በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 16 ሺህ እየተጠጋ ነው

በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ የማህበረሰብ ስርጭት በፍጥነት እየተስፋፋ ነው። በዛሬው ዕለት ቫይረሱ እንዳለባቸው በምርመራ የተረጋገጠውን 610 ሰዎች ጨምሮ በአጠቃላይ በአገሪቱ በቫይረሱ መያዛቸው የታወቀው ሰዎች ቁጥር ወደ 16 ሺህ እየተጠጋ ነው። ። ቫይረሱ በስፋት እየተሰራጨ ካለባች ከተሞች ደግሞ ቀዳሚውን የምትይዘው ዋና መዲናዋ አዲስ አበባ ስትሆን፣ እስከ አሁን በዋና መዲናዋ ብቻ 10ሺህ 703 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ታውቋል። ከአዲስ አበባም ኮቪድ-19 ይበልጥ እየተሰራጨባቸው የሚገኙት ክፍለ ከተሞች ቦሌ (1652 ሰዎች)፣ አዲስ ከተማ (1329 ሰዎች) እንዲሁም ጉለሌ (1308 ሰዎች) ናቸው። የሕክምና ባለሙያዎች በተደጋጋሚ እንደሚሉት በህብረተሰቡ ዘንድ የሚታየው ቸልተኝነት ለወረርሽኙ በስፋት መሰራጨት አስተዋጽኦ አድርጓል። እናም አሁንም ቢሆን አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ ማስክ ማድረግና እጅን መታጠብ ላይ መዘናጋት ዋጋ ያስከፍላል።

የቀጥታ ሽፋን

  1. በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 16 ሺህ እየተጠጋ ነው

  2. ማኅበረሰቡ ከኮቪድ-19 ራሱን ከመጠበቅ ተዘናግቷል፡ የተለያዩ ከተማ ነዋሪዎች

  3. እስካሁን ኮሮናቫይረስ ያልተገኘባት አፍሪካዊቷ አገር ለመጀመሪያ ጊዜ ህሙማን አስመዘገበች

    ምዕራባዊ ሰሀራ እስካሁን ኮሮናቫይረስ ያልተገኘባት አገር የነበረች ሲሆን፤ ለመጀመሪያ ጊዜ አራት ግለሰቦች ላይ ቫይረሱ እንደተገኘ ይፋ አድርጋለች።

    አገሪቱ በአፍሪካ ሕብረት 55ኛዋ አገር ሆና የተመዘገበች ቢሆንም፤ ሞሮኮ ግን ዌስተርን ሰሀራ የግዛቴ አካል ነች ትላለች።

    በመላው አህጉሪቱ በበሽታው የተያዙ ሰዎች 750,000 እንደደረሱና ከ15,000 በላይ ሰዎች እንደሞቱ የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።

    በሁሉም የአፍሪካ አገራት ወረርሽኙ ተገኝቷል። የዓለም ጤና ድርጅት በበሽታው የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረ ነው ሲል አስጠንቅቋል።

  4. በሩስያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ከ800 ሺህ አለፉ

    በሩስያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ800 ሺህ ማለፉ ተገለጸ።

    የአገሪቱ የኮሮናቫይረስ መከላከል ግብረ ሀይል እንዳለው እስካሁን 800,849 ሰዎች በኮቪድ-19 ሲያዙ 3,046 ሰዎች ደግሞ ህይወታቸው አልፏል።

    588,774 ሰዎች ከበሽታው አገግመዋል።

  5. አውስትራሊያ በመቶ ዓመት ያልታየ የሕዝብ ቁጥር መቀነስ ሊገጥማት ነው

    አውስትራሊያ ላለፉት 100 ዓመታት ባልታየ ሁኔታ የሕዝብ ቁጥር መቀነስ ሊገጥማት እንደሆነ ተገለጸ።

    የሕዝብ ቁጥር እድገቱ ከ2 በመቶ ወደ 0.6 በመቶ የሚቀንስ ሲሆን፤ ምክንያቱ የአገሪቱ ድንበር መዘጋቱና ስደተኞች እየገቡ አለመሆኑ ነው ተብሏል።

    በሌላ በኩል አገሪቱ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ወዲህ ባልታየ ሁኔታ የምጣኔ ኃብት ውድቀት ገጥሟታል። 488 ቢሊዮን ዶላር የመንግሥት እዳ ከአገሪቱ አጠቃላይ ምርት አንድ አራተኛውን ይይዛል።

    አሁን ላይ በሜልቦርን እና በሲድኒ ከተሞች የበሽታውን ስርጭት ለመግታት ጥረት እየተደረገ ይገኛል።

    ቫይረሱ ካለባቸው ሰዎች ጋር ንክኪ ያላቸውን ሰዎች ለማግኘት ተጨማሪ ሁለት ሺህ ወታደሮች በሜልቦርን እንደሚሰማሩ ተነግሯል።

  6. ቦሊቪያ ለሁለተኛ ጊዜ ምርጫ አራዘመች

    ቦሊቪያ በኮሮናቫይረስ ስርጭት ስጋት አጠቃላይ ምርጫ ለሁለተኛ ጊዜ አራዘመች።

    ቦሊቪያ ኮሮናቫይረስ በተቀሰቀሰበት ወቅት ምርጫውን አራዝማ ነበር። የተራዘመው ቀን ደግሞ በቦሊቪያ የቫይረሱ ስርጭት ጫፍ የሚደርስበት ወቅት እንደሚሆን በመተንበዩ አጠቃላይ ምርጫው ለሁለተኛ ጊዜ እንዲራዘም ግድ ሆኗል።

    የአገሪቱ ባለስልጣናት በወረሃ ነሐሴ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ደረጃ ላይ ይደርሳል ብለዋል።

    ባለስልጣናት ለሁለተኛ ጊዜ የተራዘመው ምርጫ ጥቅም 8 ይካሄዳል ብለዋል።

    የቦሊቪያ ተጠባባቂ ፕሬዝደንት ጄዓኒኔ አኔዝ ከሁለት ሳምንታት በፊት በኮሮናቫይረስ መያዛቸው ተረጋግጦ ነበር።

    በደቡብ አሜሪካዋ አገር ቦሊቪያ እስካሁን ከ2400 በላይ ሰዎች ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን 65ሺህ ገደማ ሰዎች ደግሞ እስካሁን በቫይረሱ ተይዘዋል።

  7. ደቡብ አፍሪካ የሕዝብ ትምህርት ቤቶችን ዘጋች

    በደቡብ አፍሪካ በኮቪድ-19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር መጨመሩን ተከትሎ የሕዝብ ትምህርት ቤቶች ለአራት ሳምንታት ተዘጉ።

    ፕሬዘዳንት ሲሪል ራማፎሳ፤ ትምህርት ቤቶች የቫይረሱ መሰራጫ መሆን የለባቸውም ብለዋል። የመጀመሪያና የሁለተኛ ደረጃ ተማሪዎች ወደ ትምህርት የተመለሱት ሐምሌ ስድስት ነበር። “የባለድርሻ አካላትና የባለሙያዎችን ምክር ከግምት በማስገባት ትምህርት ቤቶች ለቀጣይ አራት ሳምንታት እንዲዘጉ ተወስኗል” ብለዋል ፕሬዘዳንቱ።

    የዘንድሮው ትምህርት በወረርሽኙ ሳቢያ ስለተቆራረጠ በቀጣዩ ዓመት እንደሚሰጥም ተናግረዋል።

    በሌላ በኩል ለጤና ዘርፉ 30 ቢሊዮን ዶላር መመደቡን ራማፎሳ አስታውቀዋል።

  8. የዓለም ጤና ድርጅት የፖምፔዮን አስተያየት አጣጣለ

    የዓለም ጤና ድርጅት፤ የአሜሪካው የውጪ ጉዳይ ኃላፊ ማይክ ፖምፔዮ የዓለም ጤና ሥርዓት በቻይና “ቁጥጥር ስር ነው” ማለታቸውን አጣጣለ።

    የድርጅቱ ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም፤ የፖምፔዮ ክስ “ሐሰተኛ፣ ተቀባይነት የሌለው እና መሠረተ ቢስ ነው” ብለዋል።

    ዶ/ር ቴድሮስ “በዚህ አስተያየት መስመራችንን አንስትም” ብለዋል።

    አሜሪካ በተደጋጋሚ የዓለም ጤና ድርጅትን ወቅሳለች። ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ እንደሚሉት፤ ድርጅቱ ቻይናን ለወረርሽኙ ተጠያቂ ሳያደርግ ቀርቷል።

    ከወራት በፊት “ቻይና የዓለም ጤና ድርጅትን ሙሉ በሙሉ ትቆጣጠራለች” ማለታቸውም ይታወሳል።

  9. ቶኒ ብሌር ኮሮናቫይረስ ስለማይጠፋ 'ከቫይረሱ ጋር አብሮ መኖርን መማር ይኖርብናል' አሉ

    የቀድሞ የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚንሰትር ቶኒ ብሌር ኮሮናቫይረስ ከምድራችን ስለማይጠፋ ከቫይረሱ ጋር እንዴት አብረን መኖር እንደምንችል መማር ይኖርብናል አሉ።

    የቀድሞ ጠቅላይ ሚንስትር ከፕሬስ አሶሲዬሽን ጋር በነበራቸው ቃለ መጠይቅ በዩኬ ቫይረሱ በሁለተኛ ዙር እንደ ወረርሽኝ ሊቀሰቀስ የሚችልበት አጋጣሚ '50/50' ነው ብለዋል። ለዚህም መንግሥት እና ሕዝቡ ዝግጅት ማድረግ ይኖርባቸዋል ብለዋል።

    ቶኒ ብሌር ቫይረሱ ዳግም ስርጭቱ ቢያይል ከዚህ ቀደም ወዳለፍንበት የእንቅስቃሴ ገደብ መግባት ስለማንችል መንግሥት ሌሎች የቫይረሱን ስርጭት የሚገቱ አማራጮችን በጥንቃቄ ማጤን ይኖርበታል ብለዋል።

    በቀድሞው ጠቅላይ ሚንስትር የሚመራ ተቋም፤ የጅምላ የኮሮናቫይረስ ምርመራ እንዲደረግ እና ሕዝብ በሚሰበሰብበት ቦታ የፊት እና አፍ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግ ግዴታ መሆን አለበት የሚሉ ምክረ ሃሳቦችን ለግሷል።

  10. በብራዚል በአንድ ቀን ከ67ሺህ በላይ ሰዎች ቫይረሱ ተገኘባቸው

    በብራዚል በአንድ ቀን ቫይረሱ እንዳለባቸው የተረጋገጡ ሰዎች ቁጥር ከ67 ሺህ አልፏል። ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በበሽታው ምክንያት መሞታቸውንም የጤና ሚንስትር ሪፖርት አድርጓል።

    በአገሪቱ በሽታው እንዳለባቸው የተረጋገጡ ሰዎች ቁጥር 2.2 ሚሊዮን ደርሷል። ከአሜሪካ ቀጥሎ በሽታው ክፉኛ ያጠቃት አገር ብራዚል ናት።

    ጥቂት የጤና ባለሙያ በሚገኝባቸው አነስተኛ የገጠር ከተሞች በሽታው እየተዛመተ ይገኛል። ቀደምት ማኅበረሰቦች በዋነኛነት ጉዳት እየደረሰባቸው ነው።

  11. በሕንድ በኮቪድ-19 ለይቶ ማቆያ ወሲባዊ ጥቃት ደረሰ

    በሕንድ መዲና ደልሂ በኮሮናቫይረስ ለይቶ ማቆያ ውስጥ የ14 ዓመት ታዳጊ ላይ ወሲባዊ ጥቃት ደረሰ። ታዳጊዋ ጥቃት የደረሰባት በሌላ ታካሚ ነው ተብሏል።

    ተጠርጣሪው የ19 ዓመት ግለሰብና ጥቃቱን በቪድዮ የቀረጸው ሌላ ወንድ በፖሊስ ቁጥጥር ስር ውለዋል።

    ሦስቱም ኮሮናቫይረስ የተገኘባቸው ሲሆን፤ መጠነኛ ምልክት ስለሚያሳዩ ነበር ለይቶ ማቆያ የገቡት። ማቆያው በሕንድ ከሚገኙ ማዕከሎች ትልቁ ሲሆን፤ 10 ሺህ አልጋዎች አሉት።

    ጥቃቱ የተፈጸመው ሐምሌ 15 መጸዳጃ ቤት ውስጥ ነበር።

    ታዳጊዋ ጥቃት እንደደረሰባት በዛው ማዕከል ለሚገኝ ቤተሰቧ ካሳወቀች በኋላ ኃላፊዎች እንዲያውቁት ተደርጓል።

  12. ትራምፕ በኮሮናቫይረስ ስጋት የሪፐብሊካኖቸን መድረክ ሰረዙ

    የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኮሮናቫይረስ ስጋት በፍሎሪዳ ሊካሄድ የነበረውን የሪፐብሊካኖች መድረክ ሰረዙ።

    ትራምፕ መድረኩን የሰረዙት “አሁን ጊዜው አይደለም” በማለት ነበር። ፕሬዘዳንቱ በሌላ መንገድ ንግግራቸውን እንደሚያስተላልፉ ገልጸዋል።

    በአሜሪካ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከአራት ሚሊዮን ማለፉ ተዘግቧል።

    አንዳንድ የሪፐብሊካን ወኪሎች በሻርሎት፣ ኖርዝ ካሮላይና ይሰበሰባሉ። መድረኩ መጀመሪያ ሊካሄድ በታቀደበት ቦታ እንደሚገኙም ተገልጿል።

    ትራምፕ መድረኩን በከፊል ወደ ፍሎሪዳ ያዘዋወሩት በኖርዝ ካሮላይና በወጣው አካላዊ ርቀት የመጠበቅ ሕግ ምክንያት ነበር።

    ነሐሴ 24 በሚካሄደው የግማሽ ቀን ሥነ ሥርዓት ፕሬዘዳንቱ በፓርቲያቸው በይፋ እጩ ተደርገው ይቀርቡ ነበር።

  13. በአሜሪካ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ4 ሚሊዮን ተሻገረ

    በኮሮናቫይረስ ክፉኛ በተጠቃችው አሜሪካ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ4 ሚሊዮን ተሻግሯል።

    ከጆንስ ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ የተገኘው መረጃ እንደሚያሳያው፤ በአሜሪካ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 4,034,102 ነው።

    ካሊፎርኒያ፣ ኒው ዮርክ፣ ፍሎሪዳ፣ ቴክሳስ እና ኒው ጀርሲ እንደየቅደም ተከተላቸው በቫይረሱ የተያዙ በርካታ ሰዎች የሚገኙባቸው የአሜሪካ ግዛት ናቸው።

    ከአሜሪካ በመቀጠል ብራዚል እና ሕንድ በቫይረሱ ክፉኛ ተጠቅተዋል።

    ብራዚል 2,227,514 እንዲሁም ሕንድ 1,238,798 ዜጎቻቸው በኮቪድ-19 ተይዘዋል።

  14. እንደምን አደራችሁ?

    እንዴት አደራችሁ ውድ የቢቢሲ አማርኛ ወዳጆች?

    በቀጥታ ስርጭት ገጻችን ከአሁኗ ሰዓት ጀምሮ ከአገር ውስጥ እና ከተቀረው ዓለም ከቫይረሱ ስርጭት ጋር የተያያዙ መረጃዎችን ወደ እናንተ እናደርሳለን።

    ድረ-ገጻችንን እና የፌስቡክ ገጻችንን መጎብኘት አይዘንጉ።

    መልካም ቀን!