በኢትዮጵያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ወደ 16 ሺህ እየተጠጋ ነው

በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ የማህበረሰብ ስርጭት በፍጥነት እየተስፋፋ ነው። በዛሬው ዕለት ቫይረሱ እንዳለባቸው በምርመራ የተረጋገጠውን 610 ሰዎች ጨምሮ በአጠቃላይ በአገሪቱ በቫይረሱ መያዛቸው የታወቀው ሰዎች ቁጥር ወደ 16 ሺህ እየተጠጋ ነው። ። ቫይረሱ በስፋት እየተሰራጨ ካለባች ከተሞች ደግሞ ቀዳሚውን የምትይዘው ዋና መዲናዋ አዲስ አበባ ስትሆን፣ እስከ አሁን በዋና መዲናዋ ብቻ 10ሺህ 703 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ታውቋል። ከአዲስ አበባም ኮቪድ-19 ይበልጥ እየተሰራጨባቸው የሚገኙት ክፍለ ከተሞች ቦሌ (1652 ሰዎች)፣ አዲስ ከተማ (1329 ሰዎች) እንዲሁም ጉለሌ (1308 ሰዎች) ናቸው። የሕክምና ባለሙያዎች በተደጋጋሚ እንደሚሉት በህብረተሰቡ ዘንድ የሚታየው ቸልተኝነት ለወረርሽኙ በስፋት መሰራጨት አስተዋጽኦ አድርጓል። እናም አሁንም ቢሆን አካላዊ ርቀትን መጠበቅ፣ ማስክ ማድረግና እጅን መታጠብ ላይ መዘናጋት ዋጋ ያስከፍላል።

የቀጥታ ሽፋን

  1. “በዚህ ዓመት ሕይወት ወደ ቀደሞ ገጽታው አይመለስም”

    የአሜሪካው የተላላፊ በሽታዎች ባለሙያ ዶ/ር አንቶኒ ፋውቺ፤ በዚህ ዓመት ሕይወት ወደ ቀድሞ ገጽታው አይመለስም አሉ።

    በዚህ ዓመት መጨረሻ ላይ ክትባት ቢገኝ እንኳን ለማከፋፈል እስከሚቀጥለው ዓመት መጨረሻ ድረስ ጊዜ እንደሚወስድ ተናግረዋል።

    “ክትባት መሥራቱ ወይም ውጤታማ አለመሆኑ የሚታወቀው በሙከራ ነው። በሚቀጥለው ሳምንት ሦስት ሙከራዎች ይከናወናሉ። በሌሎች አገሮችም ምርምር እየተደረገ ነው” ብለዋል።

    2021 ገብቶ ከወራት ቆይታ በኋላ ክትባት በአሜሪካ መሰራጨት እንደሚችልም ዶ/ር ፋውቺ ተናግረዋል።

  2. በበይነ መረብ የሚካሄድ ኑዛዜ ተቀባይነት አገኘ

    ኮሮናቫይረስ በርካታ ሥራዎች በበይነ መረብ እንዲከናወኑ ምክንያት ከሆነ ሰነባብቷል።

    ስብሰባና ትምህርት የሚካሄደው፣ ወዳጅ ዘመድ የሚጠያየቀውም እንደ ዙምና ፌስታይም ባሉ መተግበሪያዎች አማካይነት ነው።

    አሁን ደግሞ የዩናይትድ ኪንግደሞቹ እንግሊዝ እና ዌልስ በበይነ መረብ ለሚደረግ ኑዛዜ ሕጋዊ እውቅና ሰጥተዋል።

    ከበሽታው ራስን ለመከላከል አካላዊ ርቀትን መጠበቅ የግድ በመሆኑ ሰዎች ኑዛዜ እያካሄዱ ያሉት በበይነ መረብ ነው።

    ይህ የኑዛዜ ማስተላለፊያ መንገድ እስከ ጎርጎሮሳውያኑ 2022 ድረስ ተቀባይነት እንዳለው ተገልጿል።

  3. ጭምብል የሚያደርጉት በትክክል ነው?

    የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት መወሰድ ካለባቸው ርምጃዎች አንዱ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማድረግ ነው።

    አገራት፤ በሕዝብ መጓጓዣዎች፣ በመደብሮች እንዲሁም ሰው በሚበዛባቸው ሌሎችም አካባቢዎች ጭምብል ማድረግን አስገዳጅ እያደረጉ ነው።

    ሆኖም ግን አፍና አፍንጫቸውን በአግባቡ የማይሸፍኑ በርካቶች ናቸው።

    ጭምብልን አገጭ ላይ ማድረግ፣ አፍንጫን ከጭምብል አውጥቶ አፍን ብቻ መሸፈን በተደጋጋሚ የሚስተዋሉ ስህተቶች ናቸው።

    የጤና ባለሙያዎች እንደሚሉት፤ ቫይረሱ በአፍ ወይም በአፍንጫ በኩልም ስለሚገባ በጭምብል መሸፈን ተገቢ ነው።

    አንዳንዶች ከሰው ጋር ሲያወሩ ጭምብላቸውን ያወልቃሉ። ይህም ስህተት ነው። አካላዊ ርቀት መጠበቅ በማይቻልበት አካባቢ ጭምብል ማድረግ ይመከራል።

    ጭምብል ከማድረግዎ በፊት እንዲሁም ከማውለቅዎ በፊትም እጅዎን በውሃና በሳሙና መታጠብ አለብዎት። ጭምብልዎን በማይጠቀሙበት ወቅት ንጹህ ቦታ ማስቀመጥም አይዘንጉ።

  4. ዶ/ር ፋውቺ በእርሳቸው እና በቤተሰባቸው ላይ ማስፈራሪያ እየደረሰ ነው አሉ

    የተላላፊ በሽታ እና አለረጂ ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት እውቁ የጤና ባለሙያ ዶ/ር አንቶኒ ፋውቺ የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት በሚደረገው ጥረት በሚሰጡት የባለሙያ አስተያየት እና ምክረ ሐሳብ የተለያዩ ማስፈራሪያዎች እየደረሷቸው እንደሆነ ተናገሩ።

    ዶ/ር ፋውቺ ለሲኤንኤን ሲናገሩ፤ በእርሳቸው እና በቤተሰባቸው ላይ የሚደርሱ ማስፈራሪያዎች እየተበራከቱ ነው ብለዋል።

    ዶ/ር ፋውቺ በሙያቸው በሚሰጡት ምክረ ሐሰብ "የግል ሕይወታቸውን የተጋፋሁ መስሏቸው የሚበሳጩብኝ በርካታ ሰዎች ናቸው" ብለዋል።

    "በጣም ከባድ ነው። በእኔ ላይ፣ በባለቤቴ እና በሴት ልጆቼ ላይ እየደረሰ ያለው ማስፈራሪያ ከባድ ነው" ካሉ በኋላ፤ "በዚህች አሜሪካ ነው ይህ ሁሉ ማስፈራሪያ የሚደርሰው?" ሲሉ ጠይቀዋል።

  5. ሩሲያ ባለፉት 24 ሰዓታት ከ5ሺህ በላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን መዘገበች

    ሩሲያ ባለፉት 24 ሰዓታት በኮሮናቫይረስ የተያዙ 5,871 ሰዎችን መመዝገቧን ሬውተርስ ዘግቧል።

    ከዚህ በተጨማሪም በአንድ ቀን ውስጥ ከ146 ሰዎች በላይ ከኮቪድ-19 ጋር በተያያዘ ሕይወታቸውን አጥተዋል።

    እስካሁን በሩሲያ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 806,720 የደረሰ ሲሆን የሟቾች ቁጥር ደግሞ 13,192 ደርሷል።

