ኬንያዊው ዋነኛ የኮሮናቫይረስ ሳይንቲስት ከደረጃቸው ዝቅ መደረጋቸው አነጋጋሪ ሆኗል
ኬንያ ውስጥ የኮሮናቫይረስን በመመርመር የሚታወቁት ጉምቱ ሳይንቲስት ከእርከናቸው ዝቅ መደረጋቸው የሙያ አጋሮቻቸውን እንዳስቆጣ የአገሪቱ መገናኛ ብዙሃን እየዘገቡ ነው።
የኬንያ ጤና ሚኒስቴር እንዳለው ጆዌል ሉቶሚያህ ከእርከናቸው ዝቅ ያሉት ቫይረሱን የምርመራ ውጤቶችን በማሳወቅ ረገድ ዝግመት በመታየቱና በአስተዳደር ጉዳዮች ነው።
ዶክተር ጆዌል፤ የቫይረስ ምርምር ማዕከል ኃላፊ ሆነው እያገለገሉ ነበር። አሁን ግን አጥኚ ሳይንቲስት የሚል ቦታ ተሰጥቷቸው ከኃላፊነታቸው እንዲወርዱ ሆነዋል።
የሙያ አጋሮቻቸው ግን ዶክተሩ ከኃላፊነታቸው የተነሱት መንግሥት የኮሮናቫይረስ ምርምር ለሚደረግበት ማዕከል የገንዘብ እርዳታ እንዲያደርግና ቁሣቁስ እንዲያሟላ አዘውትረው በመጠየቃቸው ምክንያት ነው ሲሉ ለመገናኛ ብዙሃን ተናግረዋል።
ዴይሊ ኔሽን ለተሰኘው ጋዜጣ ድምፃቸውን የሰጡ አንድ ሳይንቲስት እንደሚሉት ዶ/ር ጆዌል መንግሥት ለባለሙያዎች ግላዊ መከላከያ የማያሟላ ከሆነ ምርመራ አላደርግም ሲሉ አስፈራርተዋል።
የምርምር ማዕከሉ ሠራተኞች በቂ የሆነ ግላዊ መከላከያ ቁሣቁስ እንዳልተሟላላቸው ይነገራል።