የአያቶላህ አሊ ኻሜኒን ግድያ ተከትሎ ኢራን እና እስራኤል እንደ አዲስ ጥቃት መፈጸም ቀጥለዋል

የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ በአሜሪካ እና እስራኤል ጥቃት እንደተገደሉ ከተረጋገጠ በኋላ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ በአሜሪካ የጦር ሰፈሮች እና በእስራኤል ላይ “አስከፊ ጥቃት” እንደሚፈጽም አስጠንቅቋል። ይህንንም ተከትሎ ባህሬን፣ ኩዌት፣ ኳታር፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ኢራቅ እና ኦማን ውስጥ ጥቃት ተፈጽሟል። የእስራኤል ጦርም የኢራን ዋና ከተማ ቴህራንን ዒላማ ያደረጉ ጥቃቶችን መፈጸሙን አስታውቋል።

ጭምቅ ሃሳብ

የቀጥታ ሽፋን

  1. ዱባይ እና እስራኤል ውስጥ የተፈጸመውን የኢራን ጥቃት የሚያሳዩ ምሥሎች

    ኢራን፤ ትናንት ሌሊት እና ዛሬ ዱባይ እና እስራኤል ላይ በፈጸመቻቸው ጥቃቶች የደረሰውን ጉዳት የሚያሳዩ ምሥሎች እየወጡ ነው።

    ኢራን ምሽት ላይ የተባበሩት አረብ ኤምሬቶች ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያን ጨምሮ በዱባይ የሚገኙ ዒላማዎችን አጥቅታለች። በተጨማሪም ቅዳሜ ሌሊት የተወነጨፉ የኢራን ሚሳዔሎች በማዕከላዊ ቴል አቪቭ ውስጥ የሚገኙ የመኖሪያ ሕንጻዎችን መትተዋል።

    በኢራን ጥቃት ከተመታው የዱባይ ጄበል አሊ ወደብ ላይ እሁድ ጠዋት ጭስ ታይቷል

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, በኢራን ጥቃት ከተመታው የዱባይ ጄበል አሊ ወደብ ላይ እሁድ ጠዋት ጭስ ታይቷል
    ኢራን ጥቃት ከፈጸመች በኋላ ከዱባይ የባሕር ዳርቻ ላይ ሲወጣ የነበረ ጥቅጥቅ ያለ ጭስ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ኢራን ጥቃት ከፈጸመች በኋላ ከዱባይ የባሕር ዳርቻ ላይ ሲወጣ የነበረ ጥቅጥቅ ያለ ጭስ
    ቅዳሜ ምሽት የተወነጨፈ የኢራን ሚሳዔል ቴል አቪቭ ውስጥ የሚገኝ የመኖሪያ ሕንጻን አውድሟል

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, ቅዳሜ ምሽት የተወነጨፈ የኢራን ሚሳዔል ቴል አቪቭ ውስጥ የሚገኝ የመኖሪያ ሕንጻን አውድሟል
    የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በኢራን ሚሳዔል በተመታው የቴል አቪቭ የመኖሪያ ሕንፃ ደርሰው እገዛ ሲያደርጉ ነበር

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, የአደጋ ጊዜ ሠራተኞች በኢራን ሚሳዔል በተመታው የቴል አቪቭ የመኖሪያ ሕንጻ እገዛ ሲያደርጉ ነበር
  2. ከኢራን ጦርነት ጋር በተያያዘ ሌሊት ላይ የተፈጠሩ ዋና ዋና ክስተቶች

    የኢራን ባንዲራን እና ጠቅላይ መሪው አያቶላህ አሊ ኻሜኒን ፎቶ የያዘ እጅ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የአሜሪካ እና እስራኤል ጥቃት የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒን መግደሉን ተከትሎ የአገሪቶ ጦር፤ “እጅግ አስከፊ” የሆነ የአጸፋ እርምጃ እንደሚወስድ አስጠንቅቋል። ባለፉት ሰዓታት ከኢራን ጦርነት ጋር የተያያዙ በርካታ ክስተቶች ተፈጥተዋል፤ ዋና ዋናዎቹ እነዚህ ናቸው፦

    • አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ቢሮቸው ውስጥ መገደላቸውን የኢራን የመንግሥት ቴሌቪዥን ዘግቧል። አገሪቱን ለ37 ዓመታት የመሩት ጠንካራውን የሃይማኖት መሪ የተገደሉባት ኢራን የ40 ቀናት ብሔራዊ ሐዘን አውጃለች።
    • የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ለመሪው መገደል አጻፋ የሚሆን “አስከፊ ጥቃት” በአሜሪካ የጦር ሰፈሮች እና በእስራኤል ላይ እንደሚፈጽም አስጠንቅቋል።
    • በኢራን ሕገ መንግሥት መሠረት የአያቶላህ አሊ ኻሜኒ ተተኪ የሚመረጠው እርሳቸውንም እዚህ ሥልጣን ላይ በሾማቸው የአመራር ሊቃውንት ጉባኤ ነው።
    • ጥቃቱ ከተፈጸመ እና የኻሜኒን ሞት ከተረጋገጠ በኋላ አንዳንድ ኢራናውያን ደስታቸውን ሲገልጹ የታዩ ሲሆን ሌሎች ደግሞ ሐዘን ላይ ናቸው።
    • የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በበኩላቸው አያቶላህ ኻሜኒ፤ ”በታሪክ ከታዩ እጅግ ክፉ ሰዎች አንዱ” ነበሩ ብለዋል። የኻሜኒ ሞት፤ “የኢራን ሕዝብ አገሩን መልሶ ለመያዝ የሚያስችለው ብቸኛው ታላቅ ዕድል” እንደሆነም ገልጸዋል።
    • የቀይ ጨረቃ መረጃ እንደሚያመለክተው ኢራን ውስጥ በተፈጸመው ጥቃት ከ200 በላይ ሰዎች ተገድለዋል። በአሜሪካ የቢቢሲ አጋር የሆነው ‘ሲቢኤስ ኒውስ’ በበኩሉ 40 ገደማ የኢራን ባለሥልጣናት መሞታቸውን ዘግቧል።
    • ኢራን፤ በመካከለኛው ምሥራቅ ባሉ የአሜሪካ አጋሮች ላይ እና የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች በሚገኙባቸው ቦታዎች ላይ ጥቃቶችን ፈጽማለች። ጥቃቱ ከተሰነዘረባቸው መካከል፤ ዱባይ፣ ዶሃ፣ ባህሬን እና ኩዌት ይገኙበታል።
    • በዓለም ላይ እጅግ በርካታ በረራዎችን ከሚያስተናግዱ የአቪዬሽን ማዕከላት አንዱ በሆነው በዱባይ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ እንዲከሽፍ የተደረገ ኢራን የሚሳዔል ስብርባሪዎች ወድቆ አራት ሰዎች እንደቆሰሉ የአገሪቱ መንግሥት አስታውቋል።
    • የዩናይትድ ኪንግደም ጠቅላይ ሚኒስትር ኪር ስታርመር በበኩላቸው፤ ብሪታንያ ዜጎቿን እና ቀጣናዊ አጋሮቿን ለመጠበቅ ስትል “የተቀናጀ የቀጣናዊ የመከላከል ዘመቻ” ውስጥ እየተሳተፈች መሆኑን አስታውቀዋል።
  3. አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ትምህርት ቤት ባደረሱት ጥቃት 148 ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ

    ቢቢሲ በአካባቢው ፍንዳታ ከደረሰ በኋላ ነዋሪዎች ተደናግጠው መሰባሰባቸውን አረጋግጧል።

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, ቢቢሲ በአካባቢው ፍንዳታ ከደረሰ በኋላ ነዋሪዎች ተደናግጠው መሰባሰባቸውን አረጋግጧል።

    በደቡባዊ ኢራን በሚገኝ ትምህርት ቤት ላይ አሜሪካ እና እስራኤል ባደረሱት ጥቃት ቢያንስ 148 ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ።

    የኢራን ፕሬዝዳንት ማሱድ ፔዚሽኪያን “ኋላ ቀር ድርጊት ነው። አጥቂዎቹ ከፈጸሟቸው አሰቃቂ ድርጊቶች አንዱ ሆኖ ተመዝግቧል” ብለዋል።

    አሜሪካ እና እስራኤል በትምህርት ቤት ላይ ጥቃት ስለመድረሱ ያሉት ነገር የለም።

    የኢራን ቀይ ጨረቃ እንዳለው በመላው አገሪቱ ቢያንስ 201 ሰዎች የሞቱ ሲሆን 747 ሰዎች ተጎድተዋል።

    በጄኔቫ የሚገኙ የቀይ ጨረቃ እና ቀይ መስቀል አመራሮች እንዳሉት፤ የባለሙያዎች ቡድን ወደ ትምህርት ቤቱ ተልኳል።

    በኢራን ሆርሞግዣን ግዛት፣ ሚንዳብ ከተማ በሚገኘው ትምህርት ቤት ላይ “ሦስት የሚሳዔል ጥቃት” መፈጸሙን አንድ ባለሥልጣን ተናግረዋል።

    ቢቢሲ በአካባቢው ፍንዳታ ከደረሰ በኋላ ነዋሪዎች ተደናግጠው መሰባሰባቸውን አረጋግጧል። ምን ያህል ሰዎች እንደተገደሉ ግን ማረጋገጥ አልተቻለም።

    ኢራናውያን ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ቁጣቸውን እየገለጹ ነው። አንድ ከኢራን ውጭ የሚኖሩ የአገሪቱ ዜጋ ወታደራዊ እርምጃውን አውግዘው “የጦርነታቸው የመጀመሪያዎቹ ሰለባዎች በሚሳዔል የተመቱ 40 ታዳጊ ሴቶች ናቸው። ይሄንን ድርጊት ነው የምታወድሱት?” ብለዋል።

  4. የመጨረሻው የኢራን ንጉሥ ልጅ የአያቶላህ ኻሜኒ መገደል “የአገሪቱን አቅጣጫ ሊቀይር ይችላል” አሉ

    የኢራን ንጉስ (ሻህ) ልጅ ሬዛ ፓህላቪ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    አሜሪካ ውስጥ ስደት ላይ ያሉት የመጨረሻው የኢራን ንጉሥ (ሻህ) ልጅ ረዛ ፓህላቪ፤ የጠቅላይ መሪው አያቶላህ አሊ ኻሜኒን ሞት በደስታ መቀበላቸውን የሚገልጽ ጽሁፍ አውጥተዋል።

    ፓህላቪ ምሽት ላይ በአሜሪካው ዋሽንግተን ፖስት ጋዜጣ ላይ ባወጡት ጽሁፍ፤ “የነፃነታችሁ ሰዓት ተቃርቧል” በማለት ለኢራን ሕዝብ መልዕክት ላስተላለፉት ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ምስጋና አቅርበዋል።

    ለግማሽ ክፍለ ዘመን ያህል እስላማዊ ሪፐብሊኳ “የጎረቤት አገራትን ሉዓላዊነት ስትጥስ፣ በዓለም ዙሪያ ግጭቶችን ስታቀጣጥል እንዲሁም የኒውክሌር መሣሪያዎችን እና ኒውክሌር የሚያስወነጭፉ ረዥም ርቀት ተጓዥ ሚሳዔሎችን ለመታጠቅ ስትሠራ ቆይታለች” ብለዋል።

    የእስላማዊ ሪፐብሊኳ እጅግ “አስከፊ ወንጀሎች” የተፈጸሙት ግን አገር ውስጥ ነው ሲሉ ጽፈዋል። ባለፈው ጥር ላይ ተቃውሞ በወጡ ሰልፈኞች ላይ በተወሰደው እርምጃ በሺህዎች የሚቆጠሩ ተቃዋሚዎች መገደላቸውንም በማሳያነት ጠቅሰዋል።

    የአገሪቱ ቀጣይ ጉዞ አዲስ ሕገ መንግሥት ማርቀቅ እና በሕዝበ ውሳኔ መጽደቅን፤ በመቀጠልም “ዓለም አቀፍ ታዛቢዎች” በተኙበት ነጻ ምርጫዎች ማካሄድን ማካተት እንደሚገባው ገልጸዋል።

    “ብዙውን ጊዜ ታሪክ የሚታጠፍባቸውን ነጥቦች አስቀድሞ አያሳውቅም። ነገር ግን የአገርን አቅጣጫ መቀየር የሚችሉ አጋጣሚዎች ከድፍረት፣ አመራር እና አብሮነት ጋር ይመጣሉ” ብለዋል።

  5. ትራምፕ፤ ኢራን አሜሪካን ወይም እስራኤልን የምታጠቃ ከሆነ “ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ኃይል” ትመታለች አሉ

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ

    የፎቶው ባለመብት, Los Angeles Times via Getty Images

    የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ትሩዝ ሶሻል በተሰኘው የማኅበራዊ ሚዲያ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሑፍ ኢራን አሜሪካ ወይም እስራኤል ላይ የአጸፋ ጥቃት እንዳትፈጽም አስጠንቅቀዋል።

    ትራምፕ በጽሑፋቸው፤ “ኢራን ዛሬ እጅግ በኃይለኛው እንደምታጠቃ ገልጻለች፤ ከዚህ ቀደም ከፈጸሙት [ጥቃት] ሁሉ ኃይለኛ የሆነ” ብለዋል።

    “ይህንን ባያደርጉ ይሻላቸዋል፤ ምክንያቱም የሚያደርጉት ከሆነ ከዚህ ቀደም ታይቶ በማይታወቅ ኃይል እንመታቸዋለን!” ሲሉ በአጽንኦት አስጠንቅቀዋል።

    ትራምፕ ይህንን ያሉት፤ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ለአያቶላህ አሊ ኻሜኒ ግድያ የአጸፋ ምላሽ ለመስጠት የአሜሪካ የጦር ሰፈሮች እና እስራኤል ላይ ጥቃት እንደሚፈጸም ካስጠነቀቀ በኋላ ነው።

    አብዮታዊ ዘቡ ከሰዓታት በፊት፤ “በኢራን እስላማዊ ሪፐብሊክ የጦር ኃይሎች ታሪክ ውስጥ እጅግ አስከፊ የሆነው የማጥቃት ዘመቻ፤ በተወረሩ ግዛቶች እና በአሜሪካ ሽብርተኛ የጦር ሰፈሮች ላይ በደቂቃዎች ውስጥ መፈጸም ይጀምራል” ብሎ ነበር።

  6. የኢራን ሁለት ከፍተኛ አዛዦች መገደላቸውን የአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን አረጋገጡ

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ዋና አዛዥ መሐመድ ፓክፑር

    የፎቶው ባለመብት, FARS

    የምስሉ መግለጫ, የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ዋና አዛዥ መሐመድ ፓክፑር

    የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ዋና አዛዥ መሐመድ ፓክፑር እና የኢራን መከላከያ ምክር ቤት ጸሐፊ አሊ ሻምኻኒ፤ አሜሪካ እና እስራኤል በፈጸሙት ጥቃት መገደላቸውን ይፋዊው ‘ኢርና’ የዜና ወኪል አስታወቀ።

    ይህ ከመረጋገጡ አስቀድሞ የእስራኤል መከላከያ ሠራዊት፤ ፓክፑርን እና ሻምኻኒን ጨምሮ በተፈጸመው ጥቃት ተገድለዋል ያላቸውን የሰባት የኢራን የደኅንነት አመራሮችን ስም ዝርዝር ይፋ አድርጎ ነበር።

    መሐመድ ፓክፑር የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ዋና አዛዥ ሆነው የተሾሙት ባለፈው ሰኔ ላይ በተደረገው የእስራኤል እና ኢራን የ12 ቀናት ጦርነት የቀድሞው አዛዥ ከተገደሉ በኋላ ነበር። ፓክፑር እዚህ ኃላፊነት ላይ ከመሾማቸው በፊት የአብዮታዊ ዘቡን የምድር ጦር በአዛዥነት መርተዋል።

    የኢራን የጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ከፍተኛ አማካሪ የነበሩት ሻምኻኒም በ12 ቀናቱ ጦርነት ወቅት ቆስለው ነበር። አሁን የተገደሉት ሁለቱ አመራሮች በአሜሪካ የግምጃ ቤት ማዕቀብ ተጥሎባቸው ነበር።

  7. ደስታ እና ሐዘን የተቀላቀለበት የአያቶላህ አሊ ኻሜኒ ግድያ

    የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ያወጧቸው ምሥሎች የቴህራን ነዋሪዎች የአያቶላህ አሊ ኻሜኒን ምሥል ይዘው ሐዘናቸውን ሲገልጹ ያሳያሉ።

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የኢራኑ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ መገደላቸው ይፋ ከተደረገ በኋላ አንዳንድ ኢራናውያን ደስታቸውን እየገለጹ ነው።

    ትናንት አሜሪካ እና እስራኤል በከፈቱት ጥቃት አያቶላህ አሊ ኻሜኒ መገደላቸው ከተረጋገጠ በኋላ በአንዳንድ የኢራን ከተሞች ሕዝብ በአደባባይ ደስታውን ሲገልጽ እንደነበር ቢቢሲ አረጋግጧል።

    ዛሬ ጠዋት ከኢራን የወጡ ምሥሎች ደግሞ በአያቶላህ አሊ ኻሜኒ ግድያ ሐዘናቸውን የሚልጹ ሰዎችን አሳይተዋል።

    በማዕከላዊ ኢራን ኢስፋሀን ግዛት ነዋሪዎች ደስታቸውን እየገለጹ ነው። በሌላ ከተማ ደግሞ ርችት የሚተኩሱ ሰዎች ቪድዮዎች ወጥተዋል።

    በተቃውሞው ወቅት በመንግሥት ቤተሰቦቻቸው የተገደሉባቸው ኢራናውያን ደስታቸውን በየጎዳናቸው ሲገልጹ ታይተዋል።

    በቴህራን አቅራቢያ በምትገኘው ካራጅ ግዛትም ተመሳሳይ የደስታ ድባብ እንዳለ ሮይተርስ የዜና ወኪል ዘግቧል።

    የተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ያወጧቸው ምሥሎች የቴህራን ነዋሪዎች የአያቶላህ አሊ ኻሜኒን ምሥል ይዘው ሐዘናቸውን ሲገልጹ ያሳያሉ።

  8. አያቶላህ አሊ ኻሜኒ መገደላቸውን የኢራን መንግሥት አረጋግጦ 40 የሐዘን ቀናት አወጀ

    አያቶላህ አሊ ኻሜኒ

    የፎቶው ባለመብት, Getty Images

    የምስሉ መግለጫ, አያቶላህ አሊ ኻሜኒ

    የኢራኑ ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ መገደላቸውን የኢራን መንግሥት አረጋግጦ 40 የሐዘን ቀናት አወጀ።

    መሪው እስራኤል እና አሜሪካ ቅዳሜ ዕለት ቴህራን ውስጥ በፈጸሙት ጥቃት መገደላቸውን የአገሪቱ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን አረጋገጡ።

    ከኢራን ብሔራዊ የደኅነንት ጠቅላይ ምክር ቤት ወጥቶ በአገሪቱ መገናኛ ብዙኃን በተነበበው መግለጫ ላይ እንደተገለጸው አያቶላህ ኻሜኒ የተገደሉት ቅዳሜ ጠዋት ጽህፈት ቤታቸው ላይ በተፈጸመው ጥቃት ነው።

    የጠቅላይ መሪውን ሞት ተከትሎ በመላው አገሪቱ 40 የሐዘን ቀናት የታወጀ ሲሆን፣ የባለሙያዎች እና የሃይማኖት መሪዎች ምክር ቤት የሆነው የአመራር ጉባዔ በአስቸኳይ የተገደሉትን መሪ የሚተካ ሰው ይሾማል ተብሎ ይጠበቃል።

    የአገሪቱ ፕሬዝዳንት እና ሌሎች ሁለት ከፍተኛ ባለሥልጣናት በቀጣይ የሚደረገውን የመሪ ሽግግር እንደሚመሩ ተገልጿል።

    በቅዳሜ ዕለቱ ጥቃት ከአያቶላህ ኻሜኒ በተጨማሪ ከ200 በላይ ሰዎች መገደላቸውን ቀይ ጨረቃ እና ሌሎችም ምንጮች ያስታወቁ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል 40 የሚሆኑት የኢራን መንግሥት ባለሥልጣናት እንደሆኑ እየተነገረ ነው።

    በጥቃቱ የኻሜኒ ሴት ልጅ፣ ባሏ እና የልጅ ልጃቸው መገደላቻውን ከኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ ጋር ቅርብት ያላቸው መገናኛ ብዙኃን ዘግበዋል።

  9. የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ሳይገደሉ እንዳልቀረ እየተነገረ ነው

    ኻሜኒ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የኢራን ጠቅላይ መሪ መኖሪያ ላይ በተፈጸመው ከባድ ጥቃት ዙሪያ መግለጫ የሰጡት እስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታኒያሁ ስለ አያቶላ ኻሜኒ ዕጣ ፈንታ ተናገሩ።

    ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቅዳሜ ምሽት በአገራቸው ቴሌቪዥን ላይ ቀርበው እንደተናገሩት “አምባገነኑ [አያቶላህ ኻሜኒ] የለም” በማለት ቴህራን ውስጥ በተፈጸመው ጥቃት መገደላቸውን አመልክተዋል።

    ሮይተርስ የዜና ወኪል የአያቶላህ አሊ ኻሜኒ አስከሬን መገኘቱን እና መገደላቸው መታወቁን አንድ የእስራኤል ባለሥልጣን እንዳረጋገጡለት ዘግቧል።

    ነገር ግን ከኢራን ባለሥልጣናት በኩል የጠቅላይ መሪውን ሁኔታ በተመለከተ ምንም ዓይነት መግለጫ አልተሰጠም።

    ቅዳሜ ጠዋት ዋና ከተማዋ ቴህራን ውስጥ በሚገኘው የመሪው መኖሪያ በተፈጸመበት ከባድ ጥቃት የወደመ ሲሆን፣ ነገር ግን ኻሜኒ በጥቃቱ ወቅት በስፍራው እንዳልነበሩ ባለሥልጣናት ተናግረው ነበር።

  10. ኢራን በአጸፋው በየትኞቹ አገራት ላይ ጥቃት ፈጸመች?

    በምሽት የሚታይ ጭስ
    የምስሉ መግለጫ, በዱባይ የተፈጸመ ጥቃት

    አሜሪካ እና አስራኤል ጥቃት ከተፈጸመባት በኋላ ኢራን የሚጠበቀውን የአጸፋ ጥቃት በመካከለኛው ምሥራቅ ባሉ የአሜሪካ ጦር ሰፈር ባለባቸው አገራት እና በወዳጆቿች ላይ ፈጽማለች።

    • የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ ዱባይ በሚገኘው ፓልም ጁሜሪያህ ሕንጻ ላይ በደረሰ ፍንዳታ አራት ሰዎች መጎዳታቸውን ባለሥልጣናት አስታውቀዋል።
    • የኤምሬትስ መከላከያ ሚኒስቴር ከኢራን የተወነጨፉ ሚሳዔሎች እና ድሮኖችን ማክሸፉን ጠቅሶ፤ አገሪቱ በኢራን ተወንጫፊ ሚሳዔች በግልጽ መጠቃቷን ገልጿል።
    • በዶሃ፣ ኳታር ውስጥ የሚገኘው እና በመካከለኛው ምሥራቅ ትልቁ የአሜሪካ የአየር ኃይል ሰፈር የሆነው አል ኡዴይድን ዒላማ ያደረገ ፍንዳታ አጋጥሟል።
    • የባህሬን መንግሥት ዜና አገልግሎት እንደዘገበው በአገሪቱ የሚገኘው የአሜሪካ ባሕር ኃይል ሰፈር የሚሳዔል ጥቃት ደርሶበታል።
    • የኩዌት ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያን ዒላማ ደያረጉ የድሮን ጥቃት ፍንዳታዎች ተሰምተዋል፤ በጥቃቱ “በርካታ ሠራኞች መቁሰላቸው” እና ውስን ጉዳት በአውሮፕላን ማረፊያው ላይ መድረሱን የአገሪቱ ዜና ወኪል ዘግቧል።
    • ኢራቅ ኤርቢል ውስጥ በሚገኝ የአሜሪካ አየር ኃይል ሰፈር ላይ ያነጣጠረ ድሮን በአሜሪካ ኃይሎች ተመትቶ መውደቁን ሮይተርስ ዜና ወኪል ዘግቧል።
    • የእስራኤል ጎረቤት በሆነችው ዮርዳኖስ ላይ ከኢራን የተተኮሱ ሁለት ሚሳዔሎች በፀረ ሚሳዔል ተመትተው እንዲወድቁ መደረጋቸው ተዘግቧል።
    • አስራኤልም በበኩሏ በመላው አገሪቷ የአደጋ ማስጠንቀቂያ ደወል እንዲሰማ ያደረጉ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው የኢራን ሚሳዔሎች እንደተተኮሰባት አስታውቃለች። የእስራኤል ጦር የኢራን ዓላማ “ሰላማዊ ሰዎችን ማሸበር እና የመኖሪያ አካባቢዎችን ማወደም ነው” ሲል ከስሷል።
  11. እስራኤል በርካታ የኢራን “ባለሥልጣናትን” መግደሏን ተናገረች

    አንድ ከፍተኛ የእስራኤል ወታደራዊ ባለሥልጣን ዛሬ በተፈጸመው ጥቃት የኢራን መንግሥት “በርካታ ከፍተኛ መሪዎች ተደምስሰዋል” ሲሉ ተናገሩ።

    ባለሥልጣኑ እንዳሉት ጥቃቱ ከተፈጸመባቸው ስፍራዎች መካከል በሦስት ቦታዎች ላይ የኢራን መንግሥት ባለሥልጣናት ተሰብስበው ነበር ብለዋል።

    የእስራኤል መከላከያ ኃይል ከአሜሪካ ሠራዊት ጋር በቅርብ በመተባበር “ወሳኝ እና በርካታ” ዒላማ ሊሆኑ የሚችሉ ባለሥልጣናት ስም ዝርዝር ሲያዘጋጅ መቆየቱን ባለሥልጣናት ገልጸዋል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ የኢራን እስላማዊ አብዮታዊ ዘብ አመሻሽ ላይ አዲስ ተከታታይ የሚሳዔል ጥቃቶችን በመካከለኛው ምሥራቅ በሚገኙ የአሜሪካ ወታደራዊ ጦር ሰፈሮች ላይ መፈጸሙን አስታውቋል።

    የፈረንሳይ ዜና ወኪል ኤኤፍፒ የኢራን መንግሥት ቴሌቪዥንን በመጥቀስ እንደዘገበው የኢራን ሠራዊት ቀን ላይ የጀመረውን ጥቃት አጠናክሯል።

  12. የእስራኤል ጦር ጥቃቱን ማጠናቀቁን ሲገልጽ፣ የተመድ ፀጥታ ምክር ቤት በአስቸኳይ ሊሰበሰብ ነው

    በኢራን ላይ የተፈጸመው ጥቃት

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የእስራኤል መከላከያ ኃይል “በኢራን አገዛዝ” ላይ አካሄድኩ ያለውን “መጠነ ሰፊ ጥቃት” ማጠናቀቁን ሲያስታውቅ፤ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት አስቸኳይ ስብሰባ ሊያደርግ ነው።

    እስራኤል ከአሜሪካ ጋር በመቀናጀት ቅዳሜ ጠዋት በኢራን ላይ በከፈተችው ጥቃት "አንዱ ዒላማ የነበረው በምዕራባዊ ኢራን ኬርማንሻህ አካባቢ ያለው ዘመናዊ የአየር ጥቃት መከላከያ ሥርዓት” እንደነበረ የእስአኤል ጦር ገልጿል።

    ጦሩ በመግለጫው የተፈጸሙት ጥቃቶች “የኢራን አብዮታዊ ዘብ አቅምን ለማዳካም እና በእስራኤል ላይ ሊፈጸሙ የሚችሉ ጥቃቶችን ለማምከን የእስራኤል አየር ኃይል በኢራን አየር ክልል ውስጥ የሚያካሂደውን ጥቃት ያለ እንቅፋት ለመፈጸም የሚሰስችል ነው” ብሏል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ የመንግሥታቱ ድርጅት የፀጥታው ምክር ቤት ዛሬ ቅዳሜ በኒው ዮርክ የሰዓት አቆጣጠር ከሰዓት በኋላ በተፈጸመው ወታደራዊ ጥቃት ላይ ለመነጋገር አስቸኳይ ስብሰባ ጠርቷል።

    ስብሰባው እንዲካሄድ የጠየቁት ባህሬን፣ ኮሎምቢያ፣ ቻይና፣ ሩሲያ እና ፈረንሳይ ሲሆኑ፣ የመንግሥታቱ ድርጅት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ ቀደም ብለው “በመካከለኛው ምሥራቅ የታየውን ወታደራዊ ጥቃት” አውግዘዋል።

    ዋና ፀሐፊው ባወጡት መግለጫ ወታደራዊ ጥቃቶቹ ዓለም አቀፍ ሰላምን እና ደኅንነትን የሚጎዱ በመሆናቸው “በአስቸኳይ እንዲቆሙ” ጠይቀዋል።

  13. መሪዎቿ ዒላማ ደያረገ ጥቃት የተፈጸመባት ኢራን “ለወራሪዎች ትምህርት እንደምትሰጥ” ገለጸች

    ኢራን በባህሬን ዋና ከተማ ማናማ ላይ በፈጸመችው ጥቃት የተፈጠረ ጭስ

    የፎቶው ባለመብት, Reuters

    የምስሉ መግለጫ, ኢራን በባህሬን ዋና ከተማ ማናማ ላይ በፈጸመችው ጥቃት የተፈጠረ ጭስ

    እስራኤል እና አሜሪካ በተለያዩ የኢራን ግዛቶች እና ከተሞች ላይ የፈጸሙት ጥቃት መሪዎች ላይ ያነጣጠሩ እንደሆነ አስራኤል ስታረጋግጥ ኢራን ደግሞ አጸፋ እንደምትሰጥ ገልጻለች።

    ጥቃቱን ተከትሎ ኢራን በእስራኤል እና የባሕረ ሰላጤው አገራት በሆኑት ኤምሬትስ፣ ኳታር፣ ባህሬን እና ኩዌት ላይ የአጸፋ ጥቃት በመፈጸም የሙከራ እርምጃ መውሰዷን አስታውቃለች።

    ከአሜሪካ ጋር በተደረጉት ድርድሮች ላይ ዋነኛ ተሳታፊ የሆኑት የኢራን የውጭ ጉዳይ አባስ አራግቺ በአገራቸው ላይ ለተፈጸመው ጥቃት በሚሰጠው አጸፋ “ኢራን ወራሪዎችን ትምህርት ትሰጣለች” ሲሉ ዝተዋል።

    ሚኒስትሩ አሜሪካ እና አስራኤል በጋራ የፈጸሙት ጥቃትን “ምክንያት የለሽ፣ ሕገወጥ እና ተቀባይነት የሌለው” በማለት አውግዘውታል።

    አራግቺ በኤክስ ገጻቸው ላይ ባሰፈሩት ጽሁፍ የትራምፕ “ቅድሚያ ለአሜሪካ” የሚለው መፈክራቸው “ቅድሚያ ለእስራኤል” ወደሚል ተቀይሯል በማለት የአሜሪካንን ፕሬዝዳንት ተችተዋል።

    የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ለተፈጸመባቸው ጥቃት ኃያል ያሉት የኢራን ጦር ኃይል “ለዚህ ቀን ተዘጋጅቷል፣ ለወራሪዎች የሚገባቸውን ትምህርት ይሰጣቸዋል” ብለዋል።

  14. የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ በርካቶች በረራቸውን ሰረዙ

    በመካከለኛው ምሥራቅ የተፈጠረውን ወታደራዊ ግጭት ተከትሎ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ በርካታ የአፍሪካ እና የሌሎች አገራት አየር መንገዶች ወደ አካባቢው የሚያደርጓቸውን ጉዞዎች ሰረዙ።

    በአፍሪካ ትልቁ አየር መንገድ የሆነው የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ተለያዩ የመካከለኛው ምሥራቅ አገራት የሚያደርጋቸውን በረራዎች በደኅንነት ስጋት ምክንያት ለጊዜው አቋርጧል።

    በዚህም ምክንያት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ወደ ዮርዳኖስ አማን፣ እስራኤል ቴል አቪቭ እና ሊባኖስ ቤይሩት የሚያደርጋቸውን በረራዎች ሰርዟል።

    በተመሳሳይ የኬንያ፣ የሞሮኮ እና የሩዋንዳ አየር መንገዶችም በረራዎቻቸው ተስተጓጉሏል።

  15. የኢራን የአጸፋ ምላሽ

    ዛሬ ቅዳሜ ጠዋት እስራኤል በኢራን ላይ ጥቃት መክፈቷን ተከትሎ የእስራኤል ሠራዊት ከኢራን በኩል ሚሳዔሎች መተኮሳቸውን አሳውቋል። ጦሩ ሚሳዔሎቹን መመከቱን ሲገልጽ ፍንዳታዎች በአካባቢው ተሰምተዋል።

    ኢራን የአጸፋ ጥቃት የፈጸመችው በእስራኤል ላይ ብቻ ሳይሆን በዙሪያዋ ባሉት የአሜሪካ ወዳጅ በሆኑት አገራት ላይ ጭምር ነው።

    የኢራን ፋርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው በአገራቱ ያሉ ወታደራዊ ተቋማት ላይ ያነጣጠሩ ጥቃቶችን ፈጽማለች። በዚህም በኳታር ያለው የአሜሪካ አየር ኃይል ሰፈር እና በባህሬን ያለው የባሕር ኃይል ሰፈር ጥቃት ደርሶባቸዋል።

    በተጨማሪም የአሜሪካ ጦር ኃይል ባለባቸው በሌሎችም የባሕረ ሰላጤው አገራት በሆኑት በኳታር፣ በኩዌት፣ በአረብ ኤምሬትስ እና በባሕሬን ፍንዳታዎች መሰማታቸው ተዘግቧል።

    የኢራንን የአጸፋ ጥቃት ተከትሎ ሳዑዲ አረቢያ ኢራንን አውግዛለች።

  16. በኢራን በተፈጸመው ጥቃት ከ40 በላይ ሰዎች መገደላቸው ተዘገበ

    አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ ከከፈቱት ጥቃት ጋር በተያያዘ በደቡባዊቷ ኢራን ግዛት ሆርሞዝጋን ውስጥ በምትገኘው ሚናብ ከተማ በሚገኝ ትምህርት ቤት ላይ በተፈጸመ ጥቃት በርካታ ተማሪዎች መገደላቸው ተዘገበ።

    የኢራን መንግሥት የዜና ወኪል የሆነው ኢርና እንደዘገበው ሴት ልጆች በሚማሩበት የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት ላይ በደረሰው ጥቃት የተገደሉ ተማሪዎች ቁጥር ወደ 40 ደርሷል።

    የግዛቱ አስተዳዳሪ ሞሐመድ ራድሜህር ተጨማሪ 48 ሰዎች የቆሰሉ ሲሆን የሞቾች ቁጥር እንደሚጨምር ስጋታቸውን ገልጸዋል።

    የኢራን ሜህር የተባለው የዜና ወኪል ደግሞ በዋና ከተማዋ ምሥራቃዊ ክፍል ውስጥ በሚገኝ ትምህርት ቤት ላይ በተፈጸመ ጥቃት ሁለት ተማሪዎች መገደላቸውን ዘግቧል።

    ኢራን ለውጭ የዜና ወኪሎች ፈቃድ ስለምትከለክል የደረሰውን ጉዳት በተመለከተ ከገለልተኛ ወገኖች ለማረጋገጥ አዳጋች ነው።

  17. ኢራን ራሷን ለመከላከል ያላትን አቅም ሁሉ እንደምትጠቀም አስታወቀች

    አራጋቺ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    የኢራን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አባስ አራግቺ አገራቸው ራሷን ለመከላከል ያላትን ወታደራዊ አቅም ሁሉ ትጠቀማለች አሉ።

    አራግቺ እንደ ሳዑዲ አረቢያ፣ የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ፣ ኳታር፣ ኩዌት፣ ባህሬን እና ኢራቅ ካሉ አገራት ጋር የስልክ ውይይት ማድረጓን ተገልጿል።

    በዚህ የስልክ ውይይት ወቅት ኢራን የአገሪቱን አንድነት ለመጠበቅ ስትል ያላትን የወታደራዊ አቅም ሙሉ ለሙሉ እንደምትጠቀም ለመካከለኛው ምሥራቅ አገራት ባለሥልጣናት አስታውቃለች።

    አራግቺ እነዚህን አገራት አሜሪካ እና እስራኤል ኢራን ላይ ጥቃት ለመፈጸም "ተቋማቶቻቸውን እና ግዛታቸውን አላግባብ እንዳይጠቀሙ የመከላከል ኃላፊነት" እንዳለባቸው አሳስበዋል። ኢራን የምትተማመንበት እስላማዊው አብዮታዊ ዘብ ማን ነው? ምንስ አቅም አለው?

  18. የአሜሪካ ጦር በመካከለኛው ምሥራቅ

    ካርታ

    በኢራን ላይ ጥቃት ለመፈጸም ስትዝት የቆየችው አሜሪካ ወሳኝ የአየር ኃይል አውሮፕላኖችን እና የባሕር ኃይል መርከቦችን ለሳምንታት ወደ ባሕረ ሰላጤው አካባቢ ስትልክ ቆይታለች።

    አሜሪካ በኢራን ላይ ጥቃት ስትከፍት የሚሰማሩት እነዚህ ብቻ ሳይሆኑ በኢራን ዙሪያ ባሉ አገራት ውስጥ ባሉ ጦር ሰፈሮቿ የሚነሱ ኃይሎችም ይጨመሩበታል።

    በዚህም ምክንያት ዛሬ እስራኤል እና አሜሪካ ኢራን ላይ ጥቃት ሲፈጽሙ ኢራን በአጸፋው በዙሪያዋ ባሉ አገራት ውስጥ በሚገኙ የአሜሪካ ጦር ሰፈሮች ላይ ሚሳዔሎችን መተኮሷ ተዘግቧል።

    ለመሆኑ በኢራን አቅራቢያ በመካከለኛው ምሥራቅ አካባቢ ለአሜሪካ ጥቃት ወሳኝ ሊሆኑ ሚችሉት የጦር ሰፈሮች የት ይገኛሉ?

  19. በኢራን ላይ ስለተፈጸመው ጥቃት የዓለም መሪዎች ምን አሉ?

    ከቴህራን ለመውጣት የሚጠባበቁ አሽከርከሪዎች በዋና ጎዳናዎች ላይ

    የፎቶው ባለመብት, EPA

    አሜሪካ እና እስራኤል በኢራን ላይ የፈጸሙትን ጥቃት እና የቴህራንን ምላሽ ተከትሎ የዓለም መሪዎች መግለጫዎችን አውጥተዋል።

    የአውሮፓ ኅብረት ኮሚሽን ፕሬዝዳንት ኡርሱላ ቮን ደር ሌየን የአውሮፓ ኅብረት በኢራን "ጨፍጫፊ ሥርዓት" ላይ "ሰፊ ማዕቀቦችን" መጣሉን አስታውሰዋል። "ሁሉም ወገኖች ሰላማዊ ዜጎችን እንዲጠብቁ እንዲሁም ዓለም አቀፍ ሕግን እንዲያከብሩ” ጥሪ አቅርበዋል።

    የጣሊያን ጠቅላይ ሚኒስትር ጆርጂያ ሜሎኒ ቢሮ በበኩሉ ለኢራን ሰላማዊ ዜጎች ያለውን አጋርነት በመግለጽ፣ የሲቪል እና የፖለቲካ መብቶች እንዲከበሩ ጠይቋል። ጽህፈት ቤቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሜሎኒ ውጥረቱን ለማርገብ የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ አጋሮቻቸውን እና የቀጠናውን መሪዎችን እንደሚያማክሩ ጠቅሷል።

    የአውስትራሊያ ጠቅላይ ሚኒስትር አንቶኒ አልባኔዝ አገራቸው "ጀግናው የኢራን ሕዝብ ጋር በሚያደርገው ትግል ከጎኑ ትቆማለች" በማለት ኢራን የኒውክሌር ጦር መሣሪያ እንዳይኖራት ለመከላከል በሚደረገውን ጥረት ትደግፋለች ብለዋል።

    ይህ በእንዲህ እንዳለ የሩሲያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአሜሪካ እና የእስራኤልን ድርጊት "ግድየለሽ" ሲል በመጥራት ዓለም አቀፍ ሕግን የሚጥስ መሆኑን ገልጿል። ሩሲያ ሁለቱ አገራት ፖለቲካዊ እና ዲፕሎማሲያዊ መፍትሄዎች ማምጣት እንዳለባቸው ጥሪ አቅርቧል።

    ቀደም ሲል የዩናይትድ ኪንግደም መንግሥት ቃል አቀባይ አገሪቱ "ሠፊ ቀጠናዊ ግጭትን ማየት እንደማትፈልግ" አስታውቆ "ጥቅሞቻችንን ለመጠበቅ ዝግጁ ነን" ብሎ ነበር። አሜሪካ ኢራን ላይ ጥቃት ብትፈፅም ሊከሰቱ የሚችሉ ሰባት ሁኔታዎች

  20. እስራኤል የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ ቢሮ ላይ ጥቃት መፈጸሟ ተነገረ

    በኢራን ዋና ከተማ እና በበርካታ ከተሞች ላይ ጥቃት የፈጸመችው እስራኤል፣ የኢራን ጠቅላይ መሪ አያቶላህ አሊ ኻሜኒ እና የፕሬዝዳንቱን ጽህፈት ቤት ዒላማ ማድረጓ ታወቀ።

    እስራኤል በዛረው እርምጃ ኬርማንሻህ፣ ቆም፣ ኢስፋሃን፣ ታብሪዝ፣ ካራጅ እና በኬናራክ የሚገኝ የአገሪቱ ባሕር ኃይል ላይ ጥቃት ፈጽማለች።

    የእስራኤል መከላከያ ኃይል ኢራናውያን ከወታደራዊ ካምፖች አካባቢ እንዲርቁ ከጥቃቱ በፊት ማስጠንቀቂያ ሰጥቷል።

    ከቴህራን የተገኘ ሌላ ምሥል የቀድሞው የአገሪቱ ፕሬዝዳንት ማህሙድ አህመዲነጃድ መኖሪያ ጥቃት ከደረሰበት መካከል እንደሚገኝበት አመለክቷል።

    የቀድሞው ፕሬዝዳንትም ሆኑ ሌሎች የኢራን ከፍተኛ ባለሥልጣናት ላይ የደረሰ ጉዳት ስለመኖሩ የተባለ ነገር የለም።

    የኢራን አገር ውስጥ ሚኒስቴር የአገሪቱ ኃይል ሁኔታውን ለመቆጣጠር ዝግጁ መሆኑን እንዲሁም የአገሪቱ ሆስፒታሎች ዝግጁ መሆናቸውን ተናግሯል።