  6. ፈረንሳይ የተለዩ ገቢ መንገደኞችን ልትመረምር ነው

    የፈረንሳይ የውጪ ጉዳይ ሚንሰትር ጄን ካስቴክስ ቫይረሱ ከተስፋፋባቸው 16 አገራት ወደ ፈረንሳይ የሚገቡ መንገደኞች የኮቪድ-19 ምርመራ ይካሄዳል ብለዋል።

    የፈረንሳይ መንግሥት ከዚህ ውሳኔ የደረሰው በአገሪቱ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ዳግም መጨመሩን ተከትሎ ነው።

    የአገሪቱ ጤና ሚንስቴር እንዳለው፤ በየቀኑ ከ1ሺህ በላይ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች እየተገኙ ነው።

    የውጪ ጉዳይ ሚንስትሩ ምርመራ የሚደረግላቸው ሰዎች የፈረንሳይ ዜጎች እና የፈረንሳይ ነዋሪ የሆኑ ከተለዩት 16 አገራት ለሚመጡት ብቻ ነው ብለዋል።

    ቫይረሱ የሚገኘባቸው ሰዎች ራሳቸውን ለ14 ቀናት ለይተው ያቆያሉ።

    ምርመራ የሚደረግባቸው ተጓዦች ከአሜሪካ፣ ብራዚል፣ አልጄሪያ፣ ባህሬን፣ እስራኤል፣ ሕንድ፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ኩዌት፣ ኳታር፣ የተባበሩት አረብ ኤሜሬቶች፣ ፓናማ፣ ኦማን፣ ፔሩ፣ ሰርቢያ፣ ቱርክ እና ማደጋስካር ናቸው።

    የአውሮፓ ሕብረት አገራትም ሆኑ ፈረንሳይ ከዜጎች እና ከቋሚ ነዋሪዎች ውጪ ሌሎች ተጓዦችን አይቀበሉም።

  7. በደቡብ ኮርያ የህሙማን ቁጥር ጨመረ

    ደቡብ ኮርያ 113 አዲስ ታማሚዎች በአንድ ቀን መዝግባለች። ይህም በሦስት ወራት ከተመዘገበው ከፍተኛው ነው።

    የጤና ባለሙያዎች እንዳሉት፤ አዲስ ከታመሙ ሰዎች አብዛኞቹ ከሌሎች አገሮች ወደ ደቡብ ኮርያ የገቡ ናቸው።

    ባለፈው አርብ በሁለት አውሮፕላን 300 ሰዎች ወደ ደቡብ ኮርያ ከገቡ በኋላ የህሙማን ቁጥር እየጨመረ መጥቷል።

    አውሮፕላኖቹ ኢራቅ ይኖሩ የነበሩ ደቡብ ኮርያውያንን የጫኑ ነበሩ።

    ከተሳፋሪዎቹ መካል 36ቱ ኮሮናቫይረስ የተገኘባቸው ሲሆን፤ 90ው ደግሞ ምልክት አሳይተዋል።

  8. ካታሎኒያ የቫይሱን ስርጭት ለመቆጣጠር የምሽት መዝናኛ ክበቦችን ዘጋች

    በሰሜን ምሥራቅ ስፔን የምትገኘው ካታሎኒያ የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር የምሽት መዝናኛ ክበቦችን መዝጋቷን አስታወቀች።

    የምሽት መዝናኛ ቤቶች ለሁለት ሳምንታት ዝግ ሆነው ይቆያሉ ተብሏል።

    ስፔን የቫይረሱን ስርጭት ለመቆጣጠር ጥላ የነበረውን የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ባነሳች በአንድ ወር ውስጥ በቫይሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ጨምሯል።

    መዲናዋ ማድሪድ፣ ባርሴሎና እና ዛራጎዛ ከተሞች በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከጨመረባቸው ከተሞች መካከል ተጠቃሽ ናቸው።

    የሰፔን ጤና ሚንስቴር ባለፉት 24 ሰዓታት ብቻ 900 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች መገኘታቸውን አስታውቋል።

    ፈረንሳይ ዜጎቿ ወደ ካታሎኒያ ግዛት እንዳያመሩ ያስጠነቀቀች ሲሆን ኖርዌይ በበኩሏ ከስፔን የሚገቡ መንገደኞችን ወደ ለይቶ ማቆያ ማስገባት መጀመሯን አስታውቃለች።

  9. ቫይረሱ በአንድ ቀን 284 ሺህ 196 ሰዎች ላይ ተገኘ

    በርካታ አገራት የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት ጥለው የነበረውን የእንቅስቃሴ ገደብ እያነሱ ቢሆንም፤ በዓለም አቀፍ ደረጃ ቫይረሱ የሚገኝባቸው ሰዎች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን የዓለም ጤና ድርጅት አስታውቋል።

    ባለፉት 24 ሰዓታት በሽታው የተገኘባቸው ሰዎች 284 ሺህ 196 ሲሆኑ፤ ይህም እስካሁን በአንድ ቀን ከተመዘገበው የህሙማን ቁጥር ከፍተኛው ነው።

    በወረርሽኙ ሳቢያ በአንድ ቀን የሞቱ ሰዎች 9,753 ደርሷል። ቁጥሩ ከሚያዝያ 30 ወዲህ ከፍተኛው ነው።

    በአንድ ቀን ከፍተኛ የህሙማ ቁጥር ያስመዘገቡት ተከታዮቹ ናቸው፦

    • አሜሪካ - 69,641
    • ብራዚል - 67,860
    • ሕንድ - 49,310
    • ደቡብ አፍሪካ - 13,104

    በአንድ ቀን ከፍተኛ የሟቾች ቁጥር ያስመዘገቡት አገራት ደግሞ የሚከተሉት ናቸው፦

    • ፔሩ - 3,876
    • ብራዚል - 1,284
    • አሜሪካ - 1,074
    • ሜክሲኮ - 790
    • ሕንድ - 740
  10. አየርላንድ የኮቪድ-19 ህሙማን መለያ መተግበሪያ እየተጠቀመች ነው

    የተለያዩ አገራት ኮቪድ-19 ከተገኘባቸው ሰዎች ጋር ንክኪ ላላቸው ሰዎች ጥቆማ የሚሰጥ መተግበሪያ እየተጠቀሙ ነው።

    በእርግጥ መተግበሪያው የሰዎችን ግላዊነት ሊጻረር ይችላል በሚል ቅሬታ የሚያሰሙም አሉ።

    በመተግበሪያ የኮቪድ-19 ህሙማንን ከሚከታተሉ አንዷ አየርላንድ ናት።

    መተግበሪያው ጥቅም ላይ በዋለ በሁለት ሳምንታት ውስጥ 91 ሰዎች ጥቆማ ደርሷቸዋል። ግለሰቦቹ በስልካቸው ጥቆማ የደረሳቸው ኮሮናቫይረስ እንዳለባቸው ከተረጋገጠ ሰዎች ጋር ንክኪ በማድረጋቸው ነው።

    መተግበሪያው እነዚህ ግለሰቦች የኮቪድ-19 ምርመራ እንዲያካሂዱም ጠቁሟል።

  11. እንግሊዝ ከ80 አገራት የሚገቡ መንገደኞች ወደ ለይቶ ማቆያ አላስገባም አለች

    የተለያዩ አገሮች ድንበራቸውን መክፈታቸውን ተከትሎ ወደ ግዛታቸው ሲገቡ ወደለይቶ ማቆያ የሚያስገቡት የየትኞቹ አገራት ዜጎችን እንደሆነ እየገለጹ ነው።

    ወደ ለይቶ ማቆያ የማስገባቱ ተግባር በበሽታው ክፉኛ ጉዳት ከደረሰባቸው አገራት የሚጓዙ ሰዎች ቫይረሱን እንዳያሰራጩ ለማድረግ ያለመ ነው።

    ለምሳሌ እንግሊዝ የኢስቶኒያ፣ ላቲቪያ፣ ስሎቫኪያ፣ ስሎቬንያ፣ ሴንት ቪንሰንት እና ግሪኒዳድስ ዜጎችን ለይቶ ማቆያ አታስገባም።

    በአጠቃላይ ከ80 አገራት ወደ እንግሊዝ የሚያቀኑ ሰዎች በአስገዳጅ ለይቶ ማቆያ እንደማይገቡ ተገልጿል።

    ዝርዝሩ ውስጥ ካልተካተቱ አገሮች አንዷ ፖርቹጋል ናት። የፖርቹጋል መንግሥት በውሳኔው ደስተኛ አለመሆኑንም አስታውቋል።

    የአገሪቱ የውጪ ጉዳይ ሚንስትር “ውሳኔው ትክክለኛ መረጃን የተመረኮዘ አይደለም” ብለዋል።

  12. ቬትናም በወረርሽኝ ስጋት የዱር እንስሳት ንግድ አቆመች

    ቬትናም አዲስ ወረርሽኝ እንዳይቀሰቀስ በመስጋቷ የዱር እንስሳት ምርቶችን ወደ አገሯ ማስገባት አቆመች። የዱር እንስሳት ገበያዎችም እንዲዘጉ ተወስኗል።

    ቬትናም ለባሕላዊ ህክምና የሚውሉት ፓንጎሊን እና የጎሽ ቀንድ ሲሸጥ ርምጃ አልወሰደችም በሚል በተደጋጋሚ ስትወቀስ ነበር።

    ሳይንቲስቶች እንደሚሉት፤ የዱር እንስሳት ንግድ የተለያዩ በሽታዎች መነሻ ሊሆን ይችላል።

    ኮቪድ-19ም የተነሳው በዱር እንስሳት ንግድ ሳቢያ እንደሆነ ይታመናል።

    በሽታው ከሌሊት ወፎች ወደ ሌላ እንስሳ ከዛም ወደ ሰዎች የዘለለ መሆኑ ተገልጿል። በሽታውን ከሌሊት ወፎች ወደ ሰው ልጀች ያስተላለፈው እንስሳ ምን እንደሆነ አልታወቀም። ምናልባትም አይጦች፣ ፓንጎሊን ወይም ሌላ እንስሳ አስተላልፈውታል የሚል መላ ምት አለ።

  13. ሀይድሮክሲክሎሮክዊን እንደማይሠራ የብራዚል ጥናት አሳየ

    የብራዚሉ ፕሬዘዳንት ዣቪር ቦልሶናሮ ኮሮናቫይረስን ያክማል ብለው በስፋት ሲያስተዋውቁት የነበረው ሀይድሮክሲክሎሮክዊን ውጤታማ እንዳላሆነ ጥናት አሳየ።

    በ55 ሆስፒታሎች መጠነኛ ምልክት በሚያሳዩ 667 ህሙማን ላይ ተሞክሮ መድኃኒቱ ፈዋሽ ሳይሆን እንዲያውም የጎንዮሽ ጉዳት የሚያስከትል መሆኑ ተደርሶበታል።

    የወባ መድኃኒት የሆነው እንክብሉ፤ ኮቪድ-19ንም ይፈውሳል የሚል መረጃ ሲናፈስ ነበር።

    በበሽታው የተያዙት ቦልሶናሮ መድኃኒቱን እየወሰዱ እንደሆነ ተናግረው፤ ሆስፒታሎች እንክብሉን ለህሙማን እንዲሰጡም ትዕዛዝ አስተላለፈዋል።

    የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕም ሀይድሮክሲክሎሮክዊን ከኮቪድ-19 ይፈውሳል ብለው እንደነበር ይታወሳል።

    ኦክስፎርድ የተሠራ ጥናት መድኃኒቱ ለኮሮናቫይረስ እንደማይሠራ ይፋ ማድረጉን ተከትሎ፤ የዓለም ጤና ድርጅት እንክብሉ ላይ የሚካሄዱ ምርምሮችን አግዷል።

  14. እንደምን አደራችሁ?

    ውድ የቢቢሲ አማርኛ ወዳጆች እንደምን አደራችሁ?

    የቀጥታ ዘገባችን ተጀምሯል። በዚህ ገጽ ከኮሮናቫይረስ ስርጭት ጋር የተያያዙ ወቅታዊ መረጃዎችን እናደርሳችኋለን።

    በአገራችን በኮሮናቫይረስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በፍጥነት መጨመሩ እንደቀጠለ ነው።

    ትናንት ብቻ 760 ሰዎች ሲያዙ በአጠቃላይ በአገሪቱ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 12 ሺህ 693 ደርሷል። በዚህ ሳምንት ከእሁድ ጀምሮ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥርን ብቻ ብንመለከት እንኳ 3ሺህ 190 ሰዎች በቫይረሱ ተጠቅተዋል።

    የቫይረሱን ስርጭት ለመግታተ ከጤና ባለሙያዎች የሚሰጡ መመሪያዎችን ሳንዘናጋ እንተግብር።

    መልካም ቅዳሜ!

  15. በደቡብ አፍሪካ ታራሚዎች ማረሚያ ቤቱን ሰብረው አመለጡ

    በደቡብ አፍሪካ በርካታ እስረኞች ከማረሚያ ቤት ያመለጡ ሲሆን "የተወሰኑትን በቁጥጥር ስር" ማዋሉን ፖሊስ ገልጿል።

    እስረኞቹ በምዕራባዊ ኬፕ ከሚገኝ እስር ቤት ያመለጡ ሲሆን አሁንም በርካቶች እየተፈለጉ መሆኑ ተገልጿል።

    በፍለጋው ላይ የተሰማሩት መርማሪዎችን ጨምሮ ሲሆን፣ በእግርና በመኪና አሰሳው ቀጥሏል ተብሏል። እስካሁን ድረስ ሰፊውን ክፍል የሸፈነ ፍለጋ የተካሄደ መሆኑን የፖሊስ ቃል አቀባይ ብርጋዲየር ኖቬላ ፖቴልዋ ገልፀዋል።

    ከማልሜስበሪ ማረሚያ ቤት ምን ያህል ታራሚዎች እንዳመለጡ የታወቀ ነገር ባይኖርም፣ በማህበራዊ ሚዲያ ላይ የሚሽከረከሩ ምስሎች በርካቶች ሲሮጡ ይታያል።

    በዓለም ላይ በርካቶች በእስር ቤት ስለሚገኙ ግለሰቦች ያላቸውን ስጋት ሲገልፁ፣ ንጽህናው ባልተጠበቀ ስፍራ እጅግ ተቀራርቦ መኖር፣ የኮሮናቫይረስ መከላከል መመሪያዎችን ተግባራዊ ለማድረግ ከባድ መሆኑን በመጥቀስ ስርጭቱ በማረሚያ ቤቶች እንዳይስፋፋ ያላቸውን ስጋት ይገልፃሉ።

    በግንቦት ወር የደቡብ አፍሪካ ፕሬዝዳንት ሲሪል ራማፎሳ 19,000 እስረኞች የኮቪድ-19 ስርጭትን ለመግታት በሚል እንደሚለቀቁ ተናግረው ነበር።

  16. ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በተደረገ ምርመራ 760 ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸው ተገለፀ

    ባለፉት 24 ሰዓታት ለ7264 ሰዎች ኮሮናቫይረስ ምርመራ ተደርጎ 760 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው መረጋገጡን የጤና ሚኒስቴርና ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በጋራ ባወጡት መግለጫ አስታወቁ።

    ሶስት ሰዎች ሕይወታቸው ሲያልፍ 68 ሰዎች በጽኑ ሕሙማን ክፍል ውስጥ መሆናቸውም ተገልጿል።

    ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ 140 ሰዎች ማገገማቸውም በመግለጫው ላይ ተመልክቷል።

    በኢትዮጵያ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ ጊዜ ጀምሮ በአጠቃላይ ለ364ሺህ 322 ናሙናዎች የኮሮናቫይረስ ምርመራ ሲደረግ 12ሺህ 693 ሰዎች ላይ ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል።

    አጠቃላይ የሟቾች ቁጥር 200 የደረሰ ሲሆን 5ሺህ 785 ሰዎች ደግሞ ከበሽታው ሙሉ በሙሉ አገግመዋል።

    በአሁኑ ሰዓት ቫይረሱ ያለባቸውና ክትትል እየተደረገላቸው የሚገኙ ሰዎች አጠቃላይ ቁጥር 6706 እንደሆነ የጤና ሚኒስቴር መረጃ ያሳያል

  17. ሶስት ሰዎች በኮቪድ-19 የተያዙባት የቻይና ከተማ በከፊል እንቅስቃሴን ገደበች

    በቻይና ሰሜን ምስራቅ የምትገኘው የሊዮንኒንግ ግዛት ከተማ፣ ዳሊያን በከፊል እንቅስቃሴ የተገደበባት ሲሆን በከተማዋ የሚኖሩ190,000 ነዋሪዎችም የኮቪድ-19 ምርመራ እያደረጉ ነው።

    ይህ የሆነው አንድ በአሳ ምግቦች ማቀነባበሪያ ውስጥ የሚሰሩ የ58 ዓመት ሴት በኮሮናቫይረስ መያዛቸውን ተከትሎ ነው።

    ቢያንስ ሌሎች ሁለት ሰዎች የኮቪድ-19 ምልክት አሳይተው ሲመረመሩ ኮቪድ-19 የተገኘባቸው ሲሆን በዚህም የተነሳ የከተማው አስተዳደር በርካታ ንግድ ቤቶችን ዘግቷል።

    የኢንተርኔት ካፌዎች፣ የገላ መታጠቢያዎች፣ የገበያ አዳራሾች፣ እንዲሁም ሌሎች ንግድ ቤቶች ከተዘጉት ንግድ ቤቶች መካከል ናቸው።

    አስተዳደሩ በተጨማሪም በግዛቲቱ ሁለት አካባቢዎች የሚኖሩ ሰዎችን ራሳቸውን ለይተው እንዲቀመጡ አዝዟል።

    የቻይና ማዕከላዊ መንግሥት አነስተኛ ቁጥር ያላቸው ወረርሽኞች ሲከሰቱ በፍጥነት ለመቆጣጣር የሚጥር ሲሆን፣ አያይዞም የተወሰኑ አካባቢዎችን እንቅስቃሴ በመገደብ ሰፊ ምርመራ ያደርጋል።

    ባለፈው ወር በቤይዢንግ አንድ ሰው ኮቪድ-19 ስለተገኘበት ብቻ 300 ሰዎች ተመርምረው በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

  18. የቀጣዮ ዓመት የፕሪሚየር ሊግ ውድድር መስከረም 2 ይጀምራል

    የ2020-2021 የፕሪሚየር ሊግ የጨዋታ ዘመን መስከረም 2/2013 ተጀምሮ ሚያዚያ 15 እንደሚያበቃ ተገለፀ።

    በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለሶስት ወራት ተቋርጦ ዳግም የጀመረው የዚህ ዓመት ውድድር እሁድ የሚያበቃ ይሆናል።

    የፕሪሚየር ሊጉ አስተዳዳሪዎች "ሁሉንም የአገር ውስጥ ውድድሮች የጊዜ ሰሌዳዎችን በሚመለከት" ከእግርኳስ ማህበር እና ከእንግሊዝ እግርኳስ ሊግ ጋር "ምክክር" እንደሚያደርጉ ተናግረዋል።

    የዘንድሮው የሊጉ አሸናፊ ሊቨርፑል መሆኑ ይታወሳል።

  19. የኮሮናቫይረስ አበይት ዜናዎች ከዓለም ዙሪያ

    የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዓለማችን ላይ መከሰቱ ከተሰማበት ጀምሮ ከ15.5 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውና 630 000 ደግሞ መሞታቸው ተመዝግቧል።

    • ዛሬ ሕንድ 49 310 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን ስታሳውቅ ይህም እስካሁን ድረስ በአንድ ቀን ከመዘገበችው ሁሉ የላቀው ነው ተብሏል።
    • ደቡብ አፍሪካ የኮሮናቫይረስ ስርጭት በትምህርት ቤቶች ውስጥ እየተስፋፋ መምጣቱን ተከትሎ የሕዝብ ትምህርት ቤቶችን ለአንድ ወር ያህል መዝጋቷን አስታውቃለች።
    • ቼክ ሪፐብሊክ በቤት ውስጥ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግን ግዴታ አድርጋ አስቀምጣለች። በአሁኑ ሰዓት በአገሪቱ ከ5000 በላይ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተገልጿል
    • ዲዝኒ በጉጉት ሲጠበቅ የነበረውን በድርጊት የተሞላው ሙላን የተሰኘ አኒሜሽን ፊልም ለእይታ የሚያበቃበትን ጊዜ ላልተወሰነ ጊዜ አስተላልፎታል። አቫታርና ስታር ዋርስ ፊልሞችም ለእይታ የሚበቁበት ጊዜ ወደ ሌላ ጊዜ ተላልፏል።
    • ፕሬዝዳንት ትራምፕ ፓርቲያቸው በፍሎሪዳ ሊያካሄደው የነበረውን ጉባዔ "ኮሮናቫይረስ ያስፋፋል" በሚል መሰረዛቸው ተሰምቷል።
    • ቦሊቪያ በነሐሴ ወይንም መስከረም መጀመሪያ የኮሮናቫይረስ ስርጭት ይስፋፋል በሚል ፍራቻ ልታካሂደው የነበረውን ምርጫ ወደ ጥቅምት ገፍታለች።
  20. ኬንያ በኮቪድ-19 ከተያዙ ሰዎች ጋር ንክኪ ያላቸውን ሰዎች ሁሉ መለየት አልቻለችም

    የኬንያ ጤና ሚኒስቴር ከዚህ በፊት ተመርምረው ኮቪድ-19 ከተገኘባቸው ሰዎች ጋር ንክኪ የነበራቸውና በኮሮናቫይረስ የተያዙ 13000 ሰዎችን አለማግኘቱ ተሰማ።

    ረቡዕ እለት ድረስ በቫይረሱ መያዛቸው ከታወቀ 14,168 ሰዎች መካከል ከእነርሱ ጋር ንክኪ የነበራቸው 10,433 ሰዎች እስካሁን ድረስ አልተገኙም።

    የኬንያ ዋና ከተማ ናይሮቢ ውስጥ ቫይረሱ ካለባቸው ሰዎች ጋር ንክኪ የነበራቸው በርካታ ሰዎች የሚገኙ ሲሆን የባህር ዳርቻ ከተማዋ ሞምባሳ ደግሞ በመከተል ትገኛለች።

    "ሁሉም ቫይረሱ ከተያዙ ሰዎች ጋር የቅርብ ንክኪ የነበራቸው ሰዎች በፍጥነት ቢለዩ የሚመከር ቢሆንም በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ መሆንና ክትትል የሚፈልጉ ሰዎች መጨመሩ የመንግሥትን ሥራ አክብዶታል" ያሉት ተጠባባቂ የጤና ዳይሬክተሩ ፓትሪክ አሞስ ናቸው።

    ኬንያ ውስጥ እስከ ዛሬ ድረስ ተመርምረው በኮሮናቫይረስ መያዛቸው የተረጋገጠ ሰዎች ቁጥር 15,000 የደረሰ ሲሆን ከእነዚህ መካከል 263 ሰዎች ሞተዋል።

    በኬንያ የእምነት ቦታዎች ከተወሰነ ገደብ ጋር ከባለፈው ሳምንት ጀምሮ እንዲከፈቱ ተፈቅዷል።