በብሩንዲ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለፖለቲካ ድጋፍ አደባባይ መውጣታቸውን ተከትሎ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ሊስፋፋ ይችላል የሚል ስጋት አጭሯል።
የተላላፊ በሽታዎች ባለሙያ የሆኑት ኦሊቨር ማንኢ እንደዚህ አይነት ትልልቅ ስብሰባዎች ለቫይረሱ መስፋፋት ሁነኛ መንገድ ናቸው ብለዋል ለቢቢሲ።
የዓለም ጤና ድርጅትም ቢሆን በወረርሽኙ ወቅት ሰዎች አካላዊና ማህበራዊ ርቀታቸውን እንዲጠብቁ ይመክራል።
የብሩንዲ ምርጫ ኮሚሽን የገዢው ፓርቲና ዋነኛ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ባዘጋጇቸው የፖለቲካ ድጋፍ ሰልፎች ላይ ውሃና ሳሙና አቅርቧል።
አንድ የድጋፍ ሰልፉ ተሳታፊ" በሰልፉ ላይ የተገኙ ሰዎችን ሁሉ እጅ ለማስታጠብ ወይንም በሳኒታይዘር ለማጽዳት የሰዉ ቁጥር እጅግ ብዙ ነበር" ብለዋል።
ብሩንዲ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝን ለመከላከል በሚል ድንበሯን ከዘጋች ቆይታለች።
በመላው አገሪቱ መንግሥት ሰዎች እጃቸውን እንዲታጠቡ እንዲሁም እንዳይጨባበጡ የሚያስተምር ሲሆን ከዚያ በዘለለ ግን ሕይወት እንደቀድሞው መቀጠሉን ታዛቢዎች ይናገራሉ።
በብሩንዲ እስካሁን ድረስ 14 ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸው ሲታወቅ አንድ ግለሰብ ደግሞ ሞቷል።
የብሩንዲ መንግሥት ምንም እንኳ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ቢከሰትም ከ20 ቀን በኋላ ምርጫ እንዲካሄድ ወስኗል።