ ኃይሎች ከበባ ስር ሆነው የባድ መሳሪያ ድብደባ ውድመት እየደረሰባቸው ነው።
ፑቲን ለሩሲያ መዝመት የሚፈልጉ የውጭ አገር ዜጎች እንዲመዘገቡ ጥሪ አቀረቡ
ባይደን የአሜሪካ ጣልቃ መግባት ሦስተኛውን የዓለም ጦርነት ይቀሰቅሳል አሉ
የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን አገራቸው ዩክሬንን ለመከላከል ሠራዊቷን የምታሰማራ ከሆነ ሦስተኛው የዓለም ጦርነትን ሊያስከትል እንደሚችል አስጠነቀቁ።
ፕሬዝዳንቱ እንዳሉት በዚህም ምክንያት አሜሪካ ወታደሮቿን ወደ ዩክሬን እንደማትልክ አስረግጠው ገልጸዋል።
"ግልጽ ማድረግ እፈልጋለሁ፤ የኔቶ አባል አገራትን እያንዳንዷን ስነዝር መሬት በተባበረና በሙሉ ኃይል እንከላከላለን" በማለት በትዊተር ገጻቸው ላይ ያሰፈሩት ባይደን፤ "ነገር ግን ዩክሬን ውስጥ ገብተን ከሩሲያ ጋር ጦርነት አንገጥምም። በኔቶና በሩሲያ መካከል የሚደረግ ቀጥተኛ ፍጥጫ ሦስተኛውን የዓለም ጦርነት ያስከትላል" ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ባይደን ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ የአሜሪካ ወታደሮች ከሩሲያ ኃይሎች ጋር እንዲፋለሙ ማሰማራት ካሉ አማራጮች ውጪ መሆኑን ተናግረው ነበር።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከከፈተች ከሳምንት በኋላ የፕሬዝዳንት ባይደን አስተዳደር በፕሬዝዳንት ፑቲን እና በሩሲያ ላይ እጅግ ጠንካራ የሚባሉ የማዕቀብ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው።
ባለፉት ቀናት አሜሪካ ከሩሲያ በምትገዛው ነዳጅና የጋዝ ምርት ላይ ዕቀባ የታለች ሲሆን፣ ትናንት አርብ ደግሞ ከሩሲያ ወደ አሜሪካ በሚገቡ የአልኮል መጠጦች፣ የባሕር ምግቦችና የአልማዝ ምርቶች ላይ ክልከላ ጥላለች።
በተጨማሪም በግለሰብ ደረጃ ከሩሲያ መንግሥት ጋር የቀረበ ግንኙነት አላቸው በተባሉ በርካታ ቁጥር ባላቸው ሩሲያውያን ከበርቴዎች ላይ ደግሞ ማዕቀብ ትጥላለች ተብሏል።
የዩክሬን ጦርነት የምግብ ሰብሎች ዋጋን አስከ 20 በመቶ ያንራል ተባለ
ዩክሬን ውስጥ እየተካሄደ ባለው ጦርነት ምክንያት የዓለም የምግብ ዋጋ ላይ በስምንት እና በ20 በመቶ መካከል የሚሰላ የዋጋ ንረት ሊያጋጥም እንደሚችል የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት አስታወቀ።
የተባበሩት መንግሥታት የምግብና እርሻ ድርጅት ሩሲያ በዩክሬን ላይ የፈጸመችውን ወረራ ተከትሎ ባደረገው የመጀመሪያ ደረጃ ግምገማ ሊራዘም ይችላል በተባለው ጦርነት ምክንያት በዩክሬን ምርት ለመሰብሰብ የሚያስችል ዕድል ስለመኖሩ እርግጠኛ አለመሆኑን አመልክቷል።
ከዩክሬን በተጨማሪም ከሩሲያ በኩል ለዓለም ገበያ የሚቀርበውን የምግብ ምርት በተመለከተ አስተማማኝ ሁኔታ እንደሌለ ድርጅቱ ገልጿል።
ድርጅቱ ባደረገው ግምገማ በዩክሬን ውስጥ በመደበኛ ሁኔታ ከሚሰበሰው ወይም ከሚለማው የጥራጥሬ፣ የበቆሎ እና የሱፍ አበባ ሰብል ውስጥ ከ20 አስከ 30 በመቶ የሚደርሰው ላይገኝ እንደሚችል አመልክቷል።
ሩሲያ የስንዴ ምርትን ለዓለም በማቅረብ ቀዳሚዋ አገር ስትሆን ዩክሬን ደግሞ በአምስተኛ ደረጃ ስንዴ አምራች እና ላኪ ናት።
በተጨማሪም ሁለቱ አገራት በጋር 19 በመቶ የገብስ ምርት፣ 14 በመቶ ስንዴ እና 4 በመቶ በቆሎ በማምረት የዓለምን አንድ ሦስተኛ የጥራጥሬ ምርት አቅራቢ መሆናቸውን ድርጅቱ ገልጿል።
ጦርነቱ በምግብ ምርቶች ላይ ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ከማስከተሉ ባሻገር ባለንበት እና በሚቀጥለው የፈረንጆች ዓመት በዓለም ዙሪያ ያሉ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት የሚጎዱ ሰዎች ቁጥር በስምንት ሚሊዮን ጨምሮ ወደ 12 ሚሊዮን እንደሚያሻቅብ ድርጅቱን ጠቅሶ ሮይተርስ ዘግቧል።
ከ70 በላይ ኢትዮጵያውያን ከዩክሬን ወደ ፖላንድ መግባታቸው ተነገረ
ዩክሬን ውስጥ የተከሰተውን ጦርነት ተከትሎ ከ70 በላይ ኢትዮጵያውያን የጎረቤት አገር ፖላንድን ድንበር አቋርጠው መግባታቸውን በኢትዮጵያ የፖላንድ ኤምባሲ አስታወቀ።
ኤምባሲው ዛሬ ባወጣው መግለጫ እንደገለፀው የሩሲያ ሠራዊት በዩክሬን ላይ ወረራ ከከፈተ በኋላ ጦርነቱን የሸሹ ከ1.5 ሚሊዮን በላይ ዜጎች ወደ ፖላንድ መግባታቸውን ጨምሮ አስታውቋል።
ከዚህ በተጨማሪ ኤምባሲው ከ1 ሺህ 500 በላይ ኢትዮጵያውያን በፖላንድ ትምህርታቸውን እየተከታተሉ መሆኑን በመግለጫው ላይ ተገልጿል።
ፖላንድ ከዩክሬን የሚመጡ ስደተኞች የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኙ ለማድረግ በርካታ ስደተኛ መቀበያ እና ማስተናገጃ ጣቢያዎችን በመክፈት እየተቀበለች መሆኑን ኤምባሲው ጨምሮ አመልክቷል።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ጦርነት መክፈቷን ተከትሎ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ዩክሬንን ለቅቀው ወደ ጎረቤት አገራት እየሸሹ ነው።
ከዩክሬን ዜጎች በተጨማሪ በአገሪቱ ውስጥ የሚገኙ በርካታ አፍሪካውያን ተማሪዎችም ከጦርነቱ ለመራቅ በባቡርና በመኪና ወደ ድንበር አካባቢዎች ለመሄድ ጥረት ቢያደርጉም፣ በዩክሬን እና በፖላነድ ድንበር አቅራቢያ በቆዳ ቀለማቸው ምክንያት መድልዎ እንደገጠማቸው ይናገራሉ።
ፑቲን ከመካከለኛው ምሥራቅ የሚመጡ ለሩሲያ መዋጋት ይችላሉ አሉ
የሩሲያው ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን ከመካከለኛው ምሥራቅ የሚመጡ እና ፍቃደኛ የሆኑ ሰዎች ለሩሲያ መዋጋት ይችላሉ አሉ።
ፑቲን፤ ገንዘብ ሳይከፈላቸው ለሩሲያ መዋጋት የሚፈልጉ ሰዎች አሉ ካሉ በኋላ፤ “እነዚህን ሰዎች ወደ ጦር ግንባር በመላክ ማድረግ የሚፈልጉትን መተባበር አለብን” ብለዋል።
የሩሲያ መከላከያ ሚኒስትር ሰርጌይ ሾይጉ ከመካከለኛው ምሥራቅ ተነስተው በዶንባስ ግዛት ከሩሲያ ጦር ጎን መሰለፍ የሚፈልጉ 16 ሺህ ሰዎች አሉ ሲሉ ለፑቲን መናገራቸውን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።
ከዚህ ቀደም የሶሪያ ወታደሮች በሩሲያ መንግሥት እየተከፋላቸው በዩክሬን ሊዋጉ ይችላሉ የሚል መረጃ በስፋት ሲሰራጭ ነበር።
ባሻር አል-አሳድ ሕዝባዊ ተቃውሞ በተነሳባቸው ወቅት ከሩሲያ መንግሥት ጠንካራ ድጋፋ አግኝተው በሥልጣናቸው ላይ አሁንም ይገኛሉ።
ፑቲን ለፀጥታ ምክር ቤታቸው ምዕራባውያን “በግልጽ ዓለም አቀፍ ሕጎችን በመተላለፍ ተዋጊዎችን ለዩክሬን እየቀጠሩ ነው” ሲሉ ተናግረዋል።
ፌስቡክ እና ኢንስታግራም አመጽ ቀስቃሽ ንግግሮችን ‘በጊዜያዊነት’ ሊፈቅዱ ነው
ፌስቡክ እና ኢንስታግራምን የሚያስተዳድረው ሜታ፤ በዩክሬን ላይ የተፈጸመውን ወረራ ተከትሎ ግጭት ቀስቃሽ ንግግሮችን በተመለከተ የነበረውን ሕግ በጊዜያዊነት እንደሚቀይር አስታውቋል።
ሜታ፤ ግጭት ቀስቃሽ የሆኑ ንግግሮችን ‘ለተወሰነ ጊዜ’ እንደሚፈቅድ ያረጋገጠ ሲሆን፤ ለምሳሌ “ሞት ለወራሪው ሩሲያ” ብሎ መጻፍ በሜታ የአጠቃቀም ደንብ መሠረት የተፈቀደ ሆኗል።
ኩባንያው፤ የሩሲያ ንጹሃን ዜጎችን ዒላማ የሚያደርጉ አመጽ ቀስቃሽ ንግግሮችን ግን አልፈቅድም ብሏል።
ሮይተርስ የዜና ወኪል በጉዳዩ ላይ በሰራው ዘገባ፤ ሞት ለሩሲያ ፕሬዝደንት ቭላድሚር ፑቲን እና ሞት ለቤላሩሱ ፕሬዝደንት አሌክሳንደር ሉካሼንኮ የሚሉ ልጥፎች በበርካታ አገራት የተፈቀዱ ይሆናሉ።
ይህ የሩሲያ ወታደሮችን በተመለከተ የሜታ የፖሊስ ለውጥ የሚደረግባቸው አገራት አርሜኒያ፣ አዘርባጃን፣ ኢስቶኒያ፣ ጆርጂያ፣ ሃንጋሪ፣ ላቲቪያ፣ ሊቱዌኒያ፣ ፖላንድ፣ ሮማኒያ፣ ሩሲያ፣ ስሎቫኪያ እና ዩክሬን ናቸው።
ሩሲያ ከሃገር የሚወጡ ኩባንያዎችን ንብረቶች እወርሳለሁ ማለቷን አሜሪካ ተቃወመች
ሩሲያ ከሃገር የሚወጡት የምዕራባውያን ኩባንያ ንብረቶችን የሚቆጣጠር አስተዳዳሪ እፈልግላቸዋለሁ ማለቷን አሜሪካ ተቃወመች።
ሩሲያ ዩክሬን ላይ ወረራ መፈጸሟን ተከትሎ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በርካታ ግዙፍ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሥራቸውን እያቋረጡ ከሃገሪቱ ወጥተዋል።
ይህንንም ተከትሎ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ትናንት መንግሥታቸው ሩሲያን እየለቀቁ ያሉትን ኩባንያዎችን ንብረቶች ሊቆጣጠር እንደሚችል ገልጸዋል።
ፑቲን ከሩሲያ የሚወጡ ተቋማትን “የሚያስተዳድር ገለልተኛ አመራር” እንደምታቋቁም እንዲሁም “ድርጅቶቹን ሥራቸውን ለማስቀጠል ፈቃደኛ ለሆኑት” እንደምትሰጥም ተናግረዋል።
ይህን ተከትሎ የዋይት ሃውስ ቃል አቀባይ ጄን ሳኪ የፕሬዝደንት ፑቲንን ውሳኔ፤ “ማን አለብኝነት” ሲሉ ገልጸውታል።
“. . . ይህ ሩሲያ ለምዕራባውያኑ ኢንቨስትምንት እና ንግድ ደኅንነት ደንታ እንደሌላት ግልጽ መልዕክት ያስተላልፋል” ብለዋል ቃል አቀባይዋ።
የሩሲያ ወታደሮች ዳግም ኪዬቭ አቅራቢያ እየተሰባሰቡ መሆኑ ተገለጸ
የሩሲያ ጦር ዳግም ኪዬቭ አቅራቢያ ተደራጅተው እየተሰባሰቡ መሆኑን የሳተላይት ምስሎች አመለከቱ።
ይህም የሞስኮ ጦር ኪዬቭን ለመያዝ አዲስ ዝግጅት እያደረገ ስለመሆኑ የሚያሳይ ነው ተብሏል።
የሳተላይት ምስሎቹ ጦሩ በሰሜን ምዕራብ ባሉ ከተሞች አቅራቢያ ቦታ ይዘው አሳይተዋል።
ትናንት ሐሙስ አንድ የአሜሪካ መከላከያ ከፍተኛ የጦር መኮንን እንዳሉት የሩሲያ ጦር ባለፉት 24 ሰዓታት 5 ኪሎ ሜትሮች ያክል ወደ ኪዬቭ ገፍተዋል።
ከሩሲያ የሚወጡ የውጭ ድርጅቶች ንብረት ሊወሰድ እንደምትችል ፑቲን ተናገሩ
የሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን መንግሥታቸው አገራቸውን ጥለው የሚወጡ የውጭ ኩባንያዎችን ንብረት ልትወስድ እንደምትችል ተናገሩ።
ፑቲን በመሩትና ዛሬ ሐሙስ ከሰዓት በኋላ በቴሌቪዥን በተላለፈ ስብሰባ ላይ ሠራዊታቸው ዩክሬን ውስጥ እያካሄደ ባለው ዘመቻ ምክንያት በአገራቸው ላይ ከምዕራባውያን በኩል እየደረሰ ያለውን ጫና አንስተዋል።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ መፈጸሟን ተክትሎ ምዕራባውያን እጅግ ጠንካራ ምጣኔ ሀብታዊ ማዕቀቦችንና እርምጃዎችን እየወሰዱ መሆናቸው ይታወቃል።
ከዚሁ ጋር ተያይዞም በርካታ የምዕራባውያኑ ዓለም አቀፍ ተቋማት ምርትና አገልግሎታቸውን እያቋረጡ ሩሲያን እየለቀቁ በመውጣት በአገሪቱ ምጣኔ ሀብት ላይ ጫናን እያሳረፉ ነው።
ይህንንም ተከትሎ ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ዛሬ እንዳሳወቁት መንግሥታቸው ሩሲያን እየለቀቁ ያሉትን ኩባንያዎችን ንብረቶች ሊቆጣጠር እንደሚችል ገልጸዋል።
ፕሬዝዳንቱ ጨምረውም ሩሲያ የምርት ተቋማቱን እየዘጉ የሚሄዱ ድርጅቶችን “የሚያስተዳድር ገለልተኛ አመራር” እንደምታቋቁም እንዲሁም “ድርጅቶቹን ሥራቸውን ለማስቀጠል ፈቃደኛ ለሆኑ” እንደምትሰጥም ተናግረዋል።
ይህንንም ለማድረግ የሚያስችል "ሕጋዊ መንገዶችን እንደሚፈልጉ” ገልጸዋል።
ሩሲያ ዩክሬን ላይ ወረራ መፈጸሟን ተከትሎ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በርካታ ግዙፍ ዓለም አቀፍ ተቋማት ሥራቸውን እያቋረጡ ከአገሪቱ ወጥተዋል።
ሩሲያ ወደ አሜሪካ እና አውሮፓ በምትልካቸው ምርቶች ላይ ማዕቀብ ጣለች
ጋናዊው ባለሀብት ቼልሲን በ3.1 ቢሊዮን ዶላር ሊገዙ እንደሆነ ተዘገበ
ሩሲያ እና ዩክሬን በሰብዓዊ ጉዳዮች ለመስራት መስማማታቸው ተገለጸ
የሩሲያና የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ቱርክ አንታሊያ ውስጥ ባደረጉት ውይይት በሰብአዊ ጉዳዮች ላይ የተስማሙ ሲሆን፣ ጦርነቱን ለማስቆም የሚያስችል ነገር ሳይገኝ ቀርቷል።
የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሚትሮ ኩሌባ ከሩሲያ አቻቸው ሰርጌይ ላቭሮቭ ጋር ከተነጋገሩ በኋላ መግለጫ ሰጥተዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ሁለቱ አገራት በዩክሬን ያለው የሰብዓዊ ጉዳዮች ላይ በጋራ ለመስራት ተስማምተናል ብለዋል። ሰርጌይ ላቭሮቭም ከንግግሩ በኋላ በሰጡት መግለጫ፤ ይህኑን አረጋግጠዋል።
የሩሲያ እና የዩክሬን ከፍተኛ ባለሥልጣናት የቱርኩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በተገኙበት ቢነጋገሩትም ጉልህ ከሆነ ስምምንት ላይ እንዳልደረሱ ተመልክቷል።
ኩሌባ ወደፊት “ምናልባት ለችግሮች መፍትሄ መሰጥት የሚችል ንግግር ካለ” ለመገናኘት ዝግጁ ነን ብለዋል።
በቀጣይ ንግግር ላይ የሰላም እና የደኅንነት ጉዳዮች ዙሪያ እንነጋገራለን ብለን ተስፋ እናደርጋል ብለዋል ኩሌባ።
ላቭሮቭ በበኩላቸው የዩክሬን መንግሥት ንፁሃን ዜጎችን ለጦርነት እያጋለጡ ነው ያሉ ሲሆን፤ ሩሲያ ዩክሬን ውስጥ እያካሄደች ያለችው፤ “ልዩ ኦፕሬሽን በተቃደለት መልኩ እየተካሄደ ነው” ብለዋል።
ላቭሮቭ ምዕራባውያን ለዩክሬን የጦር መሳሪያ እያቀረቡ፤ “አደገኛ እርምጃዎችን እየወሰዱ ነው” ያሉ ሲሆን፤ ይህም የአገራትን ‘መርህ እና እሴት’ የሚጥስ ነው ብለዋል።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ከዩክሬን ውጪ በሌሎች አገራት ላይ ወረራ ይሰነዝሩ እንደሆነ ሲጠየቁ፤ ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ አለመፈጸሟን እና በሌላ አገር ላይ የሚከናወን ወታደራዊ እርምጃ አለመኖሩን ገልጸዋል።
ሮማን አብራሞቪች በዩኬ መንግሥት እቀባ ተጣለባቸው
የሩሲያ እና የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ተገናኙ
የሩሲያ እና የዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትሮች በቱርክ ለንግግር ተቀምጠዋል።
ከሩሲያው ሰርጌይ ላቭሮቭ እና ከዩክሬኑ አቻቸው ዲሚትሮ ኩሌባ ጋር የቱርክ የውጭ ጉዳይ ሚኒሰትር ሜቭሉ ቻቪሶሉ ተገኝተዋል።
ከዚህ ቀደም የቱርክ ፕሬዝደንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶሃን ሁለቱን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ያደራድራሉ ተብሎ በስፋት ተዘግቦ ነበር።
ፕሬዝደንት ኦርዶሃንም ሁለቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች በቱርክ በሚያደርጉት ንግግር ‘ከዘላቂ የተኩስ አቁም ስምምነት ይደርሳሉ ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ’ ብለው ነበር።
ሩሲያ በዩክሬን ላይ ወረራ ከፈጸመች በኋላ ከፍተኛ የሃገራቱ ባለስልጣናት ፊት ለፊት ሲገናኙ ይህ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።