በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 ምክንያት የመጀመሪያው ሞት መመዝገቡ ተገለፀ

የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ በመላው ዓለም ተዛምቶ የሁሉም ዋነኛ የህልውና ስጋት ሆኗል። ነገር ግን ባለሙያዎች እንደሚሉት ቀላል የመከላከያ መንገዶችን በመከተል በሽታውን መከላከል ይቻላል። እጅን በሳሙናና በውሃ መታጠብ፣ አለመጨባበጥ፣ አካላዊ እርቀትን መጠበቅና በተቻለ መጠን በርካታ ሰው ከሚሰበሰብበት ቦታ እራስን ማራቅ በሽታውን ለመከላከል ጠቃሚ እርምጃ ናቸው። ቢቢሲ አማርኛ በኮሮናቫይረስ ዙሪያ የተለያዩ ዜናና መረጃን ከኢትዮጵያና ከዓለም ዙሪያ በቀጥታ ዘገባ እዚህ ገጽ ላይ ያቀርባል። አብራችሁን በጤና ቆዩ!

የቀጥታ ሽፋን

  1. ሰበር, በኢትዮጵያ በአንድ ቀን ውስጥ ሁለተኛው የኮሮናቫይረስ ታማሚ ህይወት አለፈ

    የጤና ጥበቃ ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ፣ እንዳሳወቁት የ56 ዓመቱ የበሽታው ተጠቂ የህክምና ክትትልና ድጋፍ ሲደረግላቸው ቆይተው በዛሬው ዕለት ህይወታቸው አልፏል።

    ኢትዮጵያዊው ግለሰብ ሐሙስ መጋቢት 24/2012 ዓ.ም የኮሮናቫይረስ እንደተገኘባቸው ከተረጋገጠ በኋላ በለይቶ ህክምን መስጫ ማዕከል ውስጥ ክትትልና አስፈላጊው ህክምና ሲደረግላቸው እንደቆየ ተገልጿል።

    ታማሚው ወደ ህክምና ማዕከሉ ከገቡበት ዕለት አንስቶ የጽኑ ህሙማን ክትትል ሲደረግላችው ቆይተው፣ እሁድ አመሻሽ 12 ሰዓት አካባቢ ላይ ነው ህይወታቸው ማለፉ የተነገረው።

    ሁለተኛው ወንድ ሟች ይፋ ከመደረጉ ከሰዓታት በፊት የመጀመሪያዋ 60 ዓመት ኢትዮጵያዊት በበሽታው ሳቢያ ህይወታቸው ማለፉ ተገልጾ ነበር።

    በዚህም በአገሪቱ በአንድ ቀን ውስጥ በኮቪድ-19 ምክንያት የመጀመሪያዎቹ ሁለት ሰዎች ህይወት አልፏል።

    እስከ እሁድ ጠዋት አንድ ሰዓት ድረስ በኢትዮጵያ 1843 ሰዎች ላይ ምርመራ ተደርጎ በ43 ሰዎች ላይ ቫይረሱ ተገኝቷል።

    ከእነዚህም መካከል አራቱ ከበሽታው ሙሉ በሙሉ መዳናቸው የተነገረ ሲሆን የሁለቱ ህይወት ደግሞ ዛሬ ማለፉን የጤና ሚኒስቴር አስታውቋል::

  2. ሰበር, በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 ምክንያት የመጀመሪያው ሞት መመዝገቡ ተገለፀ

    በኢትዮጵያ በኮሮናቫይረስ ምክንያት የመጀመሪያው ሞት መመዝገቡን የጤና ጥበቃ ሚኒስትሯ ገለጹ።

    ዶክተር ሊያ ታደሰ እንዳሉት ሕይወታቸውን ያጡት ግለሰብ መጋቢት 19/2012 ዓ.ም የበሽታው ምልክት ታይቶባቸው ወደ ለይቶ ማቆያ ገብተው በተደረገላቸው ምርመራ ቫይረሱ ተገኝቶባቸው ነበር

    ቫይረሱ የተገኘባቸው የ60 ዓመት ሴት ላለፉት ስድስት ቀናት ስድስት ቀናት በጽኑ ሕክምና ክትትል ላይ የነበሩ ሲሆን በበሽታው ምክንያት በዛሬው ዕለት ሕይወታቸው ማለፉ ተገልጿል።

    በኢትዮጵያ እስከ ዛሬዋ ዕለት ድረስ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 43 መሆናቸው ቀደም ሲል ከጤና ሚኒስቴር የወጣ መረጃ አመልክቷል።

    በዛሬው ዕለት በበሽታው ሳቢያ ከሞቱት ግለሰብ ውጪ አራት ሰዎች ከበሽታው ሙሉ ለሙሉ መዳናቸው ተገልጿል።

    ቀሪዎቹም በለይቶ ህክምና መስጫ ውስጥ አስፈላጊው ክትትልና ህክምና እየተሰጣቸው መሆኑ ተገልጿል።

  3. በሲንጋፖር ሁለተኛ ዙር የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ተሰግቷል

    ሲንጋፖር ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ 120 ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸውን በምርመራ መረጋገጡን ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘገበ።

    ሲንጋፖር ከፍተኛ ምርመራና ክትትል በማድረግ የቫይረሱን ስርጭት ተቆጣጥራው ብትቆይም አሁን ግን በከፍተኛ ሁኔታ ሊሰራጭ ይችላል የሚል ስጋት አጭሯል።

    የዓለም ጤና ድርጅት የእስያ አገራት በሁለተኛ ዙር ወረርሽኝ ሊጠቁ እንደሚችሉ አስጠንቅቆ ነበር።

    የእስያ አገራት የመጀመሪያውን ዙር ወረርሽኝ ከተቆጣጠሩ በኋላ ከባህር ማዶ በሚመጡ ዜጎቻቸው ምክንያት አዳዲስ የተያዙ ሰዎች እየተገኙ ነው ተብሏል።

  4. በእስያ የሚገኙ ክርስትያኖች የተቀዛቀዘ የሆሳዕና በዓልን አከበሩ

    በመላው ዓለም ላሉ ክርስትያኖች ፋሲካ እየተቃረበ ነው። ዛሬ በእስያ የሚገኙ ክርስትያኖች የሆሳዕና በዓልን አክብረው ውለዋል።

    በዓሉን ሲያከብሩ ግን እንደከዚህ ቀደሙ በምዕመናን የተሞሉ አብያተ ክርስትያናት አልታዩም። በአገራቱ በተጣለው የመንቀሳቀስ ገደብ፣ አካላዊ እርቀትን መጠበቅና አለመጨባበጥ የተነሳ ጭር ያሉ እና የተራራቁ ምዕመናን ተስተውለዋል።

    ክርስትያኖቹ ግን በአዳዲስ መንገድ በዓሉን ሲያከብሩ ተስተውሏል።

    በፊሊፒንስ ምዕመናን ወደ ቤተክርስትያኖች እንዳይሄዱ ተከልክለዋል። ከዚያ ይልቅ በቴሌቪዥንና በኦንላየን በቀጥታ የሚተላለፉ ዝግጅቶችን እንዲመለከቱ ወይንም ደግሞ ቀሳውስት በአካባቢያቸው ሲያልፉ በራቸው ላይ በመሆን የዘንባባ ዝንጣፌ ያቸውን እንዲያስባርኩ፣ ታዝዘዋል።

    በሕንድና በኢንዶኔዢያ ደግሞ ምዕማናን ራሳቸውን ከእንቅስቃሴ አግደው በተቀመጡበት በቤታቸው ሆነው እንዲከታተሉ በሚል ስርዐዓተ ቅዳሴውና ሌሎች መርሃ ግብሮእ በቀጥታ ስርጭት ተላልፈዋል።

    በታይላንድ በቤተ እምነቶቹ ባሉ መቀመጫ ውስጥ ምዕመናን አካላዊ ርቀትን እንዲጠብቁ ማስታወቂያ ተለጥፎ ነበር።

  5. በአዲስ አበባ በኩል ደቡብ ሱዳን የገባችው ግለሰብ የአገሪቱ የመጀመሪያዋ የኮቪድ-19 ታማሚ ሆና ተገኘች

    ደቡብ ሱዳን የመጀመሪያዋ የሆነውን በኮሮናቫይረስ የተያዘ ሰው ማግኘቷን ይፋ አደረገች።

    ከአገሪቱ ምክትል ፕሬዝዳንት ጽህፈት ቤት የወጣው መግለጫ እንዳመለከተው በሽታው የተገኘባት የ29 ዓመት ወጣት ከአንድ ወር በፊት በአዲስ አበባ በኩል ከኔዘርላንድ ወደ ደቡብ ሱዳን የገባች ናት።

    በምክትል ተቀዳሚ ፕሬዝዳንቱ ሬክ ማቻር ተፈርሞ በወጣው መግለጫ ላይ ታማሚዋ ከሦስት ቀናት በፊት የኮሮናቫይረስ ምልክቶችን በማሳየቷ ወደ ህክምና ቦታ እንደሄደች ተገልጿል።

    በትናንትናው ዕለትም በተደረገላት ምርመራ የኮቪድ-19 ቫይረስ እንዳለባት ተረጋግጧል ሲል መግለጫው በደቡብ ሱዳን የመጀመሪያ በበሽታው የተያዘች ግለሰብ መገኘቷን አሳውቋል።

    ይህች ታማሚ እስክትገኝ ድረስ ደቡብ ሱዳን በዓለም ዙሪያ ምንም የኮሮናቫይረስ ታማሚ ካልተመዘገበባቸው በጣም ጥቂት አገራት መካከል አንዷ ሆና ቆይታለች።

  6. በዩናይትድ ኪንግደም ከ7 ሺህ እስከ 20 ሺህ ሊሞቱ ይችላሉ ተባለ

    አንድ ስመ ጥር የዩናይትድ ኪንግደም የጤና ባለሙያ እንደገመቱት ከ7 ሺህ እስከ 20 ሺህ የሚገመቱ ሰዎች በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ሊሞቱ እንደሚችሉ ተናገሩ።

    ፕሮፌሰር ኒል ፈርግሰን ለቢቢሲ እንደተናገሩት በበሽታው ምክንያት የሚሞቱት ሰዎች አሃዝ “በሰባት ሺህና ከ20 ሺህ በጥቂቱ ከፍ ባለ መጠን ሊሆን ይችላል” ብለዋል።

    ፕሮፌሰሩ እንዳሉት የእንቅስቃሴ እገዳው ከተጣለ በኋላ የበሽታው የመስፋፋት መጠን ዝግ ማለቱን የሚያሳዩ “አንዳንድ ምልክቶች” መኖራቸውን ገልፀዋል። ጨምረውም በሚቀጥሉት ከ7 እስከ 10 ቀናት በሚኖረው ጊዜ ባለበት ሊቆም ይችላል ብለዋል።

    በኮሮናቫይረስ ላይ ያዘጋጁትን ሞዴል ዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት እየተጠቀመበት እንደሆነ የሚነገርላቸው ፕሮፌሰር ፈርግሰን እንደሚሉት በአሁኑ ወቅት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባው ነገር በሚሞቱ ሰዎች አሃዝ ላይ የሚታየው ለውጥ ነው።

    የእንግሊዝ የጤና አገልግሎት ዳይሬክትር የሆኑት ፐሮፌሰር ስቴፈን ፖዊዝ ባለፈው ሳማንት እንዳሉት፣ በዩናይትድ ኪንግደም ውስጥ በወረርሽኙ የሚሞቱ ሰዎችን ቁጥር ከ20 ሺህ በታች ማድረግ ከቻልን “ተሳክቶልናል ማለት ይቻላል” ብለው ነበር።

  7. ሰበር, በኢትዮጵያ ተጨማሪ አምስት ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸው ተገለፀ

    በኢትዮጵያ አምስት ተጨማሪ ሰዎች የኮሮናቫይረስ እንደተገኘባቸው ተገለጸ።

    የጤና ጥበቃ ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዛሬ እሁድ ከሰዓት በኋላ በጋራ ባወጡት መግለጫ እንዳስታወቁት በአገሪቱ በበሽታው መያዛቸው የታወቁት ሰዎች ቁጥር ወደ 43 ከፍ ብሏል።

    በተጨማሪም ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ ለ59 ሰዎች ላይ የኮሮናቫይረስ ምርመራ የተደረገ ሲሆን ከመካከላቸውም አምስቱ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተረጋግጧል።

    ከአምስቱ መካከል ሦስቱ ታማሚዎች ኢትዮጵያዊያን ሲሆኑ አንድ ኤርትራዊ ሌላኛው ደግሞ ሊቢያዊ መሆናቸውን መግለጫው ጨምሮ አብራርቷል።

    ከአምስቱ ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች መካከል አራቱ የውጪ አገር የጉዞ ታሪክ የነበራቸው መሆኑ የተገለፀ ሲሆን፤ ይህም አጠቃላይ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር ወደ 43 ከፍ አድርጎታል።

  8. የማላዊ ፕሬዝዳንትና ሚኒስትሮች ገንዘብ ለማሰባሰብ የደሞዛቸውን 10 በመቶ ሰጡ

    የማላዊ ፕሬዝዳንት እና ሁሉም ሚኒስትሮች ለኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ገንዘብ ለማሰባሰብ የደሞዛቸውን 10 በመቶ ሰጡ።

    የፕሬዝዳንቱ ደሞዝ በወር 3 ሺህ ዶላር ሲሆን ከሚኒስትሮቹና ከእርሳቸው የተሰበሰበው ምን ያህል እንደሆነ የተገለፀ ነገር የለም።

    ፕሬዝዳንት ፒተር ሙታሪካ በወረርሽኙ ምክንያት የተጎዳውን የአገሪቱን ኢኮኖሚ ለማነቃቃት በሚልም የተለያዩ እርምጃዎችን ወስደዋል።

    ኢኮኖሚውን ለማነቃቃት ከወሰዷቸው እርምጃዎች መካከል ለነጋዴዎች የታክስ እፎይታ ጊዜ መስጠት፣ የነዳጅ ዋጋ ቅነሳ፣ ለሕክምና ባለሙያዎች የአበል ጭማሪ እንደሚገኙበት ሮይተርስ ዘግቧል።

    ትምባሆ የማላዊ ዋነኛ የወጪ ንግድ ሲሆን ፕሬዝዳንቱ የትምባሆ ገበያ የውጪ ምንዛሪ የምናገኝበትና ገበሬዎችን በሥራ ላይ ስለሚያቆይ ክፍት ሆኖ ይቆያል ብለዋል።

    ማላዊ የመጀመሪያውን በቫይረሱ የተያዘ ሰው ያገኘችው ሐሙስ ዕለት ሲሆን ይህም ከሌሎች አገራት ዘግይታ ሪፖርት ያደረገች አስብሏታል።

    በማላዊ ኮቪድ-19 የተገኘባቸው አራት ሰዎች ወደ ዩናይትድ ኪንግደም የተደረገ የጉዞ ታሪክ የነበራቸው ናቸው ተብሏል።

    ይህች የዓለማችን ደሃ አገር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ያወጀች ሲሆን ትምህርት ቤቶች እንዲዘጉና ሠራተኞች ከቤታቸው ሆነው እንዲሰሩ በማለት ትዕዛዝ አውጥታለች።

    በማላዊ ከ100 ሰዎች በላይ ሆኖ መሰብሰብ፣ ቀብር፣ የቤተክርስትያናት የአምልኮ መርሃ ግብሮች እንዲሁም የፖለቲካ ስብሰባዎች ተከልክለዋል።

    የ79 ዓመቱ ሙታሪካ ወደ ስልጣን የመጡት እኤአ በ2014 ሲሆን ባለፈው ዓመት በተደረገ ምርጫ ዳግም ቢመረጡም ምርጫው ተጭበርብሯል በሚል ተሰርዟል።

    ቀጣዩ ምርጫ በሐምሌ ወር ይካሄዳል ተብሎ ቀጠሮ ተይዞለታል።

  9. "እንቅስቃሴን ሙሉ ለሙሉ ለመዝጋት የሚያስችል አቅም የለንም" ጠ/ሚ ዐብይ አህመድ

    ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ባስተላለፉት መልዕክት በሌሎች አገራት እንደተደረገው የሕዝቡን እንቅስቃሴ ሙሉ ለሙሉ ለመዝጋት የሚያስችል አቅም መንግሥታቸው እንደሌለው ገልጸዋል።

    የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል “ሙሉ ለሙሉ እንቅስቃሴዎችን ለመዝጋት መንግሥት አቅም የለውም” ያሉት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አህመድ፤ የሚነገሩ የጥንቃቄ ተግባራትን በመፈፀም የተጎጂዎችን ቁጥር ለመቀነስ መንግሥታቸው እንደሚሰራ አመልክተዋል።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት ሁሉንም ዜጎች ቤታችሁ ተቀመጡ ማለት የማይቻልበትን ምክንያት ሲያስረዱ፤ ቤት የሌላቸው እንዳሉ፤ ያላቸውም ቢሆኑ የዕለት ጉርሳቸውን የሚያገኙት ከእጅ ወደአፍ በሆነ ሁኔታ መሆኑን በማስታወስ መንግሥት ለእነዚህ ወገኖች ምግብ ማቅረብ ካልቻለ የበለጠ ቀውስ እንደሚፈጠር አብራርተዋል።

    ነገር ግን በመጪው ሳምንት የሚኖረውን የወረርሽኙን አዝማሚያ በማጤን መንግሥት ተጨማሪ እርምጃዎችን ሊወስድ የሚችልበት ዕድል እንዳለ አመልክተዋል።

    ጨምረውም “ይህንን ወረርሽኝ ከተረዳዳን፣ ከተደማመጥን ዓለም ከዚህ ቀደም ከገጠማት ወረርሽኝ በበለጠ ፍጥነት ለመቆጣጠር እንችላለን” ብለዋል።

    መንግሥት ባለው አቅም ሞትን ለመቀነስ በርካታ የማስተማሪያ ስልት ቀይሶ እየሰራ ጠቅሰው፤ ነገር ግን የጥንቃቄ መልዕክቶች አሁንም ተግባራዊ ሲደረጉ እንደማይታይና መዘናጋት እንደሚስተዋል ተናግረዋል።

    የኮሮናቫይረስን በሚመለከት ከአፍሪካ መሪዎችና ከዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊዎች ጋር መወያየታቸው የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወረርሽኙ አሁን ባለው ሁኔታ በሚቀጥሉት ሳምንታት ውስጥ ከቀጠለ ያለው የአገሪቱ የመከላከል አቅም በእጅጉ እንደሚፈተንና አደጋውም ከፍተኛ ሊሆን እንደሚችል ስጋት መኖሩንና ገልፀዋል።

    ሕዝቡ ራሱን የሚነገሩትን የጥንቃቄ መልዕክቶች በአግባቡ እየተገበረ ባለመሆኑ “ስጋታችን ከፍተኛ ሆኗል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ምናልባት ችግሩ ከጸና በማለት ለኢትጵያዊያን ቤተሰቦች ጥያቄ አቅርበዋል።

    ይህም አንድ ቤተሰብ ለሌላ አንድ ቤተሰብ በቀን አንድ ምግብ ለማቅረብ እንዲዘጋጅ ጠይቀው፤ ጠቅላይ ሚንስትሩ ይህንንም “ማዕድ ማጋራት” ሲሉ ጠርተውታል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ የሆኑት ታከለ ኡማ አዲስ አበባ ሙሉ ለሙሉ የመዝጋት እቅድ እንደሌለ መናገራቸው ይታወሳል።

    ጥቂት የማይባሉ የአፍሪካ አገራት የበሽታውን መዛመት ለመግታት ሲሉ ከሁለት እስከ ሦስት ሳምንታት የሚቆዩ እንቅስቃሴን ሙሉ ለሙሉ የመዝጋት እርምጃ ወስደዋል።

  10. ቱኒዚያ ከቤት የሚወጡትን ለመቆጣጠር የሮቦት ፖሊስ አሰማራች

    በቱኒዚያን ዋና ከተማ፤ ቱኒዝ መንግሥት ያስቀመጠውን ቤት የመቀመጥ ገደብ ተፈፃሚነት ለመከታተል ሮቦት ፖሊሶች ተሰማሩ።

    ጭር ባሉት የቱኒዝ ጎዳናዎች ድንገት ብቅ ካሉና እነዚህ ሮቦት ፖሊሶች ካገኙዎ ጠጋ ብለው ወዴት? እንዴት? ብለው ይመረምሩዎታል።

    ያ ብቻ ሳይሆን ለሮቦቱ መታወቂያና ሌሎች የሚጠየቁትን መረጃዎች ማሳየት ይጠበቅብዎታል። ከዚያም ቢሮ ተቀምጦ ሮቦቶቹን የሚቆጣጠረው የፖሊስ ባልደረባ ያቀረቡትን ማስረጃ ያጣራል። ተጨማሪ ለማንበብ ከቤት የሚወጡትን ለመቆጣጠር ቱኒዚያ የሮቦት ፖሊስ አሰማራች

  11. በጎንደር ከተማ ተሽከርካሪዎች ለሁለት ሳምንት እንዳይንቀሳቀሱ ታገዱ

    የኮረናቫይረስ ወረርሽን ለመቆጣጠር የጎንደርከተማአስተዳደርከቅዳሜመጋቢት 26 ቀን 2012ዓ.ም ጀምሮ ለሚቀጥሉት ሁለት ሳምንታት የሚቆይ በተሽከርካሪዎች ላይ የእንቅስቃሴ ገደብ ጣለ።

    ቀደም ሲል የከተማው አስተዳደre ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ ታክሲዎችና ባለሦስት ጎማ ተሽከርካሪዎች (ባጃጆች) የሚያሳፍሩትን የሰው መጠን እንዲቀንሱ አድርጎ ነበር።

    ከባለፈው ሐሙስ መጋቢት 24/2012 ዓ.ም ጀምሮ የሕዝብ ትራንስፖርት ተሽከርካሪዎች ወደ ጎንደር ከተማ እንዳይገቡ ክልከላ የተጣለባቸዋል።

    አሁን ደግሞ የከተማዋ አስተዳደር የትራንስፖርት ጽህፈት ቤት ባወጣው ትዕዛዝ መሰረት ባጃጆች፣ ታክሲዎች፣ ሞተር ሳይክሎችና ጋሪዎች እንዳይንቀሳቀሱ ተከልክለዋል።

  12. በስፔን የሟቾች ቁጥር እየቀነሰ ቢሆንም የእንቅስቃሴ ገደቡ ይቆያል ተባለ

    የስፔን ጠቅላይ ሚኒስት ፔድሮ ሳንቼዝ በአገራቸው ለተከታታይ ሁለት ቀናት በኮሮናቫይረስ የሞቱ ሰዎች ቁጥር መቀነሱን ተከትሎ "የሽታው ከፍተኛ መጠን ላይ ደርሰናል" ሲሉ ተናገሩ።

    ሳንቼዝ አክለውም በቤት ውስጥ የመቀመጡ መመሪያ ለቀጣዮቹ 20 ቀናት እንደተራዘመ ያስታወቁ ሲሆን ገደቡ "ሕይወትን ይታደጋል" ብለዋል።

    ይህ ሳምንት በቀን 809 ሰዎች የሞቱበት ዝቅተኛው ሆኖ ተመዝግቧል።

    በተያያዘ የስፔን ባለስልጣናት የአገሪቱ ሕዝብ ላይ የተጣለውን ደንብ ለማላላት ለእያንዳንዱ ግለሰብ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ለማግኘት እየጣሩ ነው።

    በስፔን በአሁኑ ወቅት የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ማግኘት አዳጋች ነው። መንግሥት ከዚህ ቀደም የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል ከሆስፒታል ውጪ ያለው ግልጋሎት እምብዛም ነው ሲል ተናግሮ ነበር። ተጨማሪ ለማንበብ በስፔን የሟቾች ቁጥር እየቀነሰ ቢሆንም የእንቅስቃሴ ገደቡ ይቆያል ተባለ

  13. በዩናይትድ ኪንግደም በኮቪድ-19 የአምስት ዓመት ህፃን መሞቱ ተገለፀ

    በዩናይትድ ኪንግደም በኮሮናቫይረስ ከሞቱት መካከል ከዚህ ቀደም የጤና ችግር የነበረበት የአምስት ዓመት ሕፃን እንደሚገኝበት ተገለፀ።

    የካቢኔ ሚኒስትር የሆኑት ማይክል ጎቭ እንደተናገሩት በዩናይትድ ኪንግደም እስካሁን 4,313 ሰዎች የሞቱ ሲሆን ይህም አርብ ዕለት ከተመዘገበው የሟቾች ቁጥር በ708 ከፍ ያለ ነው ተብሏል።

    ሚኒስትሩ አክለውም በየዕለቱ በመቶዎች የሚቆጠሩ የመተንፈሻ ማሽኖች እየተመረቱ ሲሆን ከአገር ውጪም በርካታ ግዢ ተፈጽሟል።

    በዚህ ሳምንት በዩኬ ከሚኖረው ሞቃታማ አየር ጋር በተያየዓዘ ሰዎች በቤታቸው እንዲቆዩ ተነግሯቸዋል።

    “ፀሐይ ልትወጣ ትችላለች፤ እናንተ ግን መውጣት አለባችሁ ማለት አይደለም” ያሉት ደግሞ ዶ/ር ስቴፈን ፖዊስ ናቸው።

    ዶ/ር ስቴፈን የዩናይትድ ኪንግደም የብሔራዊ ጤና ሥርዓት ኃላፊ ሲሆኑ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ መፍትሄ መሆኑን ደግመው መክረዋል።

    በቫይረሱ አዲስ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እንደሚቀንስ ያላቸውን ተስፋ የገለፁት ዶክተሩ “ነገር ግን መዘናጋት አይገባም” ብለዋል።

  14. አሜሪካዊያን ለመጪው ከባድ ሳምንት እንዲዘጋጁ ትራምፕ መከሩ

    በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ከፍተኛ ሞት ሊከሰት እንደሚችል የሰጉት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ‘አስቸጋሪው ሳምንት’ ገና እየመጣ ስለሆነ አሜሪካዊያን እራሳቸውን እንዲያዘጋጁ አስጠነቀቁ።

    ፕሬዝዳንቱ በየዕለቱ በሚሰጡት መግለጫ ላይ በቀጣይ ቀናት ሊኖር ሰለሚችለው አደጋ እንዳሉት “ተጨማሪ ሞት ይኖራል” ብለዋል።

    በአገሪቱ በበሽታው ክፉኛ የተጠቁት ግዛቶችንም አንስተው የህክምና መገልገያዎች አቅርቦትና የጦር ሠራዊት አባላት ወረርሽኙን ለመቋቋም እንደሚሰማሩ ገልጸዋል።

    ጨምረውም "አገራችንን ለእንቅስቃሴ በድጋሚ ክፍት ማድረግ አለብን፤ በዚህ ሁኔታ ለተከታታይ ወራት መቆየትን አንፍልግም” ሲሉ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ቀደሞው መመለስ እንዳለባቸው አሳስበዋል።

  15. ሴኔጋል አፍሪካ ከኮሮናቫይረስ ጋር የምታደርገውን ግብግብ ትመራ ይሆን?

    የዓለም ጤና ድርጅት ከኮሮናቫይረስ ጋር በተያያዘ በተደጋጋሚ አገራት ትኩረት እንዲሰጡት በሚል “ምርመራ፣ ምርመራ፣ ምርመራ” ቢልም አፍሪካ ግን ውድ በመሆኑና ጊዜን ስለሚወስድ በስፋት መመርመር ሳትችል ቀርታለች።

    ይህ ግን አሁን የሚለወጥ ይመስላል። ሴኔጋል ቀላል፣ ፈጣን እና ከ40 ብር በታች በሆነ ወጪ ምርመራውን ለማድረግ የሚያስችል መመርመሪያ ከብሪታኒያ ኩባንያ ጋር እየሰራች ነው።

    ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ሴኔጋል የወባ መድኃኒትን የኮሮናቫይረስ ሕሙማንን ለማከም ጥቅም ላይ ማዋል የጀመረችው ቀድማ ነው።

    የዓለም ጤና ድርጅት የዚህ መድኃኒት ፈዋሽነት ገና አልተፈተሸም ያለ ሲሆን፤ ሌሎች የሕክምና ተቋማትም መድኃኒቱ ፍላጎት በከፍተኛ ሁኔታ እንዳያሻቅብ ሲሉ ስጋታቸውን ገልፀዋል።

    ነገር ግን የሴኔጋል መንግሥት ቃል አቀባይ አብዶ ላቲፍ ኩሊባሊ ለቢቢሲ እንደተናገሩት፤ የሕክምና ባለሙያዎች ለኮሮናቫይረስ ህሙማን የወባ መድኃኒት ከሰጡ በኋላ “ፈጣን መሻሻል” ማየታቸውን ጠቅሰዋል።

    አክለውም “የዓለም ጤና ድርጅት ምን ማድረግ እንዳለብን ሊነግረን አይችልም” በማለት “ሐኪሞቻችን የፈለጉትን ማድረግ ይችላሉ” ብለዋል።

    በአፍሪካ እስካሁን ድረስ 8 ሺህ ያህል ሰዎች ቫይረሱ እንዳለባቸው የተረጋገጠ ሲሆን፤ እስካሁን ድረስ እንደ ቀሪው የዓለማችን ክፍል በቫይረሱ ክፉኛ አልተጠቃችም።

    ነገር ግን ኮሮናቫይረስ በአፍሪካ አገራት ከተስፋፋ ቀውሱ ስር የሰደደ እንደሚሆን የብዙዎች ስጋት ነው።

    አፍሪካ ደካማ የሆነ የጤና ሥርዓት፣ የንጽህና ሁኔታ፣ የሰዎች ቫይረሱን የመቋቋም አቅም በተጨማሪም ቲቢ ኤችአይቪና የምግብ እጥረት ተደማምሮ ተጋላጭ ስለሚያደርጋት የሴኔጋል በርካሽ ዋጋ መመርመር የሚያስችል መሳሪያ የማምረት ጥረት የሚያበረታታ ነው ተብሏል።

  16. የቢቢሲ አማርኛ የቀጥታ ዘገባ ገጽ

    እንደምን አደራችሁ!

    ዕለተ እሁድ፤ መጋቢት 27/2012 ዓ.ም

    ቀኑ የሠላምና የጤና ይሆንላችሁ ዘንድ እንመኛለን። በተለይ ደግሞ እራሳችንንና ሌሎችን ከወቅቱ አሳሳቢ ወረርሽኝ [ኮቪድ-19] በመጠበቅ መልካም ዕለት እንዲሆን የበኩላችንን እናድርግ።

    የተለያዩ ዜናና ታሪኮችን ከዚህ የቢቢሲ አማርኛ የቀጥታ ዘገባ ገጽ ላይ ታገኛለችሁ፤ ይከታተሉን።

    የትናንት ዘገባዎችን ለማንበብ ወደታች ይወረዱ።

    መልካም ነገሮችን የምንሰማበት ዕለት ይሆን ዘንድ ምኞታችን ነው!

  17. በኬንያ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር 126 ደረሰ

    የኬንያ ጤና ሚኒስቴር ሌላ አራት ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው መረጋገጡን ዛሬ አስታወቀ።.

    በቫይረሱ የተያዙት ግለሰቦች ሦስቱ ኬንያዊ ሲሆኑ፤ ሌላኛው ፓኪስታናዊ እንደሆነ ተነግሯል።.

    ይህም በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን ቁጥር 126 አድርሶታል።.

    ኬንያ ባለፉት 24 ሰዓታት ውስጥ በወረርሽኙ የተጠረጠሩ 372 ሰዎች ላይ ምርመራ አድርጋለች።.

  18. የብሪቲሽ አየር መንገድ የበረራ ቡድን አባላት በኮቪድ-19 ሳንያዝ አንቀርም ሲሉ ሰግተዋል

    የብሪቲሽ አየር መንገድ በረራ ቡድን አባላት ላለፉት ሁለት ሳምንታት ረጅም በረራ ካደረጉ በኋላ በበሽታው ሳይያዙ እንዳልቀሩ ስጋት አድሮባቸዋል።

    የቡድኑ አባላት ማኅበር እና አብራሪዎች፤ የበረራ ሠራተኞች ለቫይረሱ እንዳይጋለጡ እርምጃ ሊወሰድ እንደሚገባ እየጠየቁ ነው።

    አንድ የአየር መንገዱ ባልደረባ ለቢቢሲ እንደገለጹት አየር መንገዱ እርምጃዎችን ለመውሰድ ዘግይቷል ብለዋል።

    ይሁን እንጂ አየር መንገዱ ኒው ዮርክን ጨምሮ ወደ አሜሪካ አሁንም በረራዎችን ያደርጋል።

    ከዚህም በተጨማሪ ከአገር ውጭ እንቅስቃሴያቸው ተገድበው የሚገኙ ዜጎችን የመመለስ ሥራ ይሰራል።

    አየር መንገዱ ለቀረበበት ቅሬታ ሲመልስ፤ ራስን መጠበቂያ ቁሳቁሶች ለሠራተኞቹ መዘጋጀቱን ጠቅሶ፤ በመንገደኞችና በበረራ ሠራተኞቹ መካከል የሚኖረውን ንክኪ ለመቀነስ እርምጃ መውሰዱን ገልጿል።

  19. በባህር ዳር የኮቪድ-19 ምርመራ ሰኞ ይጀምራል

    የአማራ ክልል የኅብረተሰብ ጤና ኢንስቲቲዩት ከሰኞ ጀምሮ በባህርዳር ከተማ የኮሮናቫይረስ ምርመራ ሊጀምር ነው።

    በዛሬው ዕለት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ምርመራው የሚደረግበትን ስፍራ የጎበኙ ሲሆን ሁለት ባለሙያዎች ስልጠና ወስደው ግብዓቶች መሟላታቸውን ተዘግቧል።

    ኢንስቲቲዩቱ አክሎም በቅርቡ በጎንደርና ደሴ ተመሳሳይ ምርመራ እንደሚጀመር ገልጿል።

    በተጨማሪም በደብረብርሃን ምርመራ ማድረግ የሚያስችለውን ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም አመልክቷል።

  20. ድምጻዊት ፒንክ በኮቪድ-19 መያዟ ተነግሯት እንደነበር ገለጸች

    አሜሪካዊቷ ድምጻዊት፣ ተዋናይት፣ ዳንሰኛ አሌሽያ ቤትሞር፤ በቅጽል ስሟ ‘ፒንክ’ በቫይረሱ መያዟ ተነግሯት እንደነበር ተናገረች።

    ድምጻዊቷ ለአስቸኳይ ጊዜ የሚሆን አንድ ሚሊየን ዶላር የገንዘብ ድጋፍ ለማድረግ ቃል ገብታለች።

    የግራሚ ሽልማት አሸናፊዋ አርቲስት እንዳለችው እርሷና ወንድ ልጇ ጀምሰን፤ ባለፉት ሁለት ሳምንታት የቫይረሱ ምልክት ታይቶባቸው ነበር።

    ከዚያም በተደረገላቸው ምርመራ እሷ በቫይረሱ እንደተያዘች ተረጋግጦ ነበር።

    ይሁን እንጅ እርሷና ልጇ ከቀናት በፊት በድጋሚ ምርመራ አድርገው ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸውን በትዊተር ገጿ ላይ ገልጻለች።

    “ልጆቻችንን፣ ቤተሰቦቻችንን፣ ጓደኞቻችንን እና ማኅበረሰባችንን ለመጠበቅ፤ ምርመራውን በነጻ እና በስፋት ማካሄድ አለብን” ብላለች ፒንክ።

    ከዚህም በተጨማሪ በፊላደልፊያ ለሚገኘው ቴምፕል ዩኒቨርሲቲ ሆስፒታልና በሎስ አንጀለስ ከንቲባ ኮቪድ-19 ቀውስን ለመቆጣጠር የሚረዳ ለእያንዳንዳቸው 500 ሺህ ዶላር የገንዘብ ድጋፍ እንደምታደርግ ቃል ገብታለች